የጀርመኑ ማዕከልና ዓላማዉ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የጀርመኑ ማዕከልና ዓላማዉ

የሟች አስከሬን ካረፈበት ጉርጓድ አልፍ ብሎ-ብዙ ጥቋቁር ባዶ ወንበሮች ተደርድረዋል።በየወንበሩ ላይ ሥም ተለጥፎበታል።አንዱ የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ነዉ።ሁለተኛዉ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ቶማስ ደ ሚዝየር።ይሕ ነዉ-ኪነታዊነቱ።መልዕክቱ-ደግሞ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:09

የጀርመኑ ማዕከልና ዓላማዉ

የፖለቲካዊ ዉበት ማዕከል (ZPS) የተሠኘዉ የጀርመን ማሕበር የአዉሮጳ መንግሥታት ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንዳይገቡ መከልከላቸዉን በድጋሚ አወገዘ።ዉግዘት ተቃዉሞዉን በኪነጥበባዊ ሥልት የሚገልፀዉ ማዕከል በቅርቡ ወደ አዉሮጳ ስትሰደድ ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ሰምጣ የሞተች አንዲት የ34 ዓመት ወጣት እናትን አስከሬን በርሊን አስመጥቶ በክብር አስቀብሯል።ከሴትዮዋ ጋር የ2 ዓመት ልጇም ሞቷል ግን አስከሬኑ ሥላልተገኘ አልተቀበረም።የፖለቲካዊ ዉበት ማዕከል ባልደረቦች እንደሚሉት ማዕከላቸዉ በርሊን ድረስ አስመጥቶ የቀበራት እናት ወደ አዉሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ የሚያልቁትን ስደተኞች የምትወክል ናት።የማዕከሉ አባላት የአዉሮጳ መንግሥታትን በተለይም የጀርመን መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አጠናቅሯል።

የቲአቲር ጥበብ አዋቂና የፖለቲካ ፈልስፍና አቀንቃኙ ፊልሊፕ ሩኽ ያሰባሰባቸዉ ሰባ ያሕል ሰዎች ፊታቸዉ ላይ ጥላሸት ጫር ያደርጉበታል።ባለባበሳቸዉ ጥቁር ቀለም ያዘወትራሉ።የሐዘን ምልክት መሆኑ ነዉ።የማዕከላቸዉን ሥም «ፖለቲካዊ እና ዉበት» ብለዉታል።ጥቁርና-ዉበት፤ ሐዘንና-ፖለቲካ።ዓላማ፤ አስተሳሰብ ምግባራቸዉ ግን ዞሮ ዞሮ-ሰብአዊነት ነዉ።

ግፉአንን መርዳት፤ በደልን መቃዉም፤ ፖለቲከኞች ለሰዉ ልጅ ጥሩ ጥሩዉን እንዲያደርጉ መምከር፤መንገር፤ እንቢኝ ሲሉ ማዉገዝ ነዉ።ድጋፍ፤ ምክር፤ ተቃዉሞ፤ ዉግዘታቸዉን ብዙ ጊዜ የሚገልጡት በኪነጥበብ ነዉ።በቀደም በርሊን ያደረጉት ግን ኪነ-ጥበብ ይሁን ፖለቲካ ለማዕከሉ አባል ለዩስቱስ ልንስም አልገባዉም።

«እኛ የምናደርገዉ በተለይ አሁን ያደረግነዉ ኪነጥበብ ነዉ ወይስ ፖለቲካ ብዙ እያነጋገረ ነዉ።እኔም እራሴ መመለስ አልችልም።ሰዎች የሰጡት አስተያየት የሚገርም ነዉ።ገሚሶቹ ኪነጥበብ ነዉ-ይላሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ የለም ይሕ ኪነጥበብ አይደለም።እኔም አልመልሰዉም።ተመልካቹ እንደየግንዛቤዉ የሚሰጠዉ ትርጓሜ አማላይ ነዉ።»

የማዕከሉ የሰሞኑ ዋና ትኩረት ስደተኞች ናቸዉ።የአዉሮጳ መንግሥታት በራቸዉን በጦር ሐይል በመዝጋታቸዉ ሺዎች ማለቃቸዉን አጥብቀዉ ይቃወማሉ።ግን የአደባባይ ሠልፍ አልጠሩም፤ አልፈከሩ፤ አላስፈከሩም።የቴሌቪዥን፤ የራዲዮ ክርክር አልገጠሙም።በርሊን መካነ-መቃብር ላይ እንዲሕ አደረጉ።

«የሙስሊም የቀብር ሥርዓት ነዉ።የአንዲት እናት እና የልጅዋ ቀብር።ልጅዬዉ አስከሬኑ ሥላልተገኘ (ማስመሰያ እንጂ) አልተቀበረም።እናትዬዉ የሰላሳ-አራት ዓመት ሶሪያዊት ናት።ጦርነቱን ሽሽት ስትሰደድ የተሳፈረችበት መርከብ ሰመጠና ባለቤትዋ እና ሰዎስት ልጆዋ ፊት ከታቀፈችዉ ሕፃን ጋር ሰመጠች።ይሕ ኪነጥበብ አይደለም።ግን የእንቅስቃሴያችን አካል ነዉ።»

የሟች ባለቤትና ልጆችዋ እዚሁ ጀርመን ናቸዉ።ግን የስደተኝነት ፍቃድ ሥላላገኙ ሰዉዬዉ ዉድ ባለቤቱን፤ ልጆች እናታቸዉን ለመቅበር ወደ በርሊን መጓዝ አልቻሉም።ይሕ ፖለቲካ «መፅዳት፤መዋብ» አለበት ባዮች ናቸዉ ከያኒያኑ።ቁሻሻ ነዉ።

የሟች አስከሬን ካረፈበት ጉርጓድ አልፍ ብሎ-ብዙ ጥቋቁር ባዶ ወንበሮች ተደርድረዋል።በየወንበሩ ላይ ሥም ተለጥፎበታል።አንዱ የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ነዉ።ሁለተኛዉ የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ቶማስ ደ ሚዝየር።ይሕ ነዉ-ኪነታዊነቱ።መልዕክቱ-ደግሞ።

«የእንቅስቃሴያችን አጠቃላይ አላማ ሰዎች (ሲሰደዱ)መሞት የለባቸዉም የሚል ነዉ።ባሁኑ ሰዓት አዉሮጳ ድንበር ላይ ጅምላ መቃብሮች አሉ።የአስከሬን ክምሮች አሉ።በየማቀዝቀዣዉ ቤት የታጨቁ፤ በየቁሻሻ ማከማቸዉ የተጣሉ እስከሬኖች አሉ።ብዙ መናገር አይቻልም።ይሕ ሁሉ የአዉሮጳ ሕብረት የፀረ-ስደተኞች መርሕ ዉጤት ነዉ።ከጀርመን የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ቢሮ የሚወጣ መርሕ ዉጤት ነዉ።ስደተኞቹን መቀበል ችግር መሆን አልነበረበትም።ረሐብ፤ ጦርነት፤ስቃይ ነዉ ያሰደዳቸዉ።አዉሮጳ እንዳይገቡ የአዉሮጳ ሕብረት ጦር የሚወስደዉ እርማጃ ሰብአዊ መብትን የጣሰ ነዉ።»

ይላሉ-ሰሚ ካገኙ።ይታገላሉም።

ነጋሽ መሀመድ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic