የጀርመንና የቡሩንዲ የልማት ትብብር መቋረጥ | አፍሪቃ | DW | 16.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የጀርመንና የቡሩንዲ የልማት ትብብር መቋረጥ

ጀርመን ከቡሩንዲ ጋር የምታደርገውን የልማት ትብብር አቋረጠች። በፌደራል ጀርመን መንግሥት የኤኮኖሚ የልማት ትብብር ሚንስትር ዴታ ቶማስ ዚልበርሆርን እንደገለፁት፣ በአሁኑ ወቅት በቡሩንዲ ላይ ከብዙ አቅጣጫዎች የተጣለዉ ጫና አስፈላጊ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:17
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:17 ደቂቃ

ጀርመን ከቡሩንዲ ጋር የልማት ትብብሯን ማቋረጧ

ዚልበርሆርን ይህን የተናገሩት በቡሩንዲ የተከሰተዉን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተከትሎ በሃገሪቱ የሚታየዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፕሬስ ነፃነት መታፈንን ተከትሎ ነዉ።

የጀርመን ፊደራል መንግሥት በቅርበት ሲሰራ ከነበረዉ ከቡሩንዲ ጋር ያለዉን የልማት የትብብር ሥራ ማቋረጡ ተገልጾአል። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የቡሩንዲዉን መንግሥት በፕሬስ ላይ የሚያደርገዉን አፈናና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ እያደረሰ ያለዉን ጥቃት እንዲገታ ከአንድ ወር በፊት አስጠንቅቀዉ ነበር። ጀርመን በቡሩንዲ መንግሥት ላይ ይህን ርምጃ ከመዉሰድዋ በፊት በቡሩንዲዉ ፕሬዚዳንት ፔር ንኩሩንዚዛ ላይ ከበስተጀርባ ጫና ለመፍጠር አልተሞከረም ነበር ይሆን ? ለሚለዉ ጥያቄ ፤ በጀርመን የኤኮኖሚ የልማት ትብብር ሚንስትር ዴታ ቶማስ ዚልበርሆርን የቡሩንዲ መንግሥት

Thomas Silberhorn

በጀርመን የኤኮኖሚ የልማት ትብብር ሚንስትር ዴታ ቶማስ ዚልበርሆርን

በሃገሪቱ ዉስጥ እየፈፀመ ያለዉን ከፍተኛ በደል ባለመግታቱ፤ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ርምጃ መውሰድ እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

« ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ነዉ የምንወስነዉ። በቡሩንዲ ከተከሰተው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የመንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና፤ የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ የደገፉ ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል። በዚህ ወቅት የቆሰሉና በሕክምና ላይ የነበሩ ወታደሮችም ሆስፒታል ዉስጥ በጥይት ተገድለዋል። በብሩንዲ እጅግ አስከፊ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቀጠሉ፣ ምንም ነገር እንዳልሆነ አሁን ከዚችዉ ሃገር ጋር ግንኙነታችንን ልንቀጥል እንደማንችል ለማሳየት ግልጽ ፖለቲካዊ ምልክት ማስተላለፍ ግድ ነበር የሆነብን። »

በቡሩንዲ ይህ አይነቱ የሰብዓዊ ጭፍጨፋ መፈፀሙን በማረጋገጡ ረገድ በመገናኛ መረብ የተሰራጩ የተለያዩ መረጃዎች ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ዚልበርሆርን ገልጸዋል።

« መረጃ የምናገኘዉ ከተለያዩ ምንጮች ነዉ። በተለያዩ ቦታዎች የሚዘዋወሩ በርካታ ምሁራ አሉን። ጋዜጦችን እናነባለን። በተጨማሪ የቡሩንዲ ጋዜጠኞች ጠንካራ ትችት ያዘለ ዘገባ ከሚያሰራጩበት የመገናኛ ብዙኃን መረብም መረጃ እናገኛለን። እንደሚታወቀዉ እነዚህ መሰሎቹን መረጃዎች በቡሩንዲ መገናኛ ብዙኃን ማቅረብ የተከለከለ ነዉ።»

Tansania Flüchtlinge aus Burundi

የቡሩንዲ ስደተኞች በታንዛንያ

ከቡሩንዲ ጋር ለሚደረገዉ የልማት ትብብር ሥራ በጎርጎረሳዉያኑ 2014 ዓ,ም እና በ2015 ዓ,ም የጀርመን ፊደራል ሬፐብሊክ 52,5 ሚሊዮን ዩሮ በጀት መመደቡ ይታወቃል። ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን ለመወዳደር በዕጩነት ለመቅረብ መፈለጋቸዉን ትክክለኛ የሚሉት የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ መንግሥታቸዉ ከጀርመን ስለተጣለበት ወቀሳም ሆነ፣ ስለተቋረጠዉ የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ጉዳይ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት መቆጠቡን ነው ጀርመናዊው የኤኮኖሚ የልማት ትብብር ሚንስትር ዴታ ቶማስ ዚልበርሆርንያመለከቱት።


« እስካሁን ምንም አይነት መልስ አልተሰጠም። ይሁንና ከቡሩንዲ መንግሥት አኳያ ለጋሾች ያም ሆነ ይህ በቀጣይ ገንዘብ መክፈላቸዉን ይቀጥላሉ የሚል አስተሳሰብ እብዳለ እናዉቃለን። እኛ በበኩላችን የቡሩንዲ መንግሥት ያለበትን ግዴታ መወጣት እንዳለበት በግልፅ ነዉ ማሳየት የምንፈልገዉ። እንደሚታወሰዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ,ም ለጋሾች በደረሱት ስምምነት መሰረት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ አለባቸዉ። እና ይህ ስምነት አሁን በጉልህ ተጥሶአል።»

በቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛን በመቃወም የጀመረዉ የአደባባይ ተቃዉሞ ስድስት ሳምንታት አልፎታል። የመንግሥት ወታደሮች በአገሪቱ ዉስጥ ከፍተኛ ጥበቃን በማድረግ ላይ ናቸዉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሃገሪቱን ለቀዉ ተሰደዋል፤ በሃገሪቱ የፕሪስ ነጻነት ተደፍጥጦአል። እንድያም ሆኖ ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ እንደሚካሄድ እየተነገረ ነዉ። እንደ ቶማስ ዚልበርሆርን በቡሩንዲዉ መንግሥት ላይ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል።

Burundi Proteste gegen Präsident Nkurunziza Demonstration

ፕሬዚዳንት ፔር ንኩሩንዚዛ ላይ የቀጠለዉ ተቃዉሞ

« ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብዙ ፖለቲካዊ ጫና መደረግ ይኖርበታል። ጀርመን፤ የአዉሮጳዉ ሕብረትና የአፍሪቃ ሕብረት፤ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪቃ ማኅበር ሁሉ በብሩንዲ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄድ ዘንድ የሰብዓዊ መብት እንዲሻሻል ጫና ማሳደር ይኖርባቸዋል። በአሁን ጊዜ ግን ይህ ገሃድ መሆኑ አጠራጣሪ ነዉ።»

ባለፉት ጊዝያት በአፍሪቃ ዉስጥ በተደረገ ምርጫ ስኬታማ በሆነ ሁኔታ መንግሥታት የተቀየሩባቸዉ ሃገሮች ናሚቢያና ናይጀርያ መሆናቸዉን ቶማስ ሲልበርሆን ሳይጠቅሱ አላለፉም። በእነዚህ ሃገራት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መካሄድ የቻለዉ የተመረጠዉ ፕሬዚዳንት እና ተቀናቃኝ ዕጩ ተመራጮች ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ ወስነዉ ለምርጫዉ በመዘጋጀታቸዉ ነዉ። ይህ ደግሞ ይላሉ የጀርመኑ የኤኮኖሚ የልማት ትብብር ሚንስትር ዴታ ቶማስ ዚልበርሆርን፤ ሌሎች አፍሪቃ መንግሥታት በምሳሌነት የሚቀርብ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነዉ።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic