የጀርመንና የሩሲያ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ትብብር፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 09.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የጀርመንና የሩሲያ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ትብብር፣

በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ እጅግ የገሠገሡ አገሮችም ሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለታዳጊ አገሮች ተማሪዎች ሊያበረክቱ የሚችሉት ድርሻም ሆነ ጠቀሜታ የሚያጠያይቅ አይደለም።

default

ዩሊያ የተባለችው ከሩሲያ የመጣችው የወሩ ምርጥ ተማሪ፣

በሳይንስና ሥነ-ቴክኒክረገድ የልውውጥ መርኀ-ግብር በመዘርጋትና በመተባበር፣ ራሳቸው የደረጁት አገሮችም ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ ይታመንበታል። በመሆኑም ፣ ጀርመንና ሩሲያ፣ ለአንዲህ ዓይነቱ ትብብር ትልቅ ትርጉም ነው የሰጡት።

ጤናይስጥልኝ እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ፣ ጀርመንና ሩሲያ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያደርጉትን ትብብር እንዳስሳለን።

2011 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት የጀርመንና የሩሲያ የሳይንስ የትብብር ዓመት ይሆን ዘንድ በሁለቱም አገሮች ዘንድ ስምምነት አለ። በመሆኑም በትምህርትና ምርምር ረገድ የልውውጥ መርኀ ግብር ተዘርግቷል። በትርዒት አዳራሾች፣ በታላላቅ ጉባዔዎች፣ በተለያዩ ስብሰባዎች፣ የሩሲያና የጀርመን ሳይንቲስቶች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች እርስ-በርስ በሚገባ ለመተዋወቅና በኅብረት የጋራ የምርምርና የኢንዱስትሪ ተቋማትን ለመንደፍም እቅዱ አላቸው። ላቅ ያለ ትኩረት ከሚደረግባቸው መካከል በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ እንዲሁም የተፈጥሮ አካባቢን መንከባከብ የሚያስችሉ የሥነ-ቴክኒክ ዓይነቶች ናቸው።

የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስቴር ፣ በግብፅ ፣ በእሥራኤል፤ በቻይናና በብራዚል የተሣካ ውጤት ያስገኙ «ፕሮጀክቶች»ን ካቋቋመ በኋላ በያዝነው 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ከሩሲያ ጋር ትብብር ይበልጥ በማጠናከር ፤ በሥነ-ቴክኒክ ረገድ አናዳንድ መርኀ-ግብሮችን ፍጻሜ ለማድረስ መጣር ብቻ ሳይሆን በአካዳሚው መስክም ወጣቶችን ይበልጥ ለማነቃቃት ተነሳስቷል። እዚህ ላይ ትኩረቱ በዩኒቨርስቲዎች ትብብር ላይ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውና ኤኮኖሚው መስክም የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ግሥጋሤ አስተዋጽዖ እንዲኖረው ይፈለጋል። ቶማስ ፕራል---

«እርግጥ ነው ሁለቱም ወገኖች ይበልጥ ትብብራቸውን የሚያጠናክሩት ላቅ ባለ ደረጃ በሚገኙባቸው መስኮች ነው። እዚህ ላይ ፣ ትምህርትና ሥልጠና ብቻ አይደሉም የሚታሰቡት። የፖለቲካው መስክም አለበት። የሳይንስ ምርምር የሚሠምረው አመቺ ሁኔታዎች ሲፈጠሩለት መሆኑ የታወቀ ነው።»

ቶማስ ፓራል፣ በጀርመን የልውውጥ አገልግሎት(DAAD) የሩሲኛውን ክፍል የሚመሩ ናቸው። እርሳቸውም፣ በሩሲያ እንዲሁም በጀርመን ሀገር ለግማሽ ዓመት የቀለም ትምህርትን እዚህም ላይ ጀርመንና ሩሲኛን የሚከታተሉ ተማሪዎችን የሚያማክሩ ናቸው።

የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስቴር በነደፈው 2011 የጀርመንና የሩሲያ የሳይንስ የትብብር ዘመን ያለፈውን መርኀ-ግብር ወደፊትም ለመደገፍ አቅዷል።

በያመቱ 12,000 ያህል ሩሲያውያን ተማሪዎች ናቸው ወደ ጀርመን እየመጡ ትምህርታቸውን በዩኒቨርስቲው የሚከታተሉት። በአካዳሚው ልውውጥ ወደ ጀርመን ብቅ ካሉት ሩሲያውያን ተማሪዎች መካከል ከዮሽካር ኦላ የመጣችው አና ኮፕቲና ትገኝበታለች። እርሷም ቦን ውስጥ ከስነ-ህይወት ጋር በተያያዘ ሥነ ቴክኒክ ነው ምርምር የምታካሂደው።

«በምርምርና ኢንዱስትሪ መካከል የሠመረ ግንኙነት በመኖሩ በጣም ጥሩ ሆኖ ነው ያገኘሁት። በምርምር የተገኙ ውጤቶች ሁሉ ፣ ከሞላ ጎደል፣ በቀጥት ነው ለኢንዱስትሪው የሚቀርቡት። በሩሲያ ከዚህ ይለያል። አንድ ሰው ፣ የምርምር ውጤቱን፤ በሥራ ፤ በተግባር ላይ እስኪያይ ድረስ ረጅም ጊዜ ነው የሚወስድበት።»

በጀርመንና በሩሲያ መካከል በትምህርትና በሳይንስ የሚደረገው የልምድ ልውውጥ፣ በሁለቱም በኩል ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ አንዱ ቅድመ ግዴታ ሳይሆን አልቀረም። የጀርመን የትምህርትና የምርምር ሚንስቴር፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች፣ አዳዲስ ሐሳቦችን በማፍለቅና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ረገድ እንዲወዳደሩ ያደፋፍራል። አዲስ ሐሳብ በማፍለቅ ፣ ይጠቅማሉ ተብለው ለሚቀርቡ እቅዶች፣ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፣ ጀርመናውያኑና ሩሲያውያኑ የሳይንስ ተመራማሪዎች በአንዲህ ዓይነት አቅድ በቀጥታ ሊገናኙ ይችላሉ። ዖልጋ ሞሮሶቫም፣ በዚሁ፣ የጋራ የሳይንስ ምርምር መታሰቢያ ዓመት በትጋት በመሥራት ልታሳልፈው ታጥቃ ሳትነሣ አልቀረችም። ዖልጋ የምትሠራው ሞስኮ ውስጥ፤ የመንግሥት በሆነው በማስተማር ዘዴዎች ላይ ባተኮረው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ነው። ጀርመን ውስጥ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችን የጎበች ስትሆን፤ በዚያም ጠቃሚ ሆኖ ያገኘችውን ሞስኮ ውስጥ በቀጥታ እንደምትጠቀምበት ነው የጠቆመች።

«አንድ አውሮፓዊ ወይም ጀርመናዊ ወደ እኛ ሲመጣ፣ የሩሲያን ተመክሮ ብቻ አይደለም የምናስረዳው፤ እኛም ለምሳሌ ያህል በጀርመን አገር እንዴት እንደሚሠራ እንገነዘባለን። ይህ ደግሞ ለእኛ የአሠራር ሥርዓት በጣም አመርቂና የሚያጓጓም ነው። »

አንዱ ትልቁ ችግር ወይም ደንቃራ የቋንቋ ልዩነት ነው። በሩሲያ አብዛኛው ትምህርት የሚሰጠው፣ በሩሲኛ ቋንቋ ነው። ለስለሆነም በሩሲያ ዩኒቨርስቲዎች ፤ በአካዳሚ የልውውጥ አቅድ፣ ለግማሽ ዓመት ትምህርታቸውን መከታታል የሚሹት ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ፣ በዚህ በተቀየሰው የጋራ የሳይንስና ምርምር መታሰቢያ ዘመን፤ የታቀዱ የምርምር ፕሮጀክቶች፣ ወጣት የሳይንስ ተመራማሪዎችን ያማልሉ ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቁ ማድረግ የግድ ይላል። እዚህ ላይ፣ የአካዳሚውን የልውውጥ አቅድ ይበልጥ ለማሣካት፣ ትምህርቱ በእንግሊዝኛም እንዲሰጥ ማድረግ ዐቢይ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ሆኗል። አና ኮፕቲና ግን ከመጀመሪያውም ትምህርቷን በጀርመን ሀገር ለመከታተል ችግር አላገጠማትም።

«የቋንቋውን መሠረት ትንሽ ለማወቅ የሞከረ ሰው እኔ እንዳደረግኹት በቀጥታ ወደ ጀርመን መምጣት ይችላል። ጀርመንኛም ምንም አላውቅም ነበረ፤ ይሁንና በጀርመን የአካዳሚ ልውውጥ መርኀ-ግብር የ 2 ወራት የቋንቋ ትምህርት ከተከታተልኹ በኋላ ፣

ዕለት-ተዕለት በዚሁ ቋንቋ መግባባት ቻልሁ። ሩሲያ ውስጥ በእንግሊዝኛ ትምህርት የሚሰጥባቸው ቦታዎች በጣም ጥቂቶች ሲሆኑ፣ እነርሱም የሚገኙት በታላላቅ ከተሞች ብቻ ነው። ብዙዎች የውጭ ሀገር ተማሪዎች ወደሩሲያ እንዳይመጡ ደንቃራ የሆነውም ይኸው የቋንቋ ችግር ነው። »

በቦሎኛ የትምህርት ተሃድሶ ለውጥ ውል መሠረት ፣ በጀርመን ሀገር በአንግሊዝኛ ትምህርት የሚሰጥባቸው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥር የጨመረ ሲሆን፤ ወደ ጀርመን በመምጣት ከፍተኛ ትምህርት ለመቅሰም የሚሹ የውጭ ተማሪዎችን የሚያማልል ሆኗል። አና ፤ በሥነ-ህይወት ሥነ- ቴክኒክ ረገድ ነው፣ ምርምር የምታካሂደው። የሚያማክሯት ፕሮፌሰር Gudrun Ulrich-Merzenich የአናን ተሰጥዖ ያደንቃሉ። የጀርመንና የሩሲያ ትብብር እንዲሁ በነባቤ-ቃል ብቻ ሳይሆን በቤተ-ሙከራም የሠመረ ውጤት እንደሚያስገኝ በማሥመስከር ላይ ነው። ፕሮፌሰር ጉድሩን ዑልሪኽ ሜርትዘኒኽ-

«የምርምር ተግባርን ማከናወን የሚጠበቅ ነው። እርሷ ( አና ) እዚህ የመጣችው ልዩ የሆነ ሥነ ቴክኒክ ለመቅሰም በመሻቷ ነው። ያን ሩሲያ ውስጥ ማከናወን አልቻለችም ነበር። እኔም በአንዳንድ ቴክኒካዊ የአሠራር ዘዴዎች በጣም ጥሩ ተመክሮ ካላት ከአና የምቀስመው አለ። በሥነ ህይወት ምርምር ረገድ፣ ሩሲያውያን ከእኛ ከጀርመናውያን ብዙ የሚማሩት አለ። በሥነ ቴክኒክና ኢንጂኔሪንግ ደግሞ እኛ ከሩሲያውያን የምንማረው ብዙ ነገር አለ።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ