የጀርመናዉያን የገና በአል አከባበር ወግ | ባህል | DW | 23.12.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የጀርመናዉያን የገና በአል አከባበር ወግ

ጀርመናዉያን የገናን በአል እጅግ የሚወዱት እና ከቤተሰብ ጋር የሚያከብሩት በአላቸዉ ነዉ። የገና በአል ሲዳረስ በተለይ የቸገረን የታመመዉን የመርዳት ባህላቸዉ ጠንከር ያለ ነዉ።

default

ዘንድሮ ለገና በአል ዝግጅት የተደረገዉ የገበያ ልዉዉጥ ከመንግዜዉም በላይ እንደሆነ የአገሪቷ የሽያጭ ክፍልና የኤኮኖሚ ባለሞያዎች ከወዲሁ በመግለጽ ላይ ናቸዉ። የአየሩም ሁኔታ ክረምት ወራት ከጀመረበት ቀን አንስቶ በረዶዉ ብን ብን እያለ ጭራሮ መስሎ የቆመዉን ዛፎፍ ሸፍኖ በየቤቱ ጣርያ ላይ እና ግንብ ላይ በረዶዉ ተከምሮ ድፍን ጀርመን የተፈጨ ጨዉ የተሸፈነች አስመስሎታል። ነገ የሚከበረዉን የገና በአል ከመድረሱ አራት ሳምንት በፊት የሚዘረጋዉም የገና ገበያ በጀርመናዉያኑ ስያሜ ቫይናትስ ማርክት የአገሪዉን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ አለም አገራት የሚመጡትን ቱሪስቶች በቀረፋ እና በሌሎች ቅመማ ቅመሞች የተፈለዉን ቀይ የወይን ጠጅ እያቀረበ በባህላዊ የምግብ መዓዛ እየሳበ ነዉ።
ወጣት አማኑኤል አማረ በጀርመን አገር መኖር ከጀመረ አምስት ዓመት ሊሞላዉ ጥቂት ወራቶች ቀርተዉታል። ትምህርቱን በኮንፒዉተር ኢንጂኔሪንግ አጠናቆ በግዙፉ የኤሌክትሮኒክስ እና ሶፍትዌር አምራች ድርጅት ኖኪያ ዉስጥ ተቀጥሮ በማገልገል ላይ ነዉ። የጀርመናዉያኑን የገና በአልን እንዴት ለማክበር ተዘጋጅተሃል ብለን ለመጠየቅ ስንደዉልለት ወደ አገር ቤት ለመሄድ ሻንጣዉን ሲሸክፍ ነበር ያገኘነዉ። ሌላዋ ኢትዮጽያዊት የበርሊን ከተማ ነዋሪ አቲዪ ተሊላ የኢትዮጽያዊ ባህልን የምታስተዋዉቅበት ባህላዊ ምግብን የምታቀርብበት የአነስተኛ ቡና ቤት ባለቤት ናት። ጀርመናዉያኑ የገናን በአል ሲያከብሩ የኢትዮጽያ ባህላዊ ምግብን አዘጋጅታ ለማክበር በዝግጅት ላይ ትገኛለች።
ዘንድሮ በጀርመን የወረደዉን በረዶ ተከትሎ እንደ ዘንድሮ አይነት ክረምት እና ብርድ ከአስርተ አመታት በፊት እንደ ነበር ተገልጸዋል። ይኸዉ የገና በአል ሊዳረስ ሲል በየመንገድ ዳርዳር ባሉ ህንጻዎች ወይም በመንገድ ዳር ላይ በተተከሉ ዛሮች ላይ የሚያብለጨልጩ ነገሮችን ሰቅለዉ እና የተለያዩ ቀለማትን የሚሰጡ ብልጭ ድርግም የሚሉ መብራቶችን አንጠልጥለዉ የክረምትን የብርድ ድብርት ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ለማምለጥ ሲሯሯጡ ይታያል። በገና በአል በተለይ ህጻናት ስጦታን ከእህት ወንድም ከእናት ከአባት ከአጎት አክስት ከአያት ከጎረቤት ስለሚያገኙ የበአሉን መምጣት በጉጉት ነዉ የሚጠብቁት። በአሉን በጉጉት የሚጠብቁት ህጻናት ብቻ ሳይሆኑ ነጋዴዎችም ናቸዉ። የሱቅ መስኮት ላይ የተለያየ ለአይን ማራኪ ጌጣጌጥ አድርገዉ በሮቻቸዉን በደንብ ከፍተዉ እበር ላይ ስጦታ የሚሰጥ ሰዉ አቁመዉ እቃዎቻቸዉ እንዲሸጡ በርካታ ዘዴዎችን የሚፈጥሩ ነጋዴዎች በገና ገበያ ሰዉ ለወዳጁ ያሰበዉን ሳይሆን ያላሰበዉንም ጨምሮ ጨማምሮ እንገዛ ያደርጉታል፣ የተለያዩ ቅናሾችን በማድረግና ጥቃቅን ስጦታዎችን በመስጠት። ኢትዮጽያዊዉ ሱራፊል ጌታቸዉ እዚሁ ጀርመን አገር ዉስጥ በመስተዋት ስራ ምህንድስና ትምህርታቸዉን ተምረዉ በአንድ የጀርመን ድርጅት ዉስጥ ተቀጥረዉ በመስራት ላይ ናቸዉ። የጀርመን ራድዮን አድማጭ የሆኑት አቶ ሱራፊል ሰሞኑን ራድዮናችሁን ስከታተል የበገና ጠጅ በሚል አንዲት ጀርመናዊት የምትጠለዉን ጠጅ ገዝቼ የፈረንጆቹ ገና እለት ከጓደኞቼ ጋር ለመቅመስ ቀጠሮ ይዣለሁ ይላሉ።
Deutschland Adventskalender Heiligabend Geschenke unter dem Weihnachtsbaum


የገና በአል ሲዳረስ አለቃ ለሰራተኞቹ ደሞዝ ጨመር አድርጎ የመስጠት ተለምዶ አሁን አሁን በኢኮነሚ ቀዉሱ እየቀነሰ መጣ እንጂ ባህሉ ያለ ነዉ። በየመስራቤቱ በየክፍል ክፍሉ የገና በአልን በማስመልከት ሁሉም እንደ አቅሙ ምግብ ሰርቶ በሞያዉ አምጥቶ ቡና ተፈልቶ ከስራ ባልደረባ ጋር መልካም ገናን ተመኝቶ ለገና እረፍት መሰነባበቱ የተለመደ ነዉ። እኛም እዚህ በዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ ላይ የኪስዋሂሊ ቋንቋ ባልደረቦች የሃዉሳ ቋንቋ ክፍል ባልደረቦች ባህላዊ ምግባቸዉን ይዘዉ እኛም እንጀራና የጾምና የፍስክ ወጣችንን ሰርተን ጀርመናዉያኑም ጥብሳ ጥብሳቸዉን እና ኬክ ብጤ ጋግረዉ ተቋድሰን የተቀደሰ የገና በአል እና መልካም አዲስ አመትን ተመኝተን እረፍት ያለዉ ወደ እረፍቱ ስራም ያለዉ መልካም ስራ እንዲሆንለት በመመኘት ተለያይተናል። የገና በአል ሲዳረስ ያዘነን ማጽናናቱ የተራበን ማብላቱ የታረዘን ማልበሱ የተለመደ ነዉ።
በገና በአል መዳረሻ በጀርመን በረዶዉ ወርዶ አገር አልብሶ ከአመት እስከ አመት ቅጠሉ የማይረግፈዉ እና አረንጓዴ ሆኖ የሚቆየዉ ጽድ በበረዶ ተሸፍኖ ሲታይ ለአገሪዉ ነዋሪ በገና በአል የተሳካለት የአየር ሁኔታ እንደሆነ ይገልጻል። በዚህም በረዶ የለበሰዉ ነጩ የገና በአላችን ይሉታል። በፈረንጆቹ ገና ምእራባዉያኑ የጽድ ዛፍን ማስጌጣቸዉ የተለመደ ነዉ። ለዘንድሮዉ ገና የሚቆረጠዉ የጽድ ዛፍ በቅድ ለዚሁ ለገና በአል ተብሎ ይተከላል፣ በደረሰም ግዜ ተቆርጦ ለገበያ ይዉላል። ታድያ አንድ ለገና በአል የታሰበ መጠነኛ ጽድ ከሃያ ብር እስከ መቶ ሃምሳ ብር ድርስ እንደሚያወጣ ተዘግቦአል፣ በየአደባባዪ የሚቆመዉን ሰማይ ጠቀስ የገና በአል ጽድን ሳይጨምር።
በነገዉ እለት ምሽት የገናን በአል ለሚያከብሩ ሁሉ መልካም የገና በአል እንመኛለን። ጥንቅሩን ያድምጡ!
አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ