የጀርመንንና የአፍሪቃ ጉባኤ፤ የሜርክል ስንብት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 31.08.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመንንና የአፍሪቃ ጉባኤ፤ የሜርክል ስንብት 

አብዛኛዎቹ የጀርመን ባለሃብቶች በአፍሪቃ የመወረት ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ነው።ምንም እንኳን የሜርክል መንግሥት በርካታ መርሃ ግብሮችን ቢደግፍም በ2019 ፣ 884 ኩባንያዎች ብቻ ነበሩ በአፍሪቃ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱት።ይህም ከ2017 ጋር ሲነጻጸር በ42 ብቻ ነው ያደገው።አፍሪቃውያኑ ደግሞ የጀርመን ኩባንያዎችን ፈሪ ሲሉ ያንኳስሷቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጉባኤና የሜርክል ስንብት

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በስልጣን ዘመናቸው መጨረሻ ከአፍሪቃ መሪዎች  ጋር  ባለፈው አርብ ጉባኤ አካሂደዋል። ይኽው የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጉባኤ ሜርክል የአፍሪቃ መሪዎችን የተሰናበቱበትም ነበር። ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጀርመን የዛሬ አራት ዓመት የጀመረችው በአፍሪቃ የግል መዋዕለ-ንዋይ ፍሰት ማበረታቻ መርሃግብር ነው።ከአፍሪቃ አስራ አንድ ሃገራት ማለትም ቤኒን ፣ኮትዲቯር ፣ግብጽ ፣ኢትዮጵያ፣ጋና፣ጊኒ ሞሮኮ፣ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል ቶጎ እና ቱኒዝያ የልማት ትብብርን ወደጋራ የኤኮኖሚ ልማት የመቀየር ዓላማ ይዞ የተነሳው የዚህ መርሃግብር አጋር ናቸው።ባለፈው ሳምንት መጨረሻ  የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ መርሃ ግብር አባላት ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ጉባኤያቸውን አካሂደዋል።አብዛኛዎቹ መሪዎች በአካል በተገኙበት የተቀሩት ደግሞ በበይነ መረብ በተሳተፉበት በዚህ ጉባኤ መርሃግብሩ ያስገኛቸው ጥቅሞች ያጋጠሙት ተግዳሮቶችና ወደፊት ሊሻሻሉ የሚገባቸው አሰራሮች ተነስተዋል። ያለፈው ሳምንት ጉባኤ የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጉባኤ ይባል እንጂ፣ የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በሥልጣን ዘመናቸው ማብቂያ የአፍሪቃ መሪዎችን የተሰናበቱበት ጉባኤም ጭምር ነበር።ዶክተር ሃይንዝ ቫልተር ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪቃ ሃገራትና የጀርመን ንግድ ድርጅት ሊቀመንበር ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት ጀርመንና የኮምፓክት መርሃግብር አጋሮች በያዝነው በ2021 ዓ.ም በተለይ በውጭ ንግዱ ዘርፍ ጥሩ ውጤት አስመዝግባዋል።
«የጀርመን የአፍሪቃና የዓለም ኤኮኖሚ አሁን ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር እየታገለ ነው።ሆኖም የአፍሪቃና የጀርመን የንግድ ልውውጥ ግን በዚህ ዓመት በግልጽ እያገገመ ነው። ከአፍሪቃ ሃገራት ወደ ጀርመን የሚካሄደው የውጭ ንግድ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት (ከጥር እስከ ሰኔ) 40 በመቶ የሚጠጋ እድገት አስመዝግቧል።የጀርመን የውጭ ንግድም በሁለት ዲጂት ጨምሯል።» 

የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ መርሃግብር የተጀመረው ፣ጀርመን የቡድን ሃያ አባል ሀገራት የወቅቱ ፕሬዝዳንት በነበረችበት በጎርጎሮሳዊው 2017 ነበር። በወቅቱ ጀርመን በአፍሪቃ  የግል መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማበረታታት ቃል በመግባት ነበር መርሃግብሩን የጀመረችው።በአፍሪቃ የጀርመን ባለሀብቶች በስፋት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ማበረታታት በዚህ መርሃግብር ጀርመን ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደችው ዋናው ዓላማዋ ነበር።የጀርመን መንግሥት ከምንም በላይ የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ እንዲወርቱ ሙሉ ድጋፍ በማድረግ እንዲበረታቱ ነው ፍላጎቱ።የአፍሪቃ ሃገራትም በፋንታቸው የኤኮኖሚ ተሀድሶዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በወቅቱ ተወስቶ ነበር። መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለጉባኤተኞቹ እንደነገሩት የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ አጋርነት ውጤታማ ነው።
«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ እየሰራ ነው።በአብዛኛዎቹ የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ሃገራት የንግዱ ሁኔታ በተሀድሶ ተሻሽሏል። ከጎርጎሮሳዊው 2019 አንስቶ እስከ  2019 ድረስ ከሌሎቹ የአፍሪቃ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር የጀርመን ኩባንያዎችን ጨምሮ መካከለኛ የሚባል መዋዕለ ንዋይ አፍሰዋል።ከዚህ በተጨማሪ በጎርጎሮሳዊው 2020 በኮምፓክት ሃገራት 0.1 በመቶ የኃኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል።ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ኤኮኖሚዎች ግን የገጠማቸውን የእድገት ማሽቆልቆል መቋቋም ነበረባቸው።
ሜርክል እንደተናገሩት ምንም እንኳን እድገት ቢታይም አሁንም አጋርነቱም የሚያደናቅፉ ተግዳሮቶች  አልጠፉም። እነዚህን ማስተካከሉም እየታሰበበት ነው ብለዋል ሜርክል
»አሁን ያሉትን የንግድና የኢንቬስትመንት መሰናክሎች በኮምፓክት ማዕቀፍ እንዴት መቀነስ እንደሚቻል አሁንም እያሰብን ነው።አፍሪቃ ብዙ የገበያ አቅም አላት። ሆኖም ይህ በአግባቡ ሊሰራበት ይገባል።የወደፊቱ ላይ ማተኮሩ ጥሩ ምክንያት አለው፤በተለይ በታዳሽ የኅይል ምንጭ ላይ ትኩረት መሰጠቱ። ይህን ማስፋፋቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም ሙቀት መጠን መጨመርን ለመከላከል የተቀመጠው ግብ ላይ ለመድረስ ትልቅ ፋይዳ አለው።»
በጉባኤው ላይ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ጥቅም ላይ በማዋል ለመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አድናቆታቸውን ከገለጹት ተሳታፊዎች አንዱ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ የገንዘብ

ሚኒስትር ኒኮላስ ካዛዲ የአፍሪቃ ሃገራትና የጀርመን አጋርነት ግልጽ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበው ነበር።ካዛዲ አፍሪቃ እንደ ጥሬ እቃ ምንጭ ሳይሆን እንደ ሙሉ አጋር መታየት አለባት ነው ያሉት።  
«ጀርመን በመራኂተ-መንግሥት ሜርክል አመራር ዘመን የኃይል ምንጭን ወደ ታዳሽ ኃይል በመቀየር ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ።እንደምታውቁት ዓለማችን የኃይል ምንጭ ለውጥ ለማድረግና በአፍሪቃም በ2021 የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እና የአረንጓዴ ኃይል  ምንጮች አሏት።አፍሪቃ በዚህ ረገድ ከጀርመን ጋር ስልታዊ አጋርነት እንዲኖራት ትፈልጋለች።ያ ማለት ግን ጥሬ እቃ አቅራቢ ሳይሆን ፣በእውነት ከጀርመን ጋር  ስልታዊ አጋር ፣ ሙሉ አጋር መሆን ነው ፍላጎቷ።»
ካዛዲ በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ስደትን ለማስቆም በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
«ለአፍሪቃ ወጣቶች የሜዴትራንያንን ባህር ከመሰደድ ውጭ ሌላ አማራጮችን እንዲያስቡ ማድረግ አለብን።ይህን ልናስቀርና ልንቋቋም  የምንችለው  በጋራ ተስማሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ነው።እንደ አፍሪቃ አህጉር ከጀርመንና ከአውሮጳ ጋር ይህ ተግዳሮት ለመወጣት ዝግጁ ነን።ይህን ለማሳካትም ብዙ የአፍሪቃ ሃገራት ጀርመን ያቀረበችውን የቡድን 20 ስምምነት ፈርመዋል። »
የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር ደግሞ ጀርመን የአፍሪቃን እድገት እውን ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አካል መሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
«አፍሪቃ በመጪዎቹ አሥርት ዓመታት የተለያዩ እድሎች የምታገኝበትና የገበያ እድገት የሚመዘገብባት ክፍለ ዓለም ናት።ባለፉት 100 ዓመታት በአውሮጳ እንደሆነው ፣በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም፣ በርካታ መሰረተ ልማቶች ይገነባሉ።የዚህ አካል መሆን እንችላለን ፣ማድረግም መሆንም አለብን ፤እንፈልጋለንም።»
«ሁላችንም ጥሩ የኤኮኖሚ ተስፋ ባላቸው የአፍሪቃ ሃገራት ጠንካራ ፍላጎት አለን።አፍሪቃ ለጀርመን ኤኮኖሚ አስፈላጊ አጋር ናት።ለዚህ ብዙ ጥሩ ምክንያቶች አሉ።ክፍለ ዓለሙ በጣም ሳቢ

Infografik Karte Mitgliedsländer der Initiative Compact with Africa DE

ገበያ ነው ።በመጪዎቹ ጥቂት አሥርት ዓመታት ከፍተኛ እድገት ከሚያመዘግቡ አካባቢዎች ጋር የመሰለፍ አቅም አላት።ከጥቂት ዓመታት በፊት አንስቶ አፍሪቃ ቢያንስ 6 በመቶ አማካይ የኤኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች።»
ሜርክል የአፍሪቃ መሪዎችን በተሰናበቱበት በዚህ ጉባኤ  በሥልጣን ዘመናቸው አፍሪቃ በጀርመን ፖለቲካ ውስጥ ከከዚህ ቀደሙ ትልቅ ሚና እንደነበራት ተወስቷል።ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ከተጀመረበት ከ2017 እስከ 2019 የጀርመን የአፍሪቃ ውረታ በ1.57 ቢሊዮን ዩሮ አድጓል።ይህም መካከለኛ የሚባል እድገት ነው።በሌላ በኩል ከሌላው ክፍለ ዓለም ጋር ሲነጻጸር የጀርመን የአፍሪቃ ውረታ አንድ በመቶ ብቻ ነው።አብዛኛዎቹ የጀርመን ባለሃብቶች በአፍሪቃ የመወረት ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ነው።ምንም እንኳን የሜርክል መንግሥት በርካታ መርሃ ግብሮችን ቢደግፍም በ2019 ፣ 884 ኩባንያዎች ብቻ ነበሩ በአፍሪቃ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱት።ይህም በ2017 ከተደረገው ጋር ሲነጻጸር በ42 ብቻ ነው ያደገው።ለዚህም የጀርመን መንግሥት መር ግብሩ እንዲሳካ በቢሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ አፍሷል ፤የምክር አገልግሎት እና ዋስትናዎችም ሰጥቷል። አፍሪቃውያኑ ደግሞ የጀርመን ኩባንያዎችን ፈሪ ሲሉ ያንኳስሷቸዋል።ሌላው እውነታ በአፍሪቃ ውድ ለሆኑት የጀርመን እቃዎች በቂ ገበያተኛ አይገኝም።ከጀርመን የአፍሪቃ ውረታና ንግድ ሁለት ሶስተኛው በደቡብ አፍሪቃ ነው የሚካሄደው። በአሁኑ ሰዓት አነጋጋሪ የሆነው ከጀርመን ምርጫ በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል የሚለው ነው።ይህም መሪዎቹ ለሜርክል ያነሱት ጥያቄ ነበር።የልማት ሚኒስትሩየጌርድ ሙለር መነሳትም አሳስቧቸዋል። ለጊዜው ማን ሥልጣን እንደሚይዝ አልታወቀም።አዲሱ መንግሥትም ለአፍሪቃ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ አሁን ግልጽ አይደለም።የጀርመን መንግሥት ግን ቃል በገባው መሠረት እንደሚቀጥል ነው የሚጠበቀው።የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ አጋር ሃገራት ምርጫም ያወዛግባል።ከመካከላቸው አምባገነኖች የሚባሉ መኖራቸው አሁንም እንዳጠያየቀ ነው።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic