የዶሃ የድርድር ዙር፣ መሰናክሉና ተሥፋው | ኤኮኖሚ | DW | 25.07.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዶሃ የድርድር ዙር፣ መሰናክሉና ተሥፋው

የዓለም ንግድ ድርጅት ሃገራት የዶሃ የድርድር ዙር ከአምሥት ዓመታት ውጣ-ውረድ በኋላ መክሸፉ ይታወሣል። በወቅቱ ለአንድ ዓመት ገደማ ተሰናክሎ የቆየውን የዶሃውን የድርድር ዙር መልሶ ለማንቀሳቀስ በቀረበ አዲስ አስታራቂ ሃሣብ ጀኔቫ ላይ ንግግር እየተካሄደ ነው። ድርድሩን ከግቡ ለማድረስ አዲስ ተሥፋ መጸነሱ ይሆን?

ኮሜሣር ማንደልሶን

ኮሜሣር ማንደልሶን

ጀኔቫ ላይ በሚገኘው የዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ በወቅቱ የዶሃውን የድርድር ዙር መልሶ ለማንቀሳቀስ በቀረበ አስታራቂ ሃሣብ ላይ ንግግር እየተካሄደ ነው። የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ዙር ግብ በገበዮች መከፈትና በንግድ ደምቦች መለዘብ የበለጠ የውጭ ንግድ፤ እንዲያም ሲል በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት አገሮች ብቻ ሣይሆን በታዳጊዎቹና ራመድ ባሉት የዚሁ ዓለም ክፍል መንግሥታት ዘንድ የበለጠ ብልጽግናን ማስፈን መሆኑ ይታወቃል።
ግቡ ዕውን እንዲሆን ሃብታሞቹ አገሮች ለታዳጊው ዓለም የእርሻ ምርቶች ገበዮቻቸውን ይበልጥ መክፈት ይጠበቅባቸዋል። በምላሹም ታዳጊዎቹና ራመድ ያሉት ብራዚልን ወይም ሕንድን የመሳሰሉ የደቡቡ ዓለም መንግሥታት ገበዮች ለሃብታሞቹ ሃገራት የኢንዱስትሪ ምርቶች በሰፊው መክፈት አለባችው። በዓለም ባንክ ግምት መሠረት ይህ የተባለው ዕውን ቢሆን በዓለምአቀፍ ደረጃ 200 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚደርስ የብልጽግና ግኝት ነው። ይሁን እንጂ ሊታረቅ በማይችል ቅራኔ የተወጠረው የዶሃ ድርድር ዙር እስካሁን የረባ ዕርምጃ አልታየበትም።

የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር የጀመረው ስሟን በወረሰው በፋርስ ባሕረ-ሰላጤ ከተማ በዶሃ ከሥድስት ዓመታት በፊት በ 2001 ነበር። በዚሁ ድርድር መጀመር በታዳጊው ዓለም ብሩህ የልማት ተሥፋ ይጸነሣል። ታዳጊው ዓለም በተለይ በእርሻው ዘርፍ የንግድ ደምቦችን በማለዘብ ሰፊ የንግድ ጠቀሜታ እንደሚያገኝ ነበር ቃል-የተገባለት። ሆኖም ይህ እንዲሆን አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የእርሻ ምርት ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱና ቀረጥ በመቀነስ የንንድ መሰናክሎችን እንዲያለዝቡ የቀረበው ጥያቄ ዛሬ እንደሚታየው ተገቢውን ምላሽ አላገኘም።

የዶሃው የድርድር ዙር አመጣጥ ወይም ሂደቱ ውስብስብና ውጣ-ውረድ የበዛው ነው። አራት ዓበይት ጥረቶቹ ድርድሩን ለግብ የሚያበቁ አልሆኑም። የክሽፈቱን ጥርጊያ አመቻጩ እንጂ! የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ሃገራት ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ በነሐሴ ወር. 2001 ዓ.ም. ድርድሩን ከከፈቱ ከሁለት ዓመታት በኋላ በድርድሩ ግብ ላይ ከአንድነት ለመድረስ ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ ንግግር ይካሄዳል። ሆኖም እርሻ ነክ ጥያቄዎችን አስመልክቶ በሰሜኑና በደቡቡ ዓለም መካከል በነበረው ሰፊ ልዩነት ንግግሩ መክሸፉ ግድ ነበር የሆነበት።

ይህም በተለይ ደቡባዊውን ዓለም ለሕብረት ማነቃቃቱ አልቀረም። ታዳጊዎቹ አገሮች የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሃብታሙ ዓለም አንጻር የራሳቸውን ግንባር ይፈጥራሉ። ይሄው ግንባር አንጻራዊ በሆነ የተራመደ የልማት ደረጃ ላይ የሚገኙትን G-20 እና የድሆቹን አገሮች G-90 ቡድን በአንድ ያሰባስባል። የደቡብ-ደቡቡ ሕብረት መጠናከር ታዲያ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ጥቂትም ቢሆን በአስታራቂ አቅጣጫ እንዲንቀሳቀሱ የተወሰነ ግፊት መፍጠሩ አልቀረም።

በ 2004 ዓ.ም. ጀኔቫ ላይ በተካሄደ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል መንግሥታት ጉባዔ በድርድሩ ለመቀጠል ከአንድ አጠቃላይ ስምምነት ይደረሳል። በዚሁ መሠረት የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካ፣ ጃፓንና ብራዚል የእርሻ ምርት መሰናክሎችን ለማስወገድና የንግዱን ተፎካካሪነት ያከበደውን ድጎማ ለማለዘብ፤ እንዲሁም ወደ አገር በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ኮታና ቀረጥ ለመቀነስ ይስማማሉ። በአጸፋው ታዳጊዎቹ አገሮች ደግሞ ቁልፍ የሆኑ ዘርፎችን የመጠበቅ መብት እንደያዙ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የጣሉትን ቀረጥ ለመቀነስ ዝግጁ ይሆናሉ።

ቀጣዩ የ 2005 የሆንግኮንግ ድርድር ዘላቂ ከሆነ ግብ ለመድረስ በዋዜማው የታቀደበት ነበር። ግን እስከዚያው የተደረጉት ዕርምጃዎች ለዚህ ዓላማ በቂ ሆነው አይገኙም። ሃብታሞቹ አገሮች የድሃ-ድሃ ከሚባሉት ታዳጊ አገሮች የሚገቡ ምርቶችን ከኮታና ከቀረጥ ነጻ ከማድረግ ባሻገር ሰፋ ላለ ዕርምጃ ፈቃደኛ አይሆኑም። ዋናው አከራካሪ ጉዳይ የኢንዱስትሪው ዓለም የእርሻ የውጭ ንግድ ድጎማም ከ 2013 በፊት እንደማይወገድ ግልጽ ያደረጉት በዚሁ ጊዜ ነበር።

የሃብታሞቹ መንግሥታት አቋም በተለይም በተፋጠነ ዕድገት እየተራመዱ ባሉት ብራዚልንና ሕንድን በመሳሰሉት የደቡቡ ዓለም አገሮች ዘንድ ብርቱ ተቃውሞን ማስከተሉ አልቀረም። ለዚህም ነበር ባለፈው 2006 ዓ.ም. የጀኔቫው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር ለመሰናከል የበቃው። የድርጅቱ ሃላፊ ፓስካል ላሚይ ታላቅ ዕድል አመለጠ ሲሉ ንግግሩ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን በቁጭት ከመናገር ሌላ ምርጫ አላገኙም። ይህ የሆነው ልክ የዛሬ ዓመት ነበር። አሁንስ፤ አስታራቂ ተብሎ የቀረበው አዲስ ሃሣብ ጭብጥ ለሆነ ግብ መንገድ ቀዳጅነቱ ምን ያህል ነው?

የእርሻ ድጎማን ቅነሣ በተመለከተና ለድርድሩ መጓተት ከደቡቡ ዓለም ብቻ ሣይሆን ከአውሮፓ ሕብረት አኳያ ጭምር ስትወቀስ በቆየችው በዩ.ኤስ.አሜሪካ የፕሬዚደንት ቡሽ የመደራደር የብሄራዊ ሸንጎ ሥልጣን በቅርቡ አክትማል። ይህ ደግሞ የአገሪቱን ገበያ ገዳቢዎች ማጠናከሩ አልቀረም። እንግዲህ በወቅቱ የዶሃውን ድርድር መልሶ ሕያው ለማድረግ ጄኔቫ ላይ ንግግር የተያዘው በዚህ የአሜሪካ ፖሊሲ በትክክል ወዴት ሊያመራ እንደሚችል በግልጽ በማይታወቅበት ሁኔታ ነው።
እርግጥ በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ በወቅቱ ንግግር በተያዘበት አዲስ ሃሣብ መሠረት አሜሪካ በያመቱ ለገበሬዎቿ የምትሰጠው የእርሻ ድጎማ በአማካይ እስካሁን ካለው ከ 22 ሚሊያርድ ወደ 15 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ማቆልቆል ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ለታዳጊዎቹ አገሮች በቂ አይደለም። ድጎማው ወደ 11 ሚሊያርድ ዶላር ማቆልቆል ይኖርበታል ባዮች ናቸው። ከአውሮፓ ሕብረት አኳያም የንግድ ፉክክር አፋላሽ የሆነው ድጎማ ወደ 28 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ዝቅ እንዲል ይጠይቃሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ከታዳጊ አገሮች በሚገቡ የእርሻ ምርቶች ላይ የጣሉትን ቀረጥ በግማሽ መቀነስ ይጠበቅባቸዋል። ጥያቄው ይህ ይሣካል ወይ ነው። በሌላ በኩል የጀርመኑ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ሚሻኤል ግሎስ የታዳጊው ዓለም ጥያቄዎች አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ከሚያሳዩት ዝግጁነት ብዙም የተራራቁ አይደሉም ባይ ናቸው። ይህም እንደርሳችው አነጋገር ጭብጥ ምክንያት አለው። በጀርመኑ ባለሥልጣን አባባል በሁሉም ተሳታፊዎች ላይ ያለው ግፊት፤ ከአንድ ውጤት መደረሱ ግድ የመሆኑም ግንዛቤ እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው።

ይሁን እንጂ የግፊቱም ሆነ የግንዛቤው መጠናከር ብቻውን ለስኬት ዋስትና ሊሆን አይችልም። በኢንዱስትሪው ዓለም ለዶሃው ድርድር ዙር መክሸፍ ዓቢይ አስተዋጽኦ ያደረገው የእርሻ ድጎማው ፖሊሲ ደጋፊዎች ድምጽ በአሜሪካ ብቻ ሣይሆን በአውሮፓም ጨርሶ የተሰወረ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል ወግ-አጥባቂው የፈረንሣይ ፕሬዚደንት ኒኮላይ ሣርኮዚይ የአገራቸውን ገበሬዎች ጥቅም ከታዳጊው ዓለም ፉክክር ለመጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን እንደ ቀደምታቸው ሁሉ በቅርቡ አመልክተዋል። ይህም ሆኖ ግን የጀርመኑ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር አስታራቂ መፍትሄ ይገኛል የሚል ተሥፋ ከጣሉት መካከል አንዱ ናቸው። እንደርሳቸው ከሆነ መሰናክል ፈጣሪዎቹ የሚገኙት አውሮፓ ውስጥ ብቻ አይደለም።

እርግጥ የዓለም ንግድ ለሁለቱም ወገን የበጎ አድራጎት ትዕይንት አይደለም። ሁሉም የድርድሩ ተሳታፊዎች ለየራሳቸው ጥቅም መቆማቸው፤ የራሳቸውን ግብ ማውጠንጠናቸው ግልጽ ነው። ሃቁ ይህ በመሆኑም በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትም በታዳጊዎቹ አገሮች አቅጣጫ የሚሰነዝሯቸው ጥያቄዎች አሏቸው። ለምሳሌ ታዳጊዎቹ አገሮች እስካሁን ካለው በበለጠ ሁኔታ ገበዮቻቸውን ለኢንዱስትሪ ምርቶችና አገልግሉቶች ሰጭ ዘርፎች እንዲከፍቱ ይጠይቃሉ።

በሌላ በኩል በልማት ራመድ ያሉት ብራዚልን፣ ደቡብ አፍሪቃንና ሕንድን የመሳሰሉት የታዳጊው ዓለም አገሮች በፊናቸው የወጣት ኢንዱስትሪዎቻችውን ጥቅም ከሃብታሞቹ አገሮች ፉክክር ለመጠበቅ መፈለጋቸው ግልጽ ነው። ሆኖም ግን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሃብታም አገሮች የአርሻ ምርት ገበዮቻቸውን በሰፊው ከከፈቱና ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡትን ድጎማ በሚገባ ከቀነሱ በአስታራቂ መፍትሄ ለመስማማት ዝግጁ መሆናቸውን ማመላከታቸው አልቀረም። የገበያውን መከፈት በተመለከተ የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ከአሁኑ የሚታየውን የአውሮፓ ገበሬዎች ማሕበር ብርቱ ተቃውሞ ማሸነፍ ይኖርበታል።

የገበሬው ማሕበር ገበያው ከተከፈተ በያመቱ ተጨማሪ 500 ሺህ ቶን የበሬና አንድ ሚሊዮን ቶን የአሣማ ሥጋ ሊገባ እንደሚችል፤ ይህም ዋጋ ማጣጣልና የገበሬው ገቢ ማቆልቆል እንደሚሆን ነው የሚያስጠነቅቀው። ይህ ሁሉ በወቅቱ ጀኔቫ ላይ በተያዘው ንግግር ጠረጴዛ ላይ ቀርቦ ይገኛል። የሕብረቱን 27 ዓባል መንግሥታት ወክለው በጉባዔው የሚሳተፉት የአውሮፓ ኮሚሢዮን የንግድ ኮሜሣር ፔተር ማንደልሶን ቀላል ሥራ አይጠብቃቸውም።
የሆነው ሆኖ የዶሃው የድርድር ዙር ከሽፎ እንዳይቀር፤ ሁሉንም ወገን የሚያግባባ አስታራቂ መፍትሄ እንዲገኝ ፍላጎታቸው ጠንካራ ነው። እርግጥ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ የጋራ ውሣኔ ማስፈን ቀላል ነገር አይደለም። የድርጅቱ ውሣኔ በአንድ ድምጽ ካልሆነ ሊሰፍን ወይም ሊጸና አይችልም። ማንደልሶን እንዳስረዱት ይህ ደግሞ እጅግ አስቸጋሪና ጊዜን የሚፈጅ ጉዳይ ነው። “ችግሩ እያንዳንዱ ዓባል አገር እኩል መብት ያለው መሆኑ ላይ ነው። መንግሥታቱ ትልቅ ይሁኑ ትንሽ፤ ሃያል ሆኑ ደካማ፤ ድሃ ወይም ሃብታም ውሣኔን የማጽደቅም ሆነ የመቃወም እኩል መብት ነው ያላቸው። በጥቅሉ ግን ትችት መኖሩ አይቅር እንጂ የዓለም ንግድ ድርጅት የውሣኔ ሂደት ዴሞክራሲያዊ ነው” ብለዋል።

በአጠቃላይ የዶሃው ድርድር ዙር ተሰናክሎ መቀጠል በአማካይም ሆነ በረጅም ጊዜ በተለይ ለታዳጊው ዓለም ነው ጎጂ የሚሆነው። የድርድሩ ፍሬ አጥቶ መጓተት ዓለምአቀፉን የንግድ ሥርዓት ከማዳከም ባሻገር ከአሁኑ እንደሚታየው መንግሥታት በተናጠል የሚያደርጉት የሁለት ወገን ስምምነት እንዲዳብር ነው የሚያደርገው። በአንጻሩ በዓለም ንግድ ድርጅት ጥላ ሥር የሚደረግ ስምምነት መላውን ዓባል ሃገራት የሚጠቅም ሲሆን የሁለት ወገኑ ባይላተራል ሂደት ግን ትንንሾቹን አገሮች ለታላላቆቹ ተጽዕኖ የሚያጋልጥ ነው የሚሆነው። የኋለኞቹ ፍላጎታቸውን የማራማድ አቅም አይኖራቸውም። በተረፈ የሰሞኑ የጀኔቫ ንግግር በዕውነት የዶሃውን ድርድር ለማነቃቃት መብቃቱን ከወዲሁ ከመተንበይ ሰንበት ብሎ መታዘቡ ይቀላል። እርግጥ ምርጫው ወደፊት መራመድ ብቻ ነው። ግን ዕርምጃው ወሣኝ ካልሆነ ብዙም ፍሬ አይኖረውም።