የጀርመኑ የካርኔቫል ድግስ | ባህል | DW | 27.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የጀርመኑ የካርኔቫል ድግስ

በጀርመን በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ለሳምንት የሚዘልቀዉ የካርኔቫል ድግስ ዛሪ በድምቀት ተጀምሮአል። ጀርመናዉያን የሚያከብሩት ብዙ ባህላዊና ልማዳዊ በዓላት አልዋቸዉ። ትልቅና ተወዳጅ ከሆኑት በዓላት መካከል ፤ የገና፣ የዘመን መለወጫ እንዲሁም የፋሲካ በዓል ሲሆን፤ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የሌለዉ የካርኔቫል ድግስም

በጀርመናዉያን ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅና የሚከበር በዓል ነዉ። የካርኔቫል በዓል የራይን ወንዝን በሚያዋስኑ የጀርመን ከተሞች፤ በተለይ በኮለኝ በዲስልዶርፍ እና በማይንዝ በድምቀት ይከበራል። የዕለቱ ዝግጅታችን እስከ ሚቀጥለዉ ሳምንት ረቡዕ ስለሚዘልቀዉ ስለ ካርኔቫል በዓል አከባበር ያስቃኘናል!

በጀርመን በተለይ በኮለኝ በዲስልዶርፍ እና በማይንዝ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበረዉ የካርኔቫል ድግስ፤ እንደዚህ ባይጎላም አሁን አሁን በሌሎች የሀገሪቱ አዉራጃዎችና ከተሞችም ሲከበር ይታያል። የካርኔቫል

ድግስ እንደየ አካባቢዉ፤ ስሙም ይለያል አንዳንዱ አካባቢ ካርኔቫል ሲሰኝ አንዳንድ አካባቢዎች ፋስትናህት አለያም ፋሺንግ ሲሉ ይሰይሙታል። በዚህም አለ በዝያ የድግሱ ይዘት ምንም አይነት ልዩነት የለዉም። ድምፁ እንዲቀረፅ ያልፈለገ አንድ ጀርመናዊ የዶቼ ቬለ የቴክኒክ ክፍል ሠራተኛ፤ የካርኔቫል ድግስን እንዴት ትገልጸዋልህ፤ ብለዉ፤ አጠር አድርጎ «ሰዎች ያለምንም ጭንቀትና ጥበት፤ ከመጠን በላይ፤ በደስታ፤ በምግብ፤ በመጠጥ፤ በዳንስ፤ በጭፈራ፤ የሚያሳልፉት በዓል» አለ። ዛሬ በተጀመረዉ ድግስ በየመሥርያ ቤቱ በየመንገዱ ፤ የተለያዩ አስቂኝ እና አስፈሪ የሆነ አልባሳትንና ጭንብልን ያደረጉ ሰዎች ሲዘፍኑ ሲደንሱ ሲጡ ይታያል። ለወትሮ ስርዓት ጠብቆ ኮስተር ብሎ ይራመድ የነበረዉ ፤ ስርዓት ጠብቆ ይናገር የነበረዉ ጀርመን፤ በካርኔቫል ድግስ በደስታ ሲያንጎራጉር ፤ ጮክ ብሎ ሲዘፍን፤ አልያም አስቂኝ ልብስ ለብሶ መንገድ ላይ ማየቱ የተለመደ ነዉ። በጋዜጠኝነት ሞያ ለ46 ዓመታት ያገለገሉት እና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት የዶቼ ቬለ ጋዜጠኛ ጌታቸዉ ደስታ፤ ሰሞኑን ወደ ቢሯችን ብቅ ባሉበት አጋጣሚ ጀርመን ሲኖሩ ለመጀመርያ ግዜ የካርኔቫል በዓልን እንዴት እንዳከበሩ ጠይቄያቸዉ ነበር፤ አከባበሩን እብደት ሲሉ በአጭሩ ይገልፁታል።

በካርኔቫል ድግስ ምክንያት ዛሬና ነገ በዚህ በቦን እና አካባቢዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዉ ይዉላሉ። ከሰላሳ ቋ በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች የሚያሠራጨ ዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያም፤ ድግሱን ለማክበር ለነገ ዓርብ ቀጠሮ ይዞአል። የጣብያዉ ባልደረባ በቀኑ ብዙ የሥራ ጫና የሌለበት ማለት ነዉ እንደተለመደዉ፤ የዉጭ ዜጋዉ የሃገር ባህል ልብሱን፤ ጀርመናዉያኑ ደግሞ ያሻዉ እንደ እብድ፤ ደሞ የፈለገ እንደ ወታደር አልያም እንደ ሙሽራ፤ አልያም እንደ ቀዳጅ ዶክተር ለብሶ፤ በገፍ የሚቀርበዉን ቢራ እየቀዳ፤ የሚቀርበዉን የተለያየ ምግብ እየተመገበ ይደንሳል፤ ይዘፍናል።

በዶይቼ ቨለ ቴክኒክ ክፍል ሲያገለግሉ ከ 25 ዓመት በላይ የሆናቸዉ ክሪስቶቭ ግሮቨ፤ ካርኔቫልን ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር በአካባቢያቸዉ እንዲሁም ከሥራ ባልደረቦቻቸዉ ጋር በጋራ ያከብራሉ፤

« በኖርድ ራይን አካባቢ ብወለድም ፤ ለካርኔቫል ድግስ ልቤ አይቆምም። እንደ አመጣጡ ነዉ የምቀበለዉ። እንደሌላዉ ሰዉ፤ ገና ድግሱ ሳይደርስ የምለብሰዉን ነገር አላዘጋጅም። እራሱ ግዜዉ ሲደርስ እጄ ያገኘዉን ነገር ገዝቼ፤ ጓደኛ ዘመድ በሚበዛበት አካባቢ ሄጄ ከተመቸኝ ጋር አከብራለሁ። ይህ ድግስ ሲመጣ በግድ ደስታ ማምጣት በግድ መጫወትን አልሻም፤ ደስ ካለኝ ነዉ፤ ሁሉን ነገር የማደርገዉ፤ ደስ ካላለኝ እና በል በል ካላለኝ ደግሞ አላከብርም። አራት ልጆች ስላሉኝ እንደዉ አላከብርም ብዬ ቁጭ ባልልም፤ ግን ራሴን አላስገድድም። ለደስታ፤ ሁኔታና ግዜን ጠብቄ እቀላቀላለሁ።»

እዚሁ በኖርድዝ ራይን ዌስት ፋልያ ግዛት፤ ከራድዮ ጣብያችን እንብዛም ሳይርቅ አንድ ግዙፋ የአዛዉንቶች መጦርያን የሚያስተዳድሩት፤ ወ/ሮ መሠረት አለፈለገሰላም በጀርመን ሲኖሩ ከ 30 ዓመት በላይ ሆኗቿዋል። ካርኔቫል ሲደርስ በድርጅታቸዉ ለሚኖሩ አዛዉንቶች በደመቀ ሁኔታ እንደሚደግሱ ገልፀዉልናል። አምስት ሺ ዘመን እንዳስቆጠረ የሚነገርለት ይህ የካርናቫል ድግስ በተለይ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የፋሲካ ጾም ለመጀመር ሲቃረቡ በፈነዝያ ለሰባት ቀናት ቆይተዉ፣ ከዚያ ስድስት ሳምንት የፋሲካን ጾም የሚጾሙበት ሁናቴ መኖሩን ዘገባዎች ያስረዳሉ። በጀርመንም አብዛኛዉ የካቶሊክ እምነት ተከታይ በምእራቡ እና በደቡባዊ የአገሪቷ ክፍል ስለሚኖር ይኽዉ በአል በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። የዶይቸ ቬለዉ የቴክኒክ ክፍል ባለሞያ ከካርኔቫል ድግስ በኋላ ይላል ፤ በሚደረገዉ ፆም፤

«ቤተሰቦቼ ካቶሊኮች ናቸዉ፤ በዚህ ሃይማኖት ነዉ አንፀዉ ያሳደጉኝ። ዓርብ ዕለት በሥጋ ምትክ እንበላ የነበረዉ፤ አሳ ነዉ፤ እና እነዚህን የመሳሰሉ ልምዶችን አዉቃለሁ። ግን በግድ ፁሙ የሚል ሕግ የለም፤ ዋናዉ ነገር ከካርኔቫል በኋላ ፋሲካ እስኪደርስ ድረስ፤ ረጋ ማለትና ብዙ ደስታን የሚሰጥ ነገር ከማድረግ እንቆጠባለን፤ የምንወደዉንም ነገር ከመብላት እንቆጠባለን። ወደ ራሳችን ተመልሰን፤ በጎ ሁኔታን እናስባለን። በአንድ የካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት ሳለሁ፤ በፆም ወራት እንዳንበላ የምንከለከላቸዉ ነገሮች ብዙ ነበሩ። በተረፈ፤ በፆም ወር ጀርመን ዉስጥ አብዛኛዉ ራሱን ያርቃል፤ እንጂ ይህን አታድርግ የሚል ሕግ የለም። ያ ማለት በካርኔቫል ወቅት እንደ ልብ ማበድ፤ መብላት፤ መጠጣት፤ መደነስ፤ ያ፤ ሲያበቃ ወደ ራስ መመለስ፤ ራስን ማረቅ ነዉ።»

ዛሪ የጀመረዉ የጀርመኑ ካርናቫል በመጠጥ በደስታ በሙዚቃ እና በፈንጠዝያ ታጅቦ እስከ ፊታችን ሰኞ በመዝለቅ፤ ረቡዕ ይጠናቀቃል። የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ይህንኑ ህዝባዊ ድግስ ተንተርስዉ በቢሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ፤ ወደ ኪሳቸዉ ማስገባታቸዉ ፤በርካታ ጀርመናዉያን ይህ ባህላዊ ድግስ ከባህልና ከልምዱ ባሻገር የንግድ መድረክ ሆነ ሲሉ ትችታቸዉን ሲያሰሙ ይደመጣል። ዶቼ ቬለ የራድዮ ጣብያም የሳምንቱን መጨረሻ አስታኮ ነገ አርብ ቢራና ምግብ በገፍ አቅርቦ፤ በካርናቫል ወቅት የጂዘፈነዉን ዘፈን የሚጫወቱ ሙዚቀኞችን ጋብዞ እኛ ሰራተኞቹን ከነቤተሰብ ጋደኛ ወዳጆቻችን ጋር ይዘን የድግሱ ተካፋይ እንድንሆን ጋብዞአል። ሙሉዉን ዝግጅት የድምፅ መጫዉን በመንካት ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic