የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ፖለቲካ ሰብዕና እና የጀርመን ቆይታ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 30.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ፖለቲካ ሰብዕና እና የጀርመን ቆይታ

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ያረፉት የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ትሁት በሳል ፖለቲከኛ እና ጠንካራ ሰብዕናን የተላበሱ ሰው እንደነበሩ በጀርመን የሚኖሩ የቀድሞ ወዳጆቻቸው እና የትግል አጋሮቻቸው ይገልጻሉ:: የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:10

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጀርመን

ቅዳሜ ሚያዝያ 20 ፤ 2011 ዓም በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ያረፉት የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ትሁት በሳል ፖለቲከኛ እና ጠንካራ ሰብዕናን የተላበሱ ሰው እንደነበሩ በጀርመን የሚኖሩ የቀድሞ ወዳጆቻቸው እና የትግል አጋሮቻቸው ይገልጻሉ:: እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር ከ 1985 ዓ.ም ጀምሮ በጀርመን ግራ ዘመም የርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ፖለቲከኞች አማካኝነት ፍራንክፈርት ከተማ ውስጥ በተመሰረተው እና ለሶስተኛ ዓለም አገራት በተለይም ለአፍሪቃ ሕዝቦች
ነጻነት እና ዴሞክራሲ በሚታገለው "ዳስ ድሪተ ቬልት" በተሰኘው ነጻ ማህበርም ዶክተር ነጋሶ  ከ 1985 ዓ.ም ጀምሮ በዳይሬክተርነት ተመርጠው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ እና የአፍሪቃን ባህል በማስተዋወቁ ረገድ የማይናቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል ሲሉም እነዚሁ ወዳጆቻቸው ከዶቼቨለ "DW"ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አስረድተዋል::
 እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ 1943 ዓ.ም በምዕራብ ኢትዮጵያ ደምቢዶሎ ከተማ የተወለዱት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ላለፉት 30 ዓመታት ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው።  ከወጣትነት ጊዜያቸው ጀምሮ ለአገራቸውና ለህዝባቸው እንደታገሉ የሕይወት ታሪካቸው የሚያስረዳ ሲሆን በደምቢ ዶሎ አዳማ እና አዲስ አበባ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህርነት የማስትሬት ዲግሪያቸውን ከቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ከወሰዱ በኋላም በምዕራብ ኢትዮጵያ በርዕሰ መምህርነት ጭምር አገልግለዋል:: ከመጀመሪያ ባለቤታቸው ወይዘሮ ዳሲቱ ቀጀላ ጋር ከ 40 ዓመታት በፊት በትውልድ መንደራቸው ወለጋ ትዳር የመሰረቱት ዶክተር ነጋሶ አንድ ወንድ እና ሴት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ከሚገኘው ዮሃን ዎልፍ ጋንግ ፎን ጎቴ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እስከሚያጠናቅቁበት ዘመንም በጋራ አብረው መኖራቸውን በፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት  እኝሁ የቀድሞ ባለቤታቸው ገልጸውልናል:: ዶክተር ነጋሶ ቤተሰባቸውን የሚወዱ እና ትዳራቸውንም አክባሪ ነበር ያሉት ወይዘሮ ዳሲቱ ከሁለት ሳምንት በፊት በጀርመን ትልቁ የፍራንክፈርቱ የዎልፍ ጋንግ ፎን ጎቴ ዩንኒቨርሲቲ ሆስፒታል ለሁለት ሳምንታት ያህል በተመላላሽ ህክምና የጤና ምርመራ ሲደረግላቸው ከቆየ በኋላ ባለፈው ሃሙስ ለድንገተኛ ህክምና እዛው ፍራንክፈርት ወደሚገኘው  ሌላው የዛክዘን ሃውሰን ሆስፒታል በአምቡላንስ ተወስደው በህክምና ላይ እንዳሉ ባለፈው ቅዳሜ ህልፈተ ዜናቸው ተሰምቷል:: ወይዘሮ ዳሲቱ  በወቅቱ ዶክተር ነጋሶ ለሞት የሚያበቃ ህመም እንዳልነበራቸው እና ጠንካራ ሰብዕና የነበራቸው የህዝብ ልጅ ነበሩ ሲሉ ስለ ቀድሞ ባለቤታቸው ይገልጻሉ:: 


ዶክተር ነጋሶ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በተማሩበት ሙያ እና በፖለቲካ ተሳትፎ የተለያዩ ግልጋሎቶችን ያበረከቱ ሲሆን  ከከፍተኛ የትምህርት ትቋም በተመረቁበት ትምህርትም የኦሮሞን ባህል፣ ታሪክ እና እሴት የሚያንፀባርቁ እና የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክሩ የተለያዩ ጥናቶችን አካሂደዋል።  እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር  በ 1974 ዓ.ም  በአገሪቱ የነበረውን የአስተዳደር ሥርዓት በመቃወም ጀርመን አገር የፖለቲካ ተገን ከጠየቁ   በኋላ በኦፍንባህ እና ፍራንክፈርት ከተማዎች ኑሮዋቸውን የቀለሱት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ የፖለቲካ ሰብዕናቸው በውጭው ዓለም የተቀረጸበትን መንገድ ለመቃኘት የረጅም ዘመን ወዳጆቻቸውን እና የትግል አጋሮቻቸውን ዶቼቨለ "DW"ለማነጋገር ሞክሮ ነበር::  ከ30 ዓመታት በፊት በፍራንክፈርቱ ዎልፍ ጋንግ ጎቴ ዩኒቨርሲቲ አብረዋቸው ከተማሩት መካከል በጀርመን የኢትዮጵያውያን ተጋሩ ሊቀመንበር ዶክተር ግደይ አሰፋ እንደሚሉት ዶክተር ነጋሶ የሰውን ሃሳብ በጥሞና የሚያዳምጡ ትሁት የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው እና በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ላይም ንቁ ተሳትፎ ያበረከቱ ነበሩ ::  
ዶክተር ነጋሶ በአውሮጳ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል በመሆንም ለበርካታ ዓመታት የፖለቲካ ትግል ሲያካሂዱ  ቆይተዋል::  የአካዳሚክ ምሁራን እና የተለያየ ሙያ ባለቤት የሆኑ ግራ ዘመም የጀርመን ርዕዮተ ዓለም የፖለቲካ አቀንቃኞች በተለይም በአፍሪቃ እና በሌሎችም የሶስተኛው ዓለም ሃገራት የሚፈጸሙ የዴሞክራሲ እና የመብት ጥሰቶች በምዕራቡ ዓለም መንግስታት በዲፕሎማሲያዊ ውይይት ትኩረት እንዲያገኙ ጫና ለመፍጠር  በመሰረቱት ማህበርም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ እና የአፍሪቃን ባህል በማስተዋወቁ ረገድ ፕሬዝዳንቱ የማይናቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል::  ገለልተኛ ማህበሩ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ለሚከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች ድጋፍ ለማስተባበር እና በስደት የሚገኙ የሶስተኛ ዓለም ሕዝቦች ከጀርመን ህግ ባህል እና ቋንቋ ጋር ትሥራቸውን እንዲያጠናክሩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለበርካታ ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል:: ከዚህ ውጭ በጀርመን ነዋሪ የሆኑ የሶስተኛው ዓለም ሃገራት ፍልሰተኞች በትውልድ አገሮቻቸው መንግስታት የሚፈጽሙትን አፈና እና ጭቆና በመቃወም በሚያዘጋጇቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ድጋፍ መስጠት ውይይት የሚያካዱባቸውን አዳራሾች ማዘጋጀት እንዲሁም በንባብ ክህሎት ንቃተ ህሊናቸውን የሚያዳብሩበትን ነጻ የቤተ መጽሃፍት አገልግሎት ማበርከትም የማዕከሉ ሌሎች ዓበይት ተግባራት ነበሩ::  በነጻ አስተሳሰብ አራማጆች ተጸንሶ
 " የሦስተኛው ዓለም ኣገራት ማዕከል  " /Das Dritte Welt Zentrum / /በሚል ስያሜ  /ፍራንክፈርት ከተማ ቦከንሃይም አካባቢ እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር በ 1981 ዓ.ም ይኸው ማህበር ሲመሰረት ዶክተር ነጋሶም  ከ 1985 ዓ.ም ጀምሮ በአባላት ዲሞክራሲያዊ አብላጫ ድምጽ ተመርጠው ለዓመታት በዳይሬክተርነት ማገልገላቸውን የራየን ማየን ኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ሊቀመንበርና በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ በጋሻው ጉርሙ በትውስታ ገልጸዋል::  

Dr. Negasso Gidada


ጉንተር ሽሮደር ከ 40 ዓመታት በፊት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የጀርመንን ምድር ከረገጡ ጀምሮ በአካል ያውቋቸዋል::በፍራንክፈርት የሶስተኛው ዓለም አገራት ማህበር የቀድሞ አመራር ናቸው:: እሳቸው ለጉብኝት አዲስ አበባ ሲሄዱም ሆነ ዶክተር ነጋሶ ጀርመን ለዕረፍት አልያም ለህክምናም ሲመጡ ለበርካታ ጊዜያት አብረው ጥሩ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን ነው የነገሩን :: በሶስተኛው ዓለም ኣገራት ማህበርም ሆነ በአገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጉዳይ ዶክተር ነጋሶ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ተወዳጅ ሰው ነበሩ ይላሉ ሚስተር ጉንተር  :: 
" ዶክተር ነጋሶ በተፈጥሮው ሰውን የሚወድ ትሁትና መልካም ባህሪ የነበረው ወዳጄ ነው:: ትውውቃችን ፍራንክፈርት ከተማ ከ 1970ዎቹ ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ነው:: ከወራት በፊት ስልክ ተደዋውለን ስለ ጤንነቱ እና በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ ተወያይተን ነበር:: በጤና ዕክል ምክንያት እዚህ ጀርመን በተለያዩ ጊዜያት ለህክምና መምጣቱን አውቃለሁ:: ድንገተኛ ዜና ዕረፍቱን ስሰማ ግን በዕውነቱ በጣም ነው ያዘንኩት:: እሱ እዚህ በሚመጣበት ወቅትም ሆነ እኔ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት ስሄድ አንድ ላይ ተገናኝተን ቡና እየጠጣን ስለ ቤተሰቦቻችን ጉዳይ ስለ ቀደሙት ትዝታዎቻችንና ስለ ፖለቲካ እንቅስቃሴ እያነሳን እንወያይ ነበር:: " ሲሉ የዶክተር ነጋሶ ወዳጅ እና በፍራንክፈርት የሶስተኛው ዓለም አገራት ማህበር የቀድሞ አባል የዕድሜ ባለጸጋው ጀርመናዊው ጉንተር ትዝታቸውን አውግተውናል :: 
በጀርመን የረጅም ዘመን ቆይታቸው በእንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ሰብዕና የተቀረጹት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር ከ1995 ዓም ጀምሮ ሀገራቸውን ለ7 ዓመታት በርዕሰ ብሄርነት አገልግለዋል:: በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ ሲደረግ በነበረው ሂደትም ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል:: የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ዶክተር ነጋሶ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለህክምና ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ ለህክምና ከመጡ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ማረፋቸው ተሰምቷል:: የሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ውጤት እንደተጠናቀቀ ወደ ኢትዮጵያ የሽኝት ፕሮግራም እንደሚደረግ በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ይፋ አድርገዋል:: 


እንዳልካቸው ፈቃደ


እሸቴ በቀለ 
 

Audios and videos on the topic