የጀርመንና የዓረቡ ዓለም የንግድ ግንኙነት | ኤኮኖሚ | DW | 23.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመንና የዓረቡ ዓለም የንግድ ግንኙነት

የጀርመንና የዓረቡ ዓለም የመንግሥታትና የኢንዱስትሪ ተጠሪዎች እ.ጎ.አ. ከ 1997 ወዲህ በያመቱ የሚያካሂዱት ስብሰባ ለንግዱ ግንኙነት መዳበር ማዕከላዊ መድረክ ሆኖ ቆይቷል። ኤኮኖሚዋ በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረው ጀርመን በአረብ አገሮች ላይ ያላት ትኩረት እየደገ ነው የመጣው። የጀርመን የንግድና የኢንዱስትሪ ም/ቤት የውጭ ተጠሪ ሚሻኤል ፋይፈር በበርሊኑ የጋራ መድረክ ላይ እንደገለጹት የአረቡ ዓለም የንግድ አካባቢ ከምሥራቅ እሢያና ምሥራቅ አውሮፓ ጎን ለጀርመን ኤኮኖሚ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር እየሆነ ነው።

“በአካባቢው የምናካሂደውን የውጭ ንግድ ባለፈው ዓመት እንደገና አሥር በመቶ ለማሳደግ ችለናል። ቀደምቱን አገሮች ከወሰድን ለምሳሌ ሳውዲት አረቢያን በዚህ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ ሶሥት ወራት ብቻ 43 በመቶ ዕድገት ታይቷል። ይህ በዓለም ላይ ተመሳሳይ የሌለው ነው። ...”

ሚሻኤል ፋይፈር አያይዘው እንዳስረዱት ጀርመን ለተባበሩት ኤሚር ግዛቶች በያመቱ በ 3.5 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚገመት፤ ለሳውዲት አረቢያም እንዲሁ 3.1 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያወጣ ምርት ትሸጣለች። ግብጽ፣ ኩዌይትና አልጄሪያም ከአንድ ሚሊያርድ በሚበልጥ ድርሻ ለጀርመን በአካባቢው ጠቃሚዎቹ የንግድ ደምበኞች ናቸው።

ይሁንና የአረብ-ጀርመኑ የንግድና የኢንዱስትሪ ማሕበር ፕሬዚደንት፤ የቀድሞው የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ካርል-ዲተር ሽፕራንገር እንደሚሉት ንግዱን ለማስፋፋት ያለው ዕድል ሁሉ ጥቅም ላይ ውሏል ማለት አይደለም። ያልተነካው ዘርፍ ገና ብዙ ነው።

በአረቡ ዓለም ዛሬ የኢንዱስትሪና የዕርሻ ዘርፍን በዘመናዊ መልክ የማቀናጀት፣ መገናኛ መዋቅሮችን የማስፋፋት፤ እንዲሁም የኤነርጂ፣ የሕክምና፣ የቱሪዝምና የትምሕርት ዘርፎችን የማሳደግ ሰፊ ፍላጎት አለ። ተገቢው ዕውቀት Know-how ያላቸው የጀርመን ኩባንያዎች ደግሞ የአረቡን ዓለም የኤኮኖሚ ይዞታ ዘመናዊ በማድረጉ በኩል በተግባር አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚስማሙ ናቸው።

በሌላ በኩል ጀርመን ከአረቡ ዓለም የምታስገባው ምርት በተለይም ነዳጅ ዘይት ባለፈው ዓመት አሥር በመቶ ዕድገት ታይቶበታል። በኤውሮ-ሜዴትራኒያኑ ሽርክና መስፈን የተነሣ የወደፊቱ የኤኮኖሚ ግንኙነት እንዲያውም የተሻለ እንደሚሆን ነው የሚታመነው። በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ደረጃ በደረጃ በአውሮፓው ሕብረት ዓባል መንግሥታትና በ 12ቱ ደቡባዊና ምሥራቃዊ የሜዴትራኒያን ተዋሣኝ ሃገራት መካከል ለኢንዱስትሪ ምርቶች ነጻ የንግድ ክልል ለማቋቋም ታስቧል።

በርከት ባሉ አረብ አገሮች ባለፉት ጊዜያት የፖለቲካና የኤኮኖሚ ለውጦች መካሄዳቸው ዕቅዱን ፍቱን ለማድረግ ተስማሚ ሁኔታዎችን እያመቻቹ መሆኑ ነው የሚነገረው። ይህ ግብጽንም ይጠቀልላል። በአረቡ ዓለም በሕዝብ ብዛት ቀደምት በሆነችው አገር ግብጽ ቢሮክራሲን በመቀነስና ገበዮችን በመክፈት በኩል ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጠቃሚ ዕርምጃ እየተደረገ ነው። የግብጽ የመዋዕለ-ነዋይና የነጻ ኤኮኖሚ ክልል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሃላፊ ዚያድ-ባሃ-ኤል-ዲን በርሊኑ መድረክ ላይ በአገሪቱ የቀረጥ ታሪፍ ላይ የተደረገው ለውጥ፣ አዲስ የግብር ሕግና ለባለሃብቶች ዋስትና የሚያረጋግጥ ደምብ ያስከተለውን የመጀመሪያ ዕርምጃ አስተዋውቀዋል።

ኤል-ዲን አያይዘው እንዳስረዱት “ግብጽ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የኑሮ ውድነትን በሰፊው ልትቀንስና መረጋጋት አጥቶ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ክምችቷንም በጠነከረ ሁኔታ ልታሻሽል በቅታለች። የኤኮኖሚው ይዞታ በአጠቃላይ ተሻሽሏል፤ የምናስበው 2004 እና 2005 ከዚህ ቀደሙ በበለጠ ሰፊ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን ወደ ግብጽ በመሣቡ በኩል ጠቃሚ ዕድገት ያሣያሉ ብለን ነው።”

የጀርመን የውጭ ንግድ በኢራቅም አስቸጋሪው ሁኔታ ሳይገታው ባለፈው ዓመት 78 በመቶ በማደግ ወደ 370 ሚሊዮን ኤውሮ ከፍ ሊል በቅቷል። የጀርመን ኩባንያዎች ከኢራቅ የንግድ ግንኙነቱን የሚያቀናብሩት የዮርዳኖስን ርዕሰ-ከተማ አማንን ማዕከል በማድረግ ነው። ከዚሁ በተጨማሪም የጀርመን-ኢራቅ የኤኮኖሚ ጉባዔዎች በዚህ በጀርመን በዓመት ከሁለት እስከ ሶሥት ጊዜ ይካሄዳሉ። መጪው በሚቀጥለው ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ሚዩኒክ ከተማ ላይ ይደረጋል።

ከአረቡ ዓለም ችግሮች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ውሃ ነው። የጀርመን ኩባንያዎች በዚሁ የውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ ሊሆኑ በሚችሉበት ሁኔታ በመጪው ሣምንት መጀመሪያ በሰሜን ጀርመን ሃኖቨር ከተማ ሁለት ቀናት የሚፈጅ ጉባዔ ያካሂዳሉ። በውሃው ችግር መፍትሄ ላይ የሚያተኩረው ጉባዔ ግንኙነት ለመፍጠርና የንግድ ስምምነቶችን ለማስፈን የተወጠነ ነው።

የባሕረ-ሰላጤው የውሃ ክምችት በያንዳንዱ ሰው በነፍስ-ወከፍ ሲታሰብ ጥቂት ቢሆንም ፍላጎቱና ፍጆቱ ግን በአንጻሩ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ነው የሚገኘው። የጀርመንና የአረቡ ዓለም ጠበብት በዚህ በመጀመሪያው የሃኖቨር የውሃ ጉባዔ ላይ መፍትሄ ለማፈላለግ ይጥራሉ።

ችግሩ ቀላል አይደለም። የባሕረ-ሰላጤው ውሃ ሊቀምሱት የሚያንገፈግፍ ጨዋማ ነው። ባሕሬይንን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የአገሪቱን ገጽታ የሚያንጸባርቁት ዝገታማ ቋጥኞች ምድር ውስጥ ለሚገኘው ውሃ ጠንቅ መሆናቸው አልቀረም። ሁኔታው ይህን የመሰለ ሲሆን ባሕሬይን በነፍስ-ወከፍ በየቀኑ የምትፈጀው ውሃ ከ 500 ሊትር ይበልጣል። ይህ በአውሮፓ ካለው አማካይ ፍጆት ሲነጻጸር ሶሥት እጥፍ መሆኑ ነው። 90 በመቶው ውሃ ከምድር የሚመነጭ ሲሆን አሥር በመቶው ከሰላሣ ዓመታት ወዲህ የባሕር ውሃ ከጨው ይዘቱ ከሚጸዳባቸው ማጥሪያ መሣሪያዎች ነው።

በኩዌይትም ቢሆን ውሃ ከነዳጅ ዘይት ይበልጥ ይወደዳል። አገሪቱ ፍላጎቷን የምትወጣው ከጨው የጸዳ የባሕር ውሃን በማከማቸት ነው። በሌላ በኩል በምድር ውስጥ የሚገኘው ውሃ በነዳጅ ዘይት ንጣፍ በመበከል አደጋ ላይ ይገኛል። ከሃምሣ ካሪ-ኪሎሜትር የሚበልጠው የአገሪቱ ምድረበዳ ብክለት የደረሰበት ነው። ሁለተኛው የባሕረ-ሰላጤው ጦርነት ጥሎት ያለፈው መጥፎ ቅርስ የዘይት ፍሳሽ ገና አሁን ነው እንዲወገድ መደረግ የጀመረው።

በተባበሩት አረብ ኤሚሮች ዛሬ የአንድ ሊትር ውሃ ዋጋ የሊትር ቤንዚንን ያህል ወይም ከዚያ የበለጠ ነው። እንዲህም ሆኖ ቁጠባ የሚባል ነገር አይታወቅም። በቀን በነፍስ-ወከፍ 800 ሊትር ገደማ የሚጠጋ ውሃ ይፈጃል። እርግጥ አብዛኛው ውሃ በቧምቧ በየቤቱ የሚደርስ ሣይሆን ደረቁን የእርሻ መሬት ለማልማትና ፍራፍሬ-አትክልት ለማምረት እንዲፈስ ነው የሚደረገው። የባሕረ-ሰላጤው አገሮች መልሶ የተጣራ ውሃን መጠቀማቸውም እየጨመረ መጥቷል። ይሁንና ችግሩ የምድሩ ውሃ ከፍታ ከሰላሣ ዓመታት ወዲህ በያመቱ በአንድ ሜትር እየቀነሰ መምጣቱ ነው።

ይህ አቆልቋይ ሂደት ከቀጠለ ፈጠነም ዘገየ አቅርቦቱ የባሕር ውሃን ከጨው ይዘት በሚያጸዱት ማጣሪያ መሣሪዎች ላይ ጥገኛ መሆኑ የማይቀር ይሆናል። የባሕረ-ሰላጤው መንግሥታት ባለፉት ሃያ ዓመታት በባሕር ውሃ ማጣሪያዎቹ መሣሪያዎች ላይ ሃምሣ ሚሊያርድ ዶላር አፍስሰዋል። ሣውዲት አረቢያ አራት መቶ ማጣሪያዎች ሲኖሯት፣ ኩዌይት ሶሥት ደርዘን የሚጠጉ፣ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤሞሮች መቶ ገደማ የሚጠጉ አሏቸው።

ሆኖም ግን የጀርመን የንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቤት ተጠሪዎች እንደሚሉት አብዛኞቹ መሣሪያዎች ያረጁ ናቸው። ቆሻሻ ምድር ውስጥ ወዳለው ውሃ እንዲዘልቅና እንዲበክል ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ ችግርና የተሃድሶው አጣዳፊነት ለጀርመን ኩባንያዎች በሚሊያርዶች የሚገመት የንግድ ዕድልን ነው የፈጠረው። የጀርመን ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ዕውቀት በአረቡ ዓለም ታላቅ ክብደት የሚሰጠውና ዝናን ያተረፈ ነው።
የባህሬይን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ተጠሪ ሞሐመድ ቃንበር ከአረብ-ጀርመኑ ጉባዔ ጭብጥ መፍትሄ ይጠብቃሉ። ለባሕረ-ሰላጤው የውሃ ችግር ከጀርመናውያኑ በኩል መፍትሄ ለመስማት እንሻለን ባይ ናቸው። የጀርመን ቴክኖሎጂ በሥራ ላይ ከዋለ ችግሩን መወጣት ይቻላል የሚሉት የሙያው አዋቂዎችም ብዙዎች ናቸው። መፍትሄ ሰጭ ዘዴዎችን ከሚያቀርቡት የጀርመን ኩባንያዎች አንዱ በዚህ በኖርድ-ራይን-ቬስትፋሊያ ፌደራል ክፍለ-ሐገር ሄርተን በተሰኘች ስፍራ ተቀማጭ የሆነው አኩዋ-ሶሣይቲይ የተሰኘ ተቋም ነው።
ኩባንያው በአየር ላይ የሚገኝ እርጥበትን አጣርቶ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት የሚያስችል መሣሪያን ያቀርባል። ለግንዛቤ ያህል በአካባቢ አየር ላይ በመላው የዓለም ወንዞች ውስጥ ከሚገኘው አሥር ዕጅ የበለጠ ውሃ መኖሩ ነው የሚገመተው። በመሠረቱ ይህን ክምችት የመጠቀሙ ሃሣብ የመነጨው እንዳጋጣሚ ነው። የቴክኖሎጂው ጥበብ በጅምሩ የተወጠነው በማዕድናት ውስጥ ያለውን አየር ለማቀዝቀዝ ነበር። ከዚያ ውሃ መገኘቱ እንግዲህ ቀደምቱ ጉዳይ አልነበረም።
የመጀመሪያው የሙከራ መሣሪያ አሁን በተባበሩት አረብ ኤሚሮች ግዛት ተተክሎ በመሥራት ላይ ይገኛል። በበጋው ወራት በአካባቢው አየር ላይ ያለው እርጥበት ከፍተኛ በመሆኑ ለሙከራው ተስማሚና ያመቸ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ሆኖም የቴክኖሎጂው ሽግግር አስፈላጊው ዕውቀት ሳይታከልበትና በተለይ ደግሞ ሃብቱን በሚገባ መንከባከብ ሣይኖር ብቻውን ፍቱን የውሃ አስተዳደርን ሊያስፍን እንደማይችል ግልጽ ነው።