የጀርመንና የአፍሪቃ ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 08.02.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የጀርመንና የአፍሪቃ ንግድ

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዕድገት በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ጋብ ቢልና በወቅቱም በኤውሮ-ዞን ችግር ተጽዕኖ ቢደቀንበትም በዕርምጃው እንደሚቀጥል ነው የሚታመነው።

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዕድገት በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ ጋብ ቢልና በወቅቱም በኤውሮ-ዞን ችግር ተጽዕኖ ቢደቀንበትም በዕርምጃው እንደሚቀጥል ነው የሚታመነው። ይህም ከውጭው ዓለም ጋር የሚደረገውን ንግድ የሚያበረታታ መሆኑ አልቀረም። አውሮፓውያንና ሌሎች ሃገራት ለአፍሪቃ ንግድ የሚሰጡት ትኩረት እየጨመረ ነው የሄደው።                                                                                                        

የጀርመን ኩባንያዎችም ከአፍሪቃ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከርና በክፍለ-ዓለሚቱ ይበልጥ ስር ለመስደድ ይፈልጋሉ። እርግጥ ለዚህ የውጭ ንግድ ብድር ዋስትና መረጋገጡ እጅግ አስፈላጊ ነው።  አስተማማኝ ለሆነ ንግድ እንግዲህ ይህ ቅድመ-ግዴታ ይሆናል ማለት ነው። ለዚሁም የጀርመን መንግሥት ኦይለር-ሄርመስ በተሰኘው የብድር መድህን ድርጅት አማካይነት በቅርቡ ከአፍሪቃ ላኪ-አስገቢ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር የትብብር ውል እንዲፈረም አድርጓል።

የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ባለፉት ዓመታት ከሌሎች ክፍለ-ዓለማት ሲነጻጸር በተፋጠነ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ ነው የሚነገረው። የውቅቱ የኤውሮ ቀውስ ምናልባት ሊገታው የሚችል ቢሆንም ችግሩን ተቋቁሞ እንደሚያልፍ ነው የሚታመነው። ዓለም በአፍሪቃ ላይ ያለው አመለካከት እየተቀየረ ሄዷል። ዘ-ኤኮኖሚስት  የተስኘው ቀደምት ጋዜጣ ከአሥር ዓመት በፊት ስለ አፍሪቃ ሲያትት «ተሥፋ ቢስ ክፍለ-ዓለም» የሚል ርዕስን ነበር የመረጠው።

ዛሬ ይህ አመለካከት ተቀይሯል። ያው ጋዜጣ በቅርቡ ስለ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ሁኔታ ሲያትት «ጸሃይ ስትፈግ» የሚል ርዕስን ነው የመረጠው። አፍሪቃ በጥሩ ዕርምጃ ላይ መሆኗ ሌሎች በርከት ያሉ ጠበብትም የሚጋሩት አስተያየት ሆኗል።  የዓለም ባንክ ለዚህ ለያዝነው 2012 ዓመት-ምሕረት የ 5,3 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት ነው የሚተነብየው።                         

 «አፍሪካን-ቢዝነስ» የተሰኘው የኤኮኖሚ ጋዜጣ አዘጋጅ አንቨር ቫዚም የዓለምአቀፉን ምንዛሪ ተቋም የአይ-ኤም-ኤፍን መረጃ በመጥቀስ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዕድገት የሚያደርጉት ሰባት ሃገራት አፍሪቃ ውስጥ እንደሚገኙ ያመለክታሉ። የአፍሪቃ የልማት ባንክ ባለሙያዎችም ክፍለ-ዓለሚቱ በዚህ ዓመት ከ 5 በመቶ በላይ ዕድገት እንደምታደርግ ነው የሚተነብዩት።                                                                    

ሆኖም የልማት ባንኩ የምርምር ዘርፍ ሃላፊ ዴዚሬ ቬንካታቼሉም እንደሚሉት በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በኦኢሲዲ ሃግራት ውስጥ ሁኔታው የተለየ አቅጣጫ ይዞ ከተራመደ ይሄው በአፍሪቃ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ጠበብት እዚህ ላይ በተለይም 2009-ን መለስ ብለው ያስታውሳሉ።                                                                            

ያኔ የዓለም ባንክ ለአፍሪቃ 5,1 ከመቶ ዕድገት ነበር የተነበየው። ሆኖም የዓለም ኤኮኖሚ የፊናንሱን ቀውስ ተከትሎ ብርቱ ችግር ላይ ሲወድቅ የአፍሪቃም ዕድገት ማቆልቆሉ አይዘነጋም። ዕድገቱ በ 2 ከመቶ ገደማ ነበር የተወሰነው። ለማንኛውም ክዚያን ወዲህ ሁኔታው መልሶ እየተሻሻለ ሲመጣ ጀርመንን የመሳሰሉት የበለጽጉ ሃገራትም የንግድ ትብብራቸውን ጥልቅ ለማድረግ ይበልጥ ሲጥሩ ነው የሚታየው።

Afghanistan Land und Leute Auto mit Baumwolle

በዚህ በኩል ቻይና በአፍሪቃ ስር ከሰደደች ቆየት ብላለች። የሩቅ ምሥራቋ ግዙፍ አገር ዛሬ ታላቋ የክፍለ-ዓለሚቱ የንግድ ሸሪክ ናት። ይሁን እንጂ የጀርመን ኩባንያዎችም ታላቅ የወደፊት የኤኮኖሚ ዕድገት በሚጠበቅባት ክፍለ-ዓለም ገበያቸውን ይበልጥ ለማስፋት እየጣሩ ነው። በጀርመን ፌደራል የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት አፍሪቃ ባለፉት አሥር ዓመታት ክ 60ኛዎቹ ወዲህ ረጅም የሆነወን የዕድገት ጊዜ ነው ያሳለፈችው።

ይህም በጥሬ ሃብት በታደሉት ሃገራት ብቻ አልነበረም። በጀርመኑ የሮላንድ በርገር የኩባንያዎች አማካሪ ድርጅት የቀረበ አንድ የጥናት ውጤት የሚያመለክተው አፍሪቃ ውስጥ ከሣሃራ በስተደቡብ ያለውን አካባቢ ጨምሮ ብዙ የዕድገት ዕድል እንዳለ ነው። ይሁን እንጂ የውጭ ንግድና የፊናንስ አዋቂ የሆኑት የ Price Waterhouse Coopers(PwC)የምጣኔ-ሐብት ምርምር ተቋም ባልደረባ አንድሬያስ ክላዘን እንደሚሉት ከአፍሪቃ ጋር መነገድ ከባድና  አደጋም የተዋሃደው ነው።   

«አፍሪቃ ታዳጊ ክፍለ-ዓለም እንደመሆኗ መጠን እርግጥ አደጋው አብዛኛውን ጊዜ ይበልጥ ከፍ ያለ ነው። ለጀርመን ኩባንያዎችና ባንኮችም ሁኔታው ቀላል አይደለም። በሌላ በኩል ምርት ለሚያቀርቡ የጀርመን ኩባንያዎች አፍሪቃ ውስጥ ትልቅ ዕድል መኖሩም ሊታወቅ ይገባል። በተለይ በመዋቅራዊ ግንባታ፣ በኤነርጂ ዘርፍ ወዘተ! ይህ ባለፉት ዓመታት ለምሳሌ በአልጄሪያ በተተከለ የጸሃይ ሃያል ማከማቻ ወይም የውሃ አቅርቦት በአንጎላ የታየ ነገር ነው። እነዚህ ደግሞ በጀርመን የውጭ ንግድ ብድር ዋስትና ከሚደገፉት ፕሮዤዎች ዋነኞቹ ናቸው»

የጀርመን መንግሥት ከምጣኔ-ሐብቱ ምርምር ተቋምና ከኦይለር ሄርመስ  ጋር በመሆን የውጭ ንግድ ብድሩን ዋስትና ሲያዘጋጅ ባለፈው ታሕሣስ ወርም የአገሪቱ ኩባንያዎች በአሕጽሮት አፍሬክሢም በመባል ከሚታወቀው ከአፍሪቃ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር የትብብር ውል መፈራረማቸው ይታወሣል። የሄርመስ ዋስትና ወይም ጋራንቲ የጀርመን መንግሥት ክ 1949 ወዲህ ሲገለገልበት የቆየው ዋነኛ የውጭ ንግድ ማራመጃ መሣሪያ እንደሆነ ይታወቃል።  ዋስትናው የጀርመን ኩባንያዎች የገንዘብ ክፍያን እንዳያጡ የሚጠብቅ ነው።

ዛሬ ከሣሃራ በስተደቡብ ከሚገኙት በርካታ ሃገራት መካከል አንዳንዶቹ በተፋጠነ ዕድገት ላይ መሆናቸውን ነው አንድሬያስ ክላዘን የሚናገሩት። ከነዚሁ መካከልም ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ጋናና ናይጄሪያ ይጠቀሳሉ። ታዲያ ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኙት 48 ሃገራት ውስጥ 750 ሚሊዮን ሕዝብ ሲኖር ሆኖም አካባቢው በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያለው ድርሻ ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው። በአፍሪቃ የጀርመን አጠቃላይ ንግድ ከ 2006 ወዲህ በሰባት ከመቶ ሲጨምር  በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ  ወዳለው አካባቢ የሚደረገው የውጭ ንግድም ከእጥፍ በላይ አድጓል።

«እንበል በ 16 ከመቶ ገደማ!በግልጽ ነው ከፍ ያለው። ግን ክሚቻለው በታች መሆናችንም ሊታወቅ ይገባል። ምክንያቱም ከጠቅላላው ዓለም ወደ አፍሪቃ የሚገባው ምርት በ 31 ከመቶ ገደማ ነው የጨመረው። ይህ ደግሞ የነዚህ ሃገራት አቅም ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው»

ጀርመን ባለፈው ዓመት ከሣሃራ በስተደቡብ ወዳለው አካባቢ ባደረገችው የውጭ ንግድ ከአንድ ሚሊያርድ ኤውሮ የሚበልጥ ገንዝብ ለማስገባት ችላለች።

«ትልቁ ግባችን ከአፍሪቃ ጋር የሚደረገውን ንግድ ሁኔታ ቀላል ማድረግ ይሆናል። ይህ ከአፍሬክሢም ባንክ ጋር የሚደረገውን ውልም የሚጠቀልል ነው። ሌላ ከ African Trade Insurance Agency የአፍሪቃ የንግድ ዋስትና ድርጅት ጋር የሚደረግ ስምምነትንም ይመለከታል። ከዚሁ ድርጅት ጋርም በቅርቡ ናይሮቢ ውስጥ ውል ተፈራርመናል። በውጭ ንግድ ላይ ለተሰማሩ የጀርመን ኩባንያዎች ደግሞ ይሄው ተጨማሪ የአካባቢ መረጃ እጅግ ጠቃሚ ነው»

ካይሮ ላይ ተቀማጭ የሆነው የአፍሪቃ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ በ 1993 በአፍሪቃ መንግሥታት፣ እንዲሁም በግልና ድርጅታዊ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ሲቋቋም የሚያተኩረውም የአፍሪቃን ንግድ በማራመዱ ላይ ነው። የአፍሪቃ የንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ የተመሰረተው ደግሞ በ 2001 ነበር።

በአጠቃላይ የውጭ ባለሃብቶች ትኩረት በአፍሪቃ እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው። ለዚሁም ዋናው ምክንያት የአፍሪቃ የወደፊት  ዕድገት ተሥፋ ሰጭነት መሆኑ ይነገራል። ፍላጎቱ እየጨመረ መሄዱ ሌላ መንስዔም ሳይኖረው አልቀረም። የጀርመን ምጣኔ-ሐብት የአፍሪቃ ማሕበር ባልደረባ ሚሻኤል ሞነርያህን እንደሚሉት ብዙ ኩባንያዎች የእሢያ ገበዮች በፍጥነት የሚያድጉበት ጊዜ ማለፉን እየተረዱ ነው። የፉክክሩንም መጠንከር እንዲሁ!

እናም አፍሪቃ ውስጥ አዲስ ገበዮችን ለመክፈት ተሥፋ ያደርጋሉ። ኤኮኖሚስት ጋዜጣ እንደሚለው መጠይቅ ከተደረገላቸው የመዋእለ-ነዋይ ባለቤቶች ግማሹ አፍሪቃ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ለዓለም ባለሃብቶች ማራኪዋ ቦታ እንደምትሆን ነው የሚያምኑት። ሲሶውም በሚቀጥሉት ዓመታት 5 በመቶ ገንዘባቸውን በዚያው በአፍሪቃ በስራ ለማዋል ይሻሉ።

እርግጥ በተለይም በጥሬ ሃብት ላይ ጥገኛ የሆነችው የአፍሪቃ ዕርምጃ በአውሮፓ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይም ጥገኛ ነው። ከዚህ አንጻር የወቅቱ የኤውሮ ቀውስ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ምን ያህል እንደሚሆን አይታወቅም። ጠበብት አደጋውን ለመቋቋም የሚመክሩት የአፍሪቃን የውስጥ ንግድ ማዳበሩ እንደሚበጅ ነው።

መሥፍን መኮንን   

ነጋሽ መሐመድ               

                 

Audios and videos on the topic

 • ቀን 08.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13yi4
 • ቀን 08.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13yi4