የዶክተር አቢይ አህመድ ማንነት | ኢትዮጵያ | DW | 28.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዶክተር አቢይ አህመድ ማንነት

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የኢህአዴግ ምክር ቤት ከጥቂት ወራት በፊት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የኦህዴድን ሊቀመንበርነት ስልጣን የያዙትን ዶክተር አቢይ አሕመድን የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። በኢህአዴግ አሰራር እና በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ዶክተር አቢይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:09

«የንግግር ስጦታና የቅቡልነት አቅም አላቸዉ»

ገዢው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የኢህአዴግ ምክር ቤት ከጥቂት ወራት በፊት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የኦህዴድን ሊቀመንበርነት ስልጣን የያዙትን ዶክተር አቢይ አሕመድን ትናንት የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል። በኢህአዴግ አሰራር እና በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ዶክተር አቢይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዶክተር አቢይ  የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ቢይዙ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ለማቃለል ምን ይህል ይረዳሉ የሚለው ጉዳይ ግን ብዙ እያነጋገረ ነው። 

ዶ/ር አቢይ አህመድ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የ«ኦህዲድ» ሊቀመንበር ሆነዉ እንደተመረጡ የተዜመላቸዉ ሙዚቃ ነበር። በ1968 ዓ,ም ጅማ ዞን አጋሮ ወረዳ የተወለዱት ዶ/ር አቢይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በአጋሮና ጅማ ከተሞች ተከታትለዋል። በመቀጠል በተለያዩ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገራት ዩንቨርስቲዎች  እስከ PhD የሚያደርስ ትምህርታቸዉን አጥንተዋል። ዶክተር አቢይ አህመድ በተካኑት የንግግር ስጦታቸዉና የአድማጭን ቀልብ ከመሳብና ቅቡልነት አቅም ሌላ በቂ የፖለቲካ ብቃት እንዳላቸዉ በበደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ከተማ በጥርስ ህክምና የሚያገለግሉት ዶ/ር መንግስቱ አሰፋ ተናግረዋል።

መምህርና የድረገፅ ፀሐፊዉ አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸዉ ዶክተር አቢይ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተፅኖ መፍጠር የሚችል ችሎታ እንዳላቸዉ አምናለሁ ብለዋል።  «ሊሰመርበት የሚገባዉ ነገር ሁለት ምርጫ የለንም ያለን ምርጫ መደመር ብቻ ነዉ»  

ዶ/ር አቢይ አህመድ ከ 1982 ዎቹ ማለትም ከ«ኦህዲድ» ምስረታ ጀምሮ የድርጅቱ አባል ናቸዉ። ከ 2002ዓ,ም ጀምሮ የ«ኦህዲድ» ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከ 2007 ዓ,ም ጀምሮ የ«ኦህዲድ» ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆን እያገለገሉ ናቸዉ። ከዚህ ሌላ ዶ/ር አቢይ በሃገር መከላከያ ሰራዊት የሌተናኮነሪልነት ማዕረግንም ተቀብለዋል።  የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ አባል ሆነዉ ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ የተመድ ተልእኮ አገልግለዋል። ዶ/ር አቢይ ጠ/ሚር ሆነዉ ቢሾሙ በኢትዮጵያ የሚታየዉን የፖለቲካ ቀዉስ ለመፍታትና ማኅበረሰቡን ለማረጋጋት ምን ያህል ሚና ይጫወቱ ይሆን ? ዶ/ር መንግሥቱ አሰፋ ጥርጣሪ አላቸዉ፤

መምህር ስዩም ተሾመ በበኩላቸዉ ዶ/ር አቢይ አህመድ የፖለቲካዉን ቀዉስ ለመፍታት ፓርቲዉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዉ ይሆን? ሲሉ ጥያቄዉን በጥያቄ ይመልሳሉ።

ዶ/ር አቢይ  በጅማ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዉ፤ የብሔራዊ መረጃ መረብ « ኢንሳ» መስራችና ዋና ዳይሬክተር የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ዳይሬክተር በመለጠቅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዲሁም  ከ 2008 ዓ,ም ጀምሮ የኦሮሚያ ከተሞችና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነዉም አገልግለዋል። ዶ/ር አቢይ አህመድ ለኢህአዴግ በተለይ ለህዉሃት ባለስልጣናት አጎብዳጅ ናቸዉ ከሚባሉት ከጠ/ሚ ኃይለማርያም ደስአለኝ ይለዩ ይሆን? 

የሃገርን ጉዳይ በተመለከተ ዶክተር አቢይ አህመድ አንድ ወቅት ይህን ተናግረዉ ነበር።                         

«ይህ ሃገር የወረስነዉ ሃገር አይደለም ብለናል። ከአባት ከናት የወረስነዉ ሳይሆን ከልጆቻችን የተዋስነዉ ሃገር ነዉ። ዉርስ መሸጥ መለወጥ ይቻላል ትዉስት ግን አጥቦ አጽድቶ የሚመለስ ነገር ነዉ። አሳምረን ማሸጋገር አለብን። »

የሃገርን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር አቢይ አንድ ወቅት እንዲህ ተናግረዉ ነበር።

«አገራችን አሳምረን ማሸጋገር አለብን»ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅርበት ያላቸዉ የሃገሪቱ መከላከያና የደኅንነት መዋቅር በህዋሃት የበላይነት ሥር መሆኑን ይናገራሉ። ዶ/ር አቢይ ወደ ጠ/ሚሩ ሥልጣን ቢመጡ የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግ የገባዉን ቃል ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመን ይሆን?

ሙሉ እንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic