የጀርመንና የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ግንኙነት | ኤኮኖሚ | DW | 07.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመንና የአፍሪቃ የምጣኔ ሃብት ግንኙነት

የጀርመን ባለሃብቶች በልዩ ልዩ ቀውሶች ና በሙስና ስሟ በሚነሳው በአፍሪቃ በአመዛኙ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ አይደፍሩም ። ይኽው ጉዳይ ከትናንት በስተያ ቦን ውስጥ በተካሄደው አፍሪቃ ውስጥ የሚሰሩ የጀርመን ባለሃብቶች የምጣኔ ሃብት ማህበር ጉባኤ ላይ ትኩረት ተስጥቶት ነበር ።

በጉባኤው ላይ የተካፈሉት የኤኮኖሚና የፖለቲካ ምሁራን ፣ የጀርመን ኩባንያዎች በማደግ ላይ ባለው የአፍሪቃ ገበያ ይበልጥ ተፈላጊ ሊሆኑ በሚችሉበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል ። ይሁንና የዶቼቬለው ፊሊፕ ዛንደር እንደዘገበው መልሱ እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም ።

በጀርመን የቶጎ አምባሳደር ኮምላ ፓካ ፣ የጀርመን ባለሃብቶች ቶጎ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ይፈልጋሉ ። ትንሽቷ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሃገር ቶጎ ባለሃብቶችን ለመሳብ በመሰረተ ልማቶች ግንባታ ረገድ የበኩሏን እየጣረች ነው ። ቶጎ የተሻሉ መንገዶች ወደቦች በእጅጉ ያስፈልጓታል ። ሃገሪቱ ከጀርመን ጋር ጥሩ ግንኙነት አላት ። አንዳንድ የጀርመን ኩባንያዎችም ቶጎ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ ። ሆኖም የእስካሁኑ የሁለቱ ሃገራት የጋራ የኤኮኖሚ ትብብር አነስተኛ ነው ። አምባሳደሩ እንደሚሉት ይህን ችግር ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ይጋሩታል ።

Comla Paka Botschafter der Republik Togo in Deutschland

ኮምላ ፓካ

« ለፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ሲፈለጉ ወይም ንግድ ማካሄድ ሲፈለጉ የአውሮፓ አጋሮቻቸው የሚያቀርቧቸው የተወሳሰቡ ቅድመ ግዴታዎች ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ያደርጓቸዋል ። ከዚያ በኋላ ቻይናንና ህንድን ወደ መሳሰሉ ሃገራት ፊታቸውን ያዞራሉ ። »

አነዚህ ሃገራት እንደ ጀርመን ኩባንያዎች ከፍተኛ ጥራት ላይ አያተኩሩም ። ቢሆንም እውነታው አምባሳደሩ እንዳሉት ነው ። አሁን አሁን አንዳንድ ነጋዴዎች በጠንካራው የጀርመን ኤኮኖሚ የአፍሪቃን ገበያ ለመያዝ የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማግኘት ይፈልጋሉ ። ቦን የተካሄደው የጀርመንና የአፍሪቃ ሃገራት የምጣኔ ሃብት ግንኙነት ማህበር ጉባኤበዚህ ላይ መክሮ ነበር ። የማህበሩ ሊቀ መንበር ሽቴፋን ሊቢንግ እንደሚሉት ከሆነ ጀርመን በአፍሪቃ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት በአውሮፓ ደረጃም ስትነፃፀር በጣም ወደ ኋላ ቀርታለች ። በርሳቸው አባባል መካከለኛ ገቢ ያለው ጀርመናዊ እጅግ ጠንቃቃ ሲሆን የመጣው ይምጣ ብሎ አፍሪቃ ውስጥ ደፍሮ የሚገባ አይደለም ።

«ብዙ ጥያቄዎች ይቀርቡልናል ። ከሁሉም የአፍሪቃን ገበያ ለማግኘት ምን ያህል ተጨማሪ የጀርመን ባለሃብቶች ማግኘት አለብን ? የሚለው አንዱ ነው ። እናም አሁን ከፖለቲካው ጋር መሥራት ካልቻልን አፍሪቃ መግቢያው ጊዜ ያልፍብናል ። »

Deutschland Stefan Liebing

ሽቴፋን ሊቢንግ

የጎሶ ግጭቶች ፣ የማያድግ የምጣኔ ሃብትና የመሳሰሉት የጀርመን ባለሃብቶች ስለ አፍሪቃ ያላቸው ምስል የጀርመኑ የኮሜርስ ባንክ ባልደረባ ፍሎርያን ቪት እንዳሉት አለአግባብ የተለጠጠ ነው ። « ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ዳግም ትንሣኤ » ሲል ባንኩ ስለ አፍሪቃ ያካሄደው ጥናት በታህሳስ ወር ለሁለተኛ ጊዜ ይቀርባል ። እንደ ጥናቱ እጎአ ከ2ሺህ አንስቶ ከእስያ ጋር ሲነፃፀር አፍሪቃ ጠንካራ የምጣኔ ሃብት እድገት አስመዝግባለች ።

እንደ አንጎላ ያሉ የነዳጅ ዘይት አምራች ሃገራት ዓመታዊ እድገታቸው ከ 11 በመቶ በልጧል ። እነዚህ ሃገራት ፣ የጥሬ እቃ ዋጋ በዓለም ገበያ አሁን እየተወደደ በመምጣቱ ተጠቃሚ ናቸው ። ሆኖም እያደገ በመሄድ ላይ ባለው የህዝቧ ቁጥር ምክንያት አፍሪቃ አዳዲስ የስራ መስኮች ያስፈልጓታል ። ማዕድን ማውጫዎች ብቻ ሳይሆን ማዕድናቱን ለሌሌች ምርቶች የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችም ያስፈልጓታል ። ይህ ደግሞ ለጀርመኖች አትራፊ የሥራ መስክ ሊሆን ይችላል ። ሽቴፋን ሊቢንግ በዚህ ረገድ ብሪክስ በመባል ከሚጠሩት ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ካሉት ከብራዚል ከሩስያ ከህንድ ከቻያናና ከደቡብ አፍሪቃ መማር ይቻላል ይላሉ ።

« ከብሪክስ መቅሰም የምንችላቸው ነገሮች አሉ ። ጥቅል መፍትሄዎችን መጠቆም መቻል ይኖርብናል ። አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ለአፍሪቃ ገበያ ባቀረብ የሚፈይደው ነገር አይኖርም ። ከዚያ ይልቅ ከአንድ መንግሥት ጋር በጋራ የኤሌክትሪክ ችግር መፍታት እንደምፈልግ ስምምነት ላይ መድረስ ይገባኛል ። »

ሊቢንግ እንደሚሉት ይህ ደግሞ ከግል ኩባንያዎች ጋር የተሻለ ትብብርን ይጠይቃል ። ከዚህ በተጨማሪም በጀርመን የፖለቲካ መርህ ውስጥም ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል ። የጀርመን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአፍሪቃ የሚያደርጓቸው ጉብኝቶች ውስን ናቸው ። የጀርመን ምጣኔ ሃብት ከአፍሪቃ እንዲጠቀም የፖለቲከኞች ትኩረትና በጉዳዩ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic