የጀርመንና የአርጀንቲና የወዳጅነት ግጥሚያ | ስፖርት | DW | 03.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የጀርመንና የአርጀንቲና የወዳጅነት ግጥሚያ

በብራዚል ፣ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከተደመደመ 2 ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ናቸው የቀሩት። ሪዮ ዴ ጃኔሮ ውስጥ በዝነኛው ማራካና ስታዲየም ፤ በፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመን ፣ አርጀንቲናን 1-0 አሸንፋ ለ 4ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ባለቤት መሆኗ

የታወቀ ነው። ዛሬ ማታ ፤ ጀርመንና አርጀንቲና፤ በዱሰልዶርፍ ከተማ የወዳጅነት የሚሰኘውን ግጥሚያ ያካሂዳሉ ። የወዳጅነት ይባል እንጂ፣ አቅም መፈተሻ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። በ 2 ወራት ገደማ ምን ዓይነት ለውጥ አለ?

ሐምሌ 6 ቀን 2006 ዓ ም ፤ ጀርመን፣ ከአትላንቲክ ማዶ በተዘጋጀ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የዓለምን ዋንጫ ለማግኘት ፣ የመጀመሪያቱ አውሮፓዊት ሀገር ናት። በብራዚል ፣ ጀርመን ከግብ ጠባቂ አንስቶ እስከ ተከላከይ ፤ መሃል ሜዳ አካፋፋይና የፊት አጥቂዎች ድረስ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ይዛ መቅረቧ አይዘነጋም። ተስፋ ያላቸው አዳዲስ ተጫዋቾች ባታጣም፤ የቀድሞዎቹ ጎበዝ ተጫዋቾች በተለይ ሚሮስላቭ ክሎዘና የቡድኑ አምበል የነበረው ፊሊፕ ላም መሰናበታቸው ትንሽ ግር የሚል ሁኔታ ይፈጥር ይሆን? ፔር ሜርተሳከር እንዲሁ ተሰናብቷል። ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር አዲሱ የብሔራዊው ቡድን አምበል ሆኗል። የ 22 ዓመቱ ወጣት ኤሪካ ዱርምና የ 20 ዓመቱ ወጣት ማትያስ ጊንተር ፤ እንዲሁም በብራዚል የመጫወት ዕድል የተነፈገው ማሪዮ ጎሜዝ ይሰለፋሉ ። ማሪዮ ጎሜዝ ወደፊትም በአጥቂነት የመሰለፍ ዕድሉ የጎላ ነው። ከአርጀንቲና በኩል ፤ ታዋቂው ኮክብ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ አይሰለፍም። ታፋው ላይ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ሳይሰለፍ የቀረው ሌላው ጎበዝ ተጫዋች አሁን ከሪያል ማድሪድ ወደ እንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ በ 75 ሚሊዮን ዩውሮ የተሸጠው አንኼል ዲ ማሪያ ዛሬ ይሰለፋል።

ጀርመን ከአርጀንቲና ጋር ዛሬ የምትጋጠመው ረዘም ላለ ጊዜ በቀጠሮ ተይዞ የቆየ እቅድ በመሆኑ ነው። የብሔራዊው ቡድን አልጣኝ ዮአኺም ሎዖቭ ፣ የዛሬው ግጥሚያ የበቀል ሳይሆን፤ እ ጎ አ በ 2016 ዓ ም ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ ለሚካሄደው የአውሮፓ ሃገራት የእግር ኳስ ዋንጫ ወድድር፤ ማጣሪያውን ለማለፍ ለሚደረገው ዝግጅት ጀርመንን እንደሚረዳት ነው የጠቆመው። ጀርመን የፊታችን እሁድ ከእስኮትላንድ ጋር ዶርትሙንድ ውስጥ የማጣሪያ ግጥሚያ ታካሂዳለች። የጀርመን የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮአኺም ሎዖቭ----

«ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአርጀንቲና በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ተገናኝተን ነበር። ይህ እንደሚሆን፣ የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሽን አስቀድሞ መተንበይ የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም። ይሁንና ረዘም ላለ ጊዜ ቀነ ቀጠሮ በተያዘለት በዚህ ጨዋታ ከጠንካራ ቡድን ጋር መጋጠማችን ከስኮትላንድ ጋር ለምናደርገው ውድድር ይረዳናል።

እንደሚመስለኝ፤ ባለፈው ሞቃት ወቅት የተከናወነውን የዓለም ዋንጫ ውድድር ስሜት ለተመልካቹ እንደገና በማሳየት ሳናረካ አንቀርም። እናም ዛሬ ረቡዕ ከአርጀንቲና ጋር የምrd,ርገውን ግጥሚያ በጉጉት ነው የምንጠባበቀው።»

ግጥሚያው የሚካሄደው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ለ 4 ሰዓት ሩብ ጉዳይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀርመን የአውሮፓ ሃገራትን የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር እ ጎ አ በ 2024 የማዘጋጀት ማለፊያ ዕድል እንዳላት የፌደሬሽኑ ዋና ጸሐፊ ሄልሙት ዛንድሮክ አስታውቀዋል።ይህም የሆነው ከኢንግላንድ ጋር ማመልከቻ በማስገባት ረገድ የማሸጋሸግ ስምምነት በማድረግ ነው ተብሏል።ጀርመን የአውሮፓ ሃገራትን የዋንጫ ውድድር እ ጎ አ በ 1988 ፤ የዓለምን የአግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ደግሞ እ ጎ አ በ 1974 እና በ 2006 ማዘጋጀቷ የሚታወስ ነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic