የዶክተር አብይ ንግግር እና የፍራክፈርት ነዋሪዎች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የዶክተር አብይ ንግግር እና የፍራክፈርት ነዋሪዎች

ሕገ መንግሥታዊ መብት ያፍናል የሚባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት እና በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የሕሊና እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሙሉ መፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለለውጥ ያላቸው ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት የሚለኩባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸው ተደጋግሞ ይወሳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:34

የዶክተር አብይ ንግግር፤ ተስፋ እና ጥርጣሬ

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ለማረጋጋት መውሰድ ካለባቸው እርምጃዎች ዋንኞቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት እና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሂደት ሊሆን እንደሚገባ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሳሰቡ :: ዶክተር አብይ በንግግራቸው ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት አበክረው መስበካቸው የሃገሪቱ መጻኢ ህልውና ሥጋት ለፈጠረባቸው ወገኖች ተስፋ ሰጭ ቢሆንም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ጉዳይ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የረበው ጥሪ ስኬት የሚያገኘው የዜጎችን የመደራጀት እና ሃሳብን የመግለጽ መብት ሙሉ በሙሉ የሚገድበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት ሲኖርበት እንደሆነም አበክረው አስገንዝበዋል።

ስለ ሃገር ፍቅር ሥሜት ስለ አብሮነት ስለ ፍትህ እና ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለማሸጋገር በስፋት የተሰበከበት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የበዓለ ሲመት ንግግር ዛሬም ህብረተሰቡን ማነጋገሩን እና ማከራከሩን ቀጥሏል :: በአንድ በኩል በሃገሪቱ ሥር እየሰደደ የመጣውን የብሔረሰቦች ግጭት እና ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ የሃገሪቱ የግዛት አንድነት እና ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል የሚል ከባድ ሥጋት ላደረባቸው መጽናናትን በሌላ በኩል ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር መሬት ወርዶ ገቢራዊ መሆን ካልቻለ ጭቆናው የበለጠ እየከፋ ዳር እስከዳር የተቀጣጠለው የነጻነት እና የመብት መከበር ጥያቄም እንዲዳፈን ምክንያት ሊሆን ይችላል ለሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከወዲሁ ጥርጣሬ እና ሥጋትን አጭሯል :: በዶክተር አብይ ተስፋ ሰጭ ንግግር ሙሉ እምነት ማሳደር የማይቻለው ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን ሥልጣን እና የስራ ሃላፊነት በተግባር ለማዋል የሚያስችል የመንግሥት አደረጃጀት መዋቅር እና ባህሪ ባለመኖሩ መሆኑን እዚሁ ጀርመን የተለያዩ ከተሞች ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ይገልጽሉ ::

የኢትዮጵያ ሕልውና እና መጻኢ ዕድል በእጅጉ የሚያሳስባቸው በብዙ ሺህ ማይልስ ርቀት ከሃገር ተሰደው የሚኖሩ አብዛኛዎቹ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ወገኖች በዶክተር አብይ ንግግር ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ መሰበኩ ያስደሰታቸው መሆኑን ዛሬም ድረስ በተለያየ መድረክ እየገለጹ ነው :: ይህን ሃሳብ የሚጋሩት ጀርመን በሚገኘው የትራንስ ዴፍ ታኖስ የሕዝብ ማመላለሻ ካምፓኒ የስራ አመራር ሃላፊ የሆኑት አቶ መላኩ ዘውዴ በኢትዮጵያ ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ልዩ ልዩ የመብት መከበር ጥያቄዎች እና አስቸኳይ አዋጁን በተመለከተ በየደረጃው ምላሽ እስኪያገኙ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ድጋፍ እና የተወሰነ ጊዜ ዕድል ልንሰጣቸው ይገባል ይላሉ ::

ላለፉት 27 ዓመታት በእርስ በርስ የጥላቻ ግጭቶች ምክንያት ብዙ ሰው ሞቷል :: አያሌ ንብረት ጠፍቷል :: ሥፍር ቁጥር የሌለው ሕዝብም ከመኖሪያ ቀየው ተፈናቅሏል :: በገዛ ሃገሩ ብዙ ሰው ስደተኛ ሆኖ እንዲኖር ተገዷል :: ኢትዮጵያዊነት የመላው ህዝብ የአንድነት መሰረት እንዲሆን ከተፈለገ ማንኛውም ዜጋ በሃገሩ ነጻነት እና ሃብት ተጠቅሞ በፈለገው አካባቢ ያለገደብ መኖር መቻል እንዳለበት ብዙዎች ያስገነዝባሉ :: ይህን ሁሉ ውስብስብ ችግር ለመፍታት ብሎም በዛች ሃገር ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት የተነሱት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዕቅድ እና ምኞት እንዲሳካ የሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልጹ ሃሳቦችም በተደጋጋሚ እየተን ጸባረቁ ነው ::

የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እና ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስም ዘላቂ እልባት ለመስጠት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጭው ምርጫ ነጻ እና ፍትሃዊ ስለሚሆንበት ሁኔታ ብዙ መስራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል :: ከዚህ ሌላ የሃገሪቱ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አስቸኳይ ውይይት እና ድርድር ማካሄድ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ያፍናል የሚባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት እና በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የሕሊና እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሙሉ መፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለለውጥ ያላቸው ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት የሚለኩባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸው ተደጋግሞ ይወሳል ::

እንዳልካቸዉ ፈቃደ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ


 

Audios and videos on the topic