የጀርመንና የእሢያ የኤኮኖሚ ግንኙነት | ኤኮኖሚ | DW | 21.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመንና የእሢያ የኤኮኖሚ ግንኙነት

የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል ባለፈው ሣምንት በሩሢያ፣ በቻይናና በካዛክስታን የአምሥት ቀናት ጉብኝት አድርገው ነበር።

default

ሜርክል/ዌን ጂያባዎ

ጉብኝቱ ይበልጡን በሁለት ወገን የኤኮኖሚ ግንኙነት ላይ ሲያተኩር የተለያዩ ውሎችን በመፈራረም በስኬት ነው የተፈጸመው። ኤኮኖሚዋ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነው ጀርመን በተለይ ከቻይና ጋር ምንም እንኳ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ አልፎ አልፎ እክል መሆኑ ባይቀርም  ሰፊ የንግድ ልውውጥ እንደምታደርግ ይታወቃል። ሜርክል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዌን ጂያባዎ ሁለቴ ተናኝተው መነጋገራቸው በዚህ በኩልም መቻቻል እየተፈጠረ መሄዱን የሚያመለክት ነው። እርግጥ በሌላ በኩል የቻይናና የጀርመን ኩባንያዎች በየፊናቸው አንዱ በሌላው አገር የገበያ መሰናክሎች እንዳሉበት በመዘርዘር ቅሬታ አሰምተዋል። በጥቅሉ ግን የአንጌላ ሜርክል ጉብኝት በቻይናም ሆነ በሩሢያ ወይም በማዕከላዊው እሢያ ለጀርመን ኩባንያዎች ይበልጥ በር ከፋች ሣይሆን አልቀረም።

ሕዝባዊት ቻይና በእሢያ ክፍለ-ዓለም ዋነኛዋ የጀርመን የንግድ ሸሪክ መሆኗ ይታወቃል። በትክክል ፌደራል ሬፑብሊክ ጀርመን በንግድ ልውውጡ ረገድ ለቻይና ከጃፓን፣ ከአሜሪካና ከደቡብ ኮሪያ ቀጥላ አራተኛዋ ተባባሪ አገር ናት። አሃዝ ለመጥቀስ ያህል የንግድ ልውውጡ መጠን ባለፈው 2009 ዓ.ም. 92  ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ደርሶ ነበር። ዘንድሮም ይጨምር እንደሆን እንጂ ይቀንሳል ተብሎ አይጠበቅም።

እርግጥ የንግዱ ልውውጥ ሚዛን የጠበቀ አይደለም። ለጊዜው ጥቅሙ ወደ ቻይና ያጋድላል። ቻይና ባለፈው ዓመት የንግድ ልውውጥ በገቢ ወጪ ንግዷ ሃያ ሚሊያርድ ኤውሮ አትራፊ ነበረች። በሌላ በኩል ጀርመንም ቢሆን ለምርት መኪናዎቿና አውቶሞቢሎቿ የተረጋጋ አስተማማኝ ገበያ በማግኘት ተጠቃሚ ነው የሆነችው። የጀርመን የቻይና ንግድ በዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ውስጥ 34 ከመቶ ዕድገት ታይቶበታል። ይህም ያለ ምክንያት አልነበረም። የጀርመን የአየር በረራ ኢንዱስትሪ ተጠሪ ሽቴፋን ሽሮደር እንደሚሉት የቻይና የዕድገት ቁርጠኝነት ለጀርመን አምራቾች ጥሩ ዕድል ነው የሆነው።

“ቻይና በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሁለተኛዋ ታላቅ የሲቪል የአየር በረራ ኢንዱስትሪ ማዕከል ልትሆን መቻሏ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው። ለአየር በረራው አውሮፕላኖች ያስፈልጋሉ። እኛ ደግሞ በዝቅተኛው ሣክሶኒያ ለነዚህ አውሮፕላኖች መገጣጠሚያ ዕቃዎችን ለማቅረብ የሚችሉ በርካታ መለስተኛ ኩባንያዎች ነው ያሉን። በተረፈ ከሉፍትሃንዛ-ቴክኒክ ዘርፍ ጋር በቅርብ የምንተባበርና የማሰልጠና አካዳሚም ያለን ሲሆን ለቻይና ገበያ ትልቅ ትኩረት ነው የምንሰጠው” 

ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ወደ ቻይና የተጓዙት የአገራቸውን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ተጠሪዎች አስከትለው ነበር። ከነዚሁ መካከል በጥቂቱ የኤየርቡስ አውሮፕላን ኩባንያ አመራር ተጠሪ ቶማስ አንደርስ፣ የንጥረ-ነገር ኩባንያው የ BASF ሃላፊ ዩርገን ሃምብሬሽት፣ የኤሌክትሮኒኩ ኩባንያ የዚመንስ ሊቀ-መንበር ፔተር ሉሸርና የፎልክስዋገን ኩባንያ ሃላፊ ማርቲን ቪንተርኮርን ይገኙበታል። እነዚህ ግዙፍ የታላላቅ ኩባንያ ተጠሪዎች ቻንስለሯን አጅበው መሄዳቸው ራሱ የሚያሳየው የቻይና ገበዮች ለጀርመን ምን ያህል ክብደት እንዳላቸው ነው።                               
በነገራችን ላይ ፍልክስዋገን ኩባንያ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ቻይና ውስጥ አንድ ሚሊዮን አውቶሞቢሎችን ሲሸጥ በዚያው የሚያመርቱት ፋብሪካዎቹ ቁጥር አሁን 11 ደርሷል። የእናት ኩባንያው መቀመጫ የዝቅተኛው ዛክሶኒያ ክፍለ-ሐገር አስተዳዳሪ ዳቪድ ማክ-አሊስተር ፍልክስዋገን ወደፊት በኤሌክትሪክ ሃይል የሚንቀሳቀሱ አውቶሞቢሎችን በማቅረቡም ረገድ ተጠቃሚ እንደሚሆን ዕምነታቸው ነው።

“እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚንቀሳቀሱ 500 ሺህ አውቶሞቢሎች በቻይና አደባባዮች ላይ እንደሚሽከረከሩ ነው የሚጠበቀው። የቻይና መንግሥት እዚሁኑ ኤሌክትሮ-አውቶሞቢሎች በሥራ ላይ እንዲውሉ ማበረታታት ይፈልጋል። ግን ችግሩ ንግዱ የሚፈቀደው ለአገሩ አቅራቢዎች ብቻ መሆኑ ላይ ነበር። እርግጥ ፎልክስዋገንም አሁን ቃል ተገብቶለታል፤ እንደ ውጭ ኩባንያ ቻይና ውስጥ የሚሰራና በዚያው የሚያመርት እስከሆነ ድረስ! ፎልክስዋን ለነገሩ ይህን የሚያሟላ ነው”

እርግጥ ብዙ ዕድል ቢኖርም ቻይና ለውጭ ኩባንያዎች ቀላል ቦታ አይደለችም። በሻንግሃይ የጀርመን የንግድ ም/ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢዮአና ክራፍት እንደሚሉት ወደ ቻይና ገበዮች መዝለቁ አሁንም ብዙ መሰናክልን ማለፍ የሚጠይቅ ነው። ይፋ ጨረታ በሚደረግበት ጊዜ የውጭ ኩባንያዎች ምንም እንኳ በአገሪቱ የሰፈሩና ግብር የሚከፍሉም ቢሆኑ ገደብ አለባቸው። ይህ ደግሞ እንደ ኢዮአና ክራፍት መቀየር ያለበት ነገር ነው። የቻይና የንግድ ባለሥልጣናትም በፊናቸው የራሳቸው ቅሬታ አላቸው።

የሁለቱ ወገን ተጠሪዎች ባለፈው ቅዳሜ ከቻንስለር አንጌላ ሜርክልና ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዌን ጂያባዎ ጋር ባደረጉት ንግግር ችግራቸውን በማያሻማ መልክ ነው በግልጽ ያስቀመጡት። የጀርመን ኩባንያዎች ልዑካን የውጭ ኩባንያዎች የገበያ አግባብ ውሱን ነው በማለት ሲያሳስቡ የቻይና ባለሥልጣናት ደግሞ ከብዙ አንዱን ለመጥቀስ ያህል የጀርመንን የቪዛ ሕግ ጥብቅነት በማንሳት ወቀሣ ሰንዝረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን ጂያባዎ በበኩላቸው በቻይና የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ሁኔታ የከፋ እየሆነ ነው የሚለውን ወቀሣ ጨርሶ አልተቀበሉትም። ከቻይና ምድር የሚገቡ ሁሉ እንደ አገሪቱ ኩባንያዎች ብሄራዊው እንክብካቤ ይደረግላቸዋል ሲሉ ነው እኩልነት እንዳለ ያስረገጡት። ያም ሆነ ይህ ሁለቱ መንግሥታት የኤኮኖሚ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማዳበር ለመፈለጋቸው በጉብኝቱ መጨረሻ አሥር ውሎችን መፈራረማቸው ማረጋገጫ ነው።

የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል የአምሥት ቀናት የእሢያ ጉብኝታቸውን ያጠቃለሉት ከካዛክስታን ጋር የ 2,2 ሚሊያርድ ኤውሮ የመዋዕለ-ነዋይ ውል በመፈራረምም ነበር። ውሉ በኤነርጂ፣ በቴሌሙኒኬሺን፣ በግንቢያ፣ በቀላል ኢንዱስትሪና በእርሻ ልማት ዘርፎች ለጀርመን ኩባንያዎች ሰፊ ጥርጊያን የሚከፍት ነው። እርግጥ ካዛክስታን በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ ለጀርመን መክፈል የሚኖርባትን የ 300 ሚሊዮን ኤውሮ ዕዳ መመለስ እንዳቃታት ቢሆንም ውሉ በረጅም ጊዜ ፍሬያማ እንደሚሆን በሰፊው ይታመናል። ካዛክስታን እንደተቀሩት የማዕከላዊ እሢያ ሬፑብሊኮች ሁሉ በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለች አገር መሆኗ የሚታወቅ ነው። በነገራችን ላይ ካዛክስታን ዛሬ ለጀርመን አራተኛዋ ታላቅ የጥሬ ዘይት ምርት አቅራቢ አገር ናት።

የጀርመን ኩባንያዎች በአውቶሞቢል ወይም በምርት መኪናዎች አቅርቦት ብቻ ሣይሆን የባቡር ሃዲዶችን በመዘርጋት፣ ባቡሮችን በመገንባትና የኤነርጂ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ወዘተ.ም ሰፊ ተፈላጊነት አላቸው። ሞስኮና በርሊን በቻንስለር አንጌላ ሜርክል ጉብኝት ወቅት በብዙ ሚሊያርድ ኤውሮ የሚገመት ውል መፈራረማቸውም ለዚሁ ማስረጃ ነው። የጀርመኑ ግዙፍ ኩባንያ ዚመንስ ለሩሢያ ባቡሮችንና የነፋስ ኤነርጂ ማምረቻ አንቀሳቃሾችን ለማቅረብ ሲዋዋል ይህም ሞስኮ ያረጀ መዋቅሯን በዘመናዊ መልክ ለማደስ ያላትን ፍላጎት ለማሟላት የተወጠነ ነው።

ዚመንስ ለሩሢያ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቆምም ሲስማማ በዚሁ ዕውቀትንም እንደሚያሸጋግር ነው የሚጠበቀው። ፕሬዚደንት ሜድቬዴቭ ሁኔታው እጅግ አበረታች ነው ሲሉ ነው ደስታቸውን የገለጹት። በአጠቃላይ በውሉ መሠረት ዚመንስ በረጅም ጊዜ 22  የሩሢያ የባቡር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ይዞታዎችን የሚያድስ ሲሆን ከሩሢያ የምድር ባቡር ባለሥልጣን በመተባበር በሚቀጥሉት አሥር ዓመታትም 240  ባቡሮችን ያንጻል። በሣንት-ፔተርስቡርግ የዚመንስ የንግድ ተጠሪ ማቲያስ ሜርታ እንደሚሉት ለኩባንያው ትልቁ የገቢ ምንጭ ያለውም በዚሁ ዘርፍ ነው።

“የታዘዘው ምርት 410 ሚሊዮን ኤውሮ ያወጣል። ይህም 38 ባቡሮችን የሚመለከት ሲሆን የሚሰሩት ደግሞ ጀርመን ውስጥ በክሬፌልድ ይዞታችን ነው። ከሶቺው የክረምት ኦሎምፒክ በኋላ ደግሞ በዚያው በሚገኝ የጋራ ኩባንያ የተሰሩ ተጨማሪ 16 ባቡሮች ይቀርባሉ። እርግጥ ለጊዜው በንግግር ላይ በመሆናችን የውስጡና የጀርመን ድርሻ ምን ያህል እንደሚሆን ገና በተጨባጭ አይታወቅም”                                               
ዚመንስ ከሩሢያው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ከሩስ-ሃይድሮ ጋር በጋርዮሽ ቢያንስ 1,250ሜጋዋት ሃይል የሚያወጣ የነፋስ ኤነርጂ አመንጪዎችን ለማቆምም ተስማምቷል። ይሄው በስልታዊ ሽርክና ላይ የተመሠረተ ትብብር የጀርመኑን ኩባንያ በታዳሽ ኤነርጂ አመራረት ረገድ ቆርቋሪ፤ ጀማሪ የሚያደርግም ነው። መጪውን የሩሢያን የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ ካነሣን የጀርመን ኩባንያዎች ታላላቅ የዓለም የስፖርት ዝግጅቶች በሚደረጉባቸው ቦታዎቹ ሁሉ በጣም ተፈላጊ መሆናቸው ይታወቃል።

በቫንኩበርና በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ጨዋታዎችም ሆነ በደቡብ አፍሪቃው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ዝግጅቶች ሁኔታው ሌላ አልነበረም። አሁንም በመጪው የሩሢያ የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ ግንቢያ በሰፊው እየተሳተፉ ሲሆን የምድር ባቡሩ ውል ብቻ ከሁለት ሚሊያርድ ዶላር የሚበልጥ ነው። የጀርመን ኩባንያዎች ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ድቀት በኋላ መልሰው በያዙት ማገገም ብሩህ ጊዜ የሚጠብቃቸው ነው የሚመስለው። መሥፍን መኮንን  ሸዋዬ ለገሠ