የጀርመናዉያኑ ኳስ ድልና የኢትዮጵያዉያኑ አስተያየት | ባህል | DW | 17.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የጀርመናዉያኑ ኳስ ድልና የኢትዮጵያዉያኑ አስተያየት

በጀርመን ሃገር የምንኖር አብዛኞች የዉጭ ሃገር ዜጎች በሃገሪቱ የፈለግነዉን ነገር ስለምናደርግ፤ አብዛኞች የዉጭ ተወላጆች ብንሆንም በዜግነት ጀርመናዊ በመሆናችን ከህዝቡ ጋር ፤ የቡድኑን ማልያ ለብሰን ባንዲራዉን አንግበን ጨዋታዉን በሚገባ በሃሳብ ተካፍለናል፤ አብረን ከቡድኑ ጋር ታመናል። ጀርመን ዋንጫዉን በመዉሰዱ በጣም ደስተኛ ሆነናል ይሉን፤

Fußball WM 2014 Empfang Nationalmannschaft in Berlin

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በበርሊን ከተማ አቀባበል ሲደረግለት

በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ትምህርታቸዉን የተከታተሉትና በአሁኑ ግዜ የበርሊን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዩናስ ለማ፣ ናቸዉ።

ብራዚል ያስተናገደችዉ 20ኛዉ የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ፤ አጓጊ በሆነ ሁኔታ በጀርመን አሸናፊነት መጠናቀቁ የቅርብ ቀናት ትዝታ ነዉ። ጀርመናዉያኑ የእግር ኳስ ተጫዋቾች እና የቡድኑን አባላት ከብራዚል ጭኖ ወደ መዲና በርሊን ያጓጓዘዉ የሉፍታንዛዉ አዉሮፕላን

Fußball WM 2014 - Angela Merkel beim Deutschland-Spiel

የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል የጀርመን እና የአርጀንቲናን የዋናጫ ግጥምያ በስቴዲዮም ሲከታተሉ

«የአሸናፊዎች መብረሪያ» የሚል ስያሜ ተሰጥቶም ነበር። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀዉን የኳስ ግጥምያ ለአራተኛ ግዜ አሸናፊ የሆነችዉ ጀርመን፤ ምዕራብና ምስራቅ ተከፍላ ቆይታ በይፋ ከተቀላቀለች ወዲህ ይህን ዋናጫ ስትወስድ የመጀመርያዋ ነዉ። የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ግጥምያዉ ለኢትዮጵያዉያን እንዴት ነበር? በጎርጎረሳዊ 1990 ዓ,ም ጀርመን የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያ አሸናፊ ሳለች ምስራቅ ጀርመን የነበሩ ኢትዮጵያዉያን የያኔዉን ትዉስታስ? የዘንድሮዉንስ ድል? የጀርመኑን ዓለም እግር ኳስ ድል ፈንጠዝያን እየቃኘን፤ ከረዥም ጊዜያን አስንቶ ጀርመን ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን የሰጡንን አስተያየት እናደምጣለን መልካም ቆይታ።
ጀርመን ከጎርጎረሳዊ 1990 ዓ,ም በኋላ ያሳካችውን የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ፤ ፤ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች በስቴዲየም ተገኝተው ተከታትለውታል። ከመሪዎቹ መካከልም የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋዉክ፤ እንዲሁም በእግር ኳስ ፍቅራቸው የሚታወቁት የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክልም ተገኝተዉ ነበር። ብራዚል ላይ የነበረዉ የጨዋታዉ ሰዓት በጀርመን የመኝታ ሰዓት በመሆኑ ማለዳ ወደ ሥራ የሚሄዱ ጀርመናዉያን፤ የእንግቅልፍ ግዜያቸዉ ተዛብቶባቸዉ ነበር። የጀርመን ቡድን ግን ባካሄዳቸዉ ግጥሚያዎች ከቀን ወደ ቀን አሸናፊነትን እያገኘ በመምጣቱ፤ ስለእንቅልፍ ማሰብ ሳይሆን በአንፃሩ መሽቶ መቼ ግጥምያዉ ተጀምሮ የሚለዉ ፍላጎት በአብዛኛዉ የጀርመን ነዋሪ አመዝኖ ይታይ ነበር። የዛኑ ያህል ቤተሰብ ጓደኛ ጎረቤት ተሰባስቦ የጀርመንን ባንዲራ በተለያየ መልኩ አንግቦ በአንድ ላይ መብላት መጠጣቱ እና ጨዋታዉን በቴሌቭዥን መከታተሉ የዓለም እግር ኳስ ግጥምያዉ ድባብ ሆኖ ሰንብቶአል። በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንም ከጀርመናዉያኑ ጎን ተሰልፈዉ ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን ድጋፋቸዉን ሲገልፁ ነዉ የሰነበቱት፤ በዝያን ጊዜዋ ምሥራቅ ጀርመን ተማሪ የነበሩትና ረዘም ላለ ግዜ በጀርመን ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮናስ ለማ፤ የዘንድሮ የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያ ይላሉ፤

Siegerflieger Fanhansa Flugzeug Lackierung Lufthansa Flughafen Rio de Janeiro WM 2014

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ከብራዚል የተመለሰበት «የአሸናፊዎች መብረሪያ»


« የዘንድሮ የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያ ለኔ ከሌሎች የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫዎች የተለየ ነበር። ምክንያቱም ደካማ ተጫዋቾች አልዋቸዉ ወይም በኳስ ጨዋታ ያላደጉ የሚባሉት ሃገራት ቡድኖች እንኳ፤ጠንካራ አጨዋወት ያሳዩበት፤ ኳስ ጋ እኩል መሆናቸዉን ያስመሰከሩበት ፤ ጠንካራ ፉክክር የታየበት ግጥምያ ነበር። የምንደግፈዉ ቡድን እንዲያሸንፍ ፀሎቱም፤ ጭንቀቱም በየአንዳንዳችን ልብ እና አዕምሮ ዉስጥ የተቀረፀ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ግሩም መድረክ ነበር። በተጨማሪ ፍቅር የታየበት አብሮ መደሰት መወያየት የተለያየ ቡድን ብንደግፍም መሰባሰብ፤ መተሳሰብ የነበረበት፤ የዓለምን ህዝብ በአንድ ወቅት ወደ ኳስ መድረክ ተስቦ አንድ እንዲሆን ያደረገ ትልቅ ስፖርት መሆኑን የተገነዘብኩበት ወቅት ሆኖ አግንቸዋለሁ።» አቶ ዩናስ የ 1990 ዉን የጀርመን የዓለም እግርኳስ ጨዋታ አሸናፊነት እንዴት ያስታዉሱት ይሆን?
«የ1990 ዓ,ም የዓለም ዋንጫ ልዩ የሚያደርገዉ በተለይ ጀርመኖችን በተመለከተ ሁለቱን ጀርመኖች ለያይቶ የነበረዉ ግንብ በፈረሰ ማግሥት የተደረገ በመሆኑ ነዉ። ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን በይፋ የተዋሃዱት በጎርጎረሳዊ 1990 ዓ,ም ጥቅምት ሶስት ቢሆንም፤ ግን ግንቡ የፈረሰዉ በ 1989 ዓ,ም በመሆኑ፤ የዓለም ዋናጫዉ ጨዋታ ከዝያ በኋላ የተካጌደ ግጥምያ ስለሆነ በተለይ ምስራቅ በነበረዉ የጀርመን ህዝብ ዘንድ በጣም ትልቅ ደስታና ፈንጠዝያ ነበር የታየዉ።
በጀርመን ሃገር ሲኖሩ ከ 40 ዓመታት በላይ የሆናቸዉ አቶ አለማየዉ ክበበዉ በበኩላቸዉ ፤ የ1990 ዉን የጀርመን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ እንዲህ ያስታዉሱታል።
«በዉህደቱ ሂደት ወቅት የተካሄደ የዓለም ዋንጫ ግጥምያ ስለነበር፤ በተለይ የምስራቅ ጀርመን ህዝቦች ደስታቸዉ ወደር የሌለዉ ነበር። በአንፃሩ በምዕራብ ጀርመን የሚገኘዉ ህዝብ ደስታዉን በቁጥቡ ነበር ያሳየዉ። በአጠቃላይ ግን የጀርመን የኳስ ፍቅር የተነሳሳዉ ከጎርጎረሳዊ 2006 ዓ,ም በኋላ ነዉ። የጀርመን ህዝብ ለኳስ ፍቋሩን እና ስሜቱን ሆ ብሎ ማሳየት ባንዲራዉን ማዉለብለብ የጀመረዉ ከዝያዉ ከጎርጎረሳዊ 2006 ዓ,ም በኋላ ነዉ።» በበርሊን ነዋሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ፤ በጀርመን ይላሉ « በጀርመን ከ2006 ዓ,ም በፊት የኳስ ፍቅር በጅጉ ቢኖርም ግን፤ የኔን ቡድን ልደግፍ ብሎ የሚታየዉ ስሜት እጅግ የተደበቀ ነበር፤ ማንም ደፍሮ ጀርመናዊ ነኝ ብሎ ደስታን የማሳየት የመግለፅ ሁኔታ አይታይም ነበር። ዛሪ እንደሚታየዉ አደባባይ ባንዲራቸዉን ይዘዉ ለሚወዱት ቡድን ድጋፍ መስጠት ሁኔታ የለም ነበር። ይህ የሆነዉ ጀርመኖች ከዚህ በፊት ባላቸዉ ታሪካዊ ሂደት፤ ማለትም በሁለተኛዉ እና በአንደኛዉ ዓለም ጦርነት ሰበብ፤ ያላቸዉን ዉስጣዊ ሃገራዊ ስሜት እንዲደብቁ አድርጎአቸዉ ቆይቶአል። ጀርመናዊ ነኝ የሚል ሥሜታቸዉን ገልፀዉ አያወጡም ነበር።»

Merkel WM deutsches Team

የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርክል የጀርመን እና የአርጀንቲና የዋናጫ ግጥምያ በጀርመን 1- 0 አሸናፊነት ከተፈፀመ በኋላ ከቡድኑ ጋር የተነሱት ፎቶግራፍ


በቻይና ኢትዮጵያ ግንኙነት የዶክትሪት ትምህርታቸዉን ጀርመን ቦን ከተማ በሚገኘዉ ዩንቨርስቲ መከታተል ላይ ያሉት አቶ አለማየሁ ደምሴ በኩላቸዉ፤ የዓለም እግር ኳስ ግጥምያን በጥሞና ተከታትለዋል። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ይላሉ፤ «ባሸነፈ ግዜ ወቅት እንኳ ባላንጣ ቡድኑን ላለመጉዳት ሲል ደስታዉን በቁጥብነት ነበር ሲገልፅ የታየዉ። በዚህም ቡድኑ የብሔራዊ ቡድኑን ስም ብቻ ሳይሆን ለጀርመን ገፅታ አዎንታዊ ሁኔታና ክብርን ነዉ ያጎናፀፈዉ። በዚህም የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ያሳየዉ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ኤኮኖሚ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምን አይነት ትምህርትን እየሰጠ ነዉ የሚል ጥያቄና ዉይይትን አስነስቶአል።»
በጀርመን ሲኖሩ ከ 25 ዓመት በላይ የሆናቸዉ በምሥራቅ ጀርመን ተማሪ የነበሩት አቶ መስፍን አማረ፤ ለረጅም ግዜ የጀርመን የእግር ካስ ቡድን ደጋፊ መሆናቸዉን ይገልፃሉ። ጀርመን ሁለት ግዜ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ሲወስድ ጀርመን የነበሩት አቶ መስፍን ባለፈዉ ግዜ ይላሉ የ 1990ዓ,ም በማስታወስ
«እኔ የጀርመን ቡድን ደጋፊ ነኝ። ቀደም ባሉት ዓመታት የጀርመን የኳስ ጨዋታ ቡድን ተወዳጅ አልነበረም። ጥሩ ጨዋታን አያሳይም፤ የኳስ ጥበብ የለዉም እየተባለ ይተች ነበር። አሁን አሁን ግን በተለይ ከጎርጎረሳዊ 2006 ዓ,ም ጀምሮ፤ ቡድኑ በአዲስ በመማዉቅር ስራ ከጀመረ በኋላ በጣም ጥሩ ጨዋታን ማሳየት ጀምሮአል። ከዝያን ግዜ ወዲህ የጀርመን የእግር ኳስ ክለቦች በርካታ ደጋፊዎችን ማፍራት ጀምረዋል፤ በርካታ ሴቶች ደጋፊዎችም አሉት። እንደሚታወቀዉ እግር ኳስ ጥቁሩ ነጩን አንድ የሚያደርግ የፍቅር መድረክ ነዉ። ጀርመን የ1990 ዓ,ም የዓለም ዋንጫን ስታሸንፍ ሁለቱ ጀርመኖች የመቀላቀል ሂደት ላይ ስለነበሩ ብዙ ግርግር ነበር፤ ብዙም ግልፅ የሆነ ነገር አይታይም ነበር። ቢሆንም ግን በጀርመን ትልቅ ክስተት ነበር። ከዝያ በፊት ከአስራ ስድስት ዓ,መት በፊት በጎርጎረሳዊ 1974 ዓ,ም ነበር የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የነበሩት።»
አንድ ሀገር የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያን ሲያሸንፍ ማየት በተደጋጋሚ የሚከሰት አይደለም ያሉት አቶ መስፍን የጀርመን ቡድን የብራዚሉን የዓለም ዋንጫ አሸንፎ በርሊን ላይ የተደረገለትን አቀባበል በተመለከተ ሲናገርሩ

Weltmeister Feier Berlin 15.07.2014 Fanmeile am Brandenburger Tor

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በበርሊን ከተማ አቀባበል ያደረገለት ህዝብ ወደ 400 ሽህ እንደሆነ ተነግሮአል

«አንድ ሰዉ የሚደግፈዉ ሃገር የዓለም ዋንጫን ሲያሸንፍ በህይወት ዘመኑ አንድ ግዜ ምናልባትም ሁለት ግዜ እግዝያብሄር ከፈቀደ ደግሞ ሶስት ግዜ ሊያይ ይችላል። እኔ እድለኛ ሆኜ ሁለት ግዜ አይቻለሁ፤ እና ነገሩ እጅግ ስሜታዊ ነዉ፤ የሚደግፉት አንድ ሃገር የኳስ ግጥምያ ሲያካሂድ እንባ እያነቀ፤ በስሜት እየታመመ ነዉ ጨዋታን የሚከታተለዉ። ለዘመናት በኳስ ጨዋታ ስትደግፋቸዉ የነበሩ ወጣቶች፤ የዓለም መድረክ ዋንጫን ሲያሸንፉ ማየት ትልቅ ደስታን ያጎናጽፋል። ይህ ደስታ ደግሞ ለደጋፊ፤ ለተጫዋቹ እንዲሁም ለሃገሪቱም ጭምር ነዉ። ጨዋታዉ ህዝቡን አንድ አድርጎ ይቻላል እንዲል፤ በዓለም የዉድድር መድረክ ዉጤት ማምጣት እንችላለን እንዲል እና ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል። ጨዋታዉ እንዲህ ቀላል ሳይሆን ደግሞ ስንት ትግል መዉደቅ፤ ርግጫና ድካም የታየበት ነበር። የጀርመን ቡድን ያመጣዉ ዉጤት ለአንድ ሰዉ ህይወት መመርያ ሊሆን የሚችል እንደ ምሳሌ የሚቀርብ ነዉ። ተምሳሌነቱ ደግሞ፤ አንድ ሰዉ ወድቆ እንዳይቀር፤ ተነስቶ እንዲሮጥ፤ ተነስቶ እንዲሰራ፤ አንድ ዓላማ እንዲኖረዉ ነዉ። ለዝያም ነበር ቡድኑ በአንድነት ለአንድ ዓላማ ተነስቶ ታግሎ ግቡ የደረሰዉ።»
ብራዚል በአስተናገደችዉ የዓለም እግር ኳስ መድረክ ተካፍሎ፤ የአሸናፊነቱን ዋንጫ ይዞ፤ በድል ወደ ሃገሩ የተመለሰዉ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን፤ በዓለም መድረክ ለጀርመን አወንታዊ ገፅታን እንዳስገኘ በዓለም ሃገራት ብዙሃን መገናኛዎች በማስተጋባት ላይ ይገኛል። እኔ በዚሁ ቅንብሬን ላጠናቅ አዜብ ታደሰ ነኝ፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን ማህደር በመጫን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic