የዶሀ የአየር ንብረት ጉባኤ | ጤና እና አካባቢ | DW | 04.12.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የዶሀ የአየር ንብረት ጉባኤ

18ኛዉ የተመድ የአየር ንብረት ጉባኤ ዶሀ ቀጠር ላይ እየተካሄደ ነዉ። ወደ200 መቶ የተገመቱ ሀገሮች እንደተሳተፉበት በተነገረዉ ዓመት ቆጥሮ የመጣ ጉባኤ ላይ ግን በኢንዱስትሪ ያደጉት ሀገሮች ለአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ የሚታመነዉን የሙቀት አማቂ በካይ ጋዞች ልቀት በምን ያህል መጠን ለመቀነስ መዘጋጀታቸዉ አልተሰማበትም።

ለበርካታ ሰዎች ህዋ ዉስጥ ስለተከሰተ ሽንቁር አለያም ስለምድር ዋልታ አካባቢ የበረዶ ግግር መቅለጥ የሚያስከትለዉ መዘዝ እጅግ ርቆ የሚታሰብ ነዉ። ይህ የማይደረሰብት የሚመስል የሳይንቲስቶች ማሳሰቢያ ከእኛ የዕለት ተዕለት ህይወት በከፍተኛ ርቀት የሚታይ መሆኑን ያስተዋሉት የኢንዶኔዢያ የፊልም ባለሙያ የሀገራቸዉ አርሶ አደሮች የሚገኙበትን የአካባቢ ተፈጥሮ ዉጥንቅጥ የሚያሳይ ፊልም ይዘዉ ቀርበዋል፤ ቀጠር ላይ ለ18ኛዉ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ ተሳታፊዎች። ሻላሁዲን ሲርጋር (The Land Beneath the Fog) ማለትም ከጭጋግ ስር ያለዉ መሬት በተሰኘዉ ፊልም፤ ጃቫ ዉስጥ በምትገኘዉ ጌኒካን በተሰኘች መንደር የሚኖሩ የሁለት ገበሬዎችንየዕለት ከዕለት ህይወት በዚህ አሉታዊ ተፅዕኖ ምን ያህል እንደተቃወሰ ለማሳየት ይሞክራሉ። ገበሬዎቹ በሚኖሩበት አካባቢ የአየር ንብረት ለዉጥ የትኛዉን የእህል አይነት መቼ መዝራት ወይም መትከል እንደሚቻል ማወቅ ከማይቻልበት ደረጃ አድርሶታል። በኢንዶኔዢያ የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ልጆች እንደእድሜ አቻዎቻቸዉ ትምህርት ቤት የመሄድና ትምህርታቸዉን የመቀጠል እድላቸዉ ተሰናክሏል፤ ሰብል በወቅቱ ስለማይደርስ፤ እንዲሁም ስለሚጨናገፍ የቤተሰቦቻቸዉ ገቢ በመመናመኑ ሊከፍሉላቸዉ አይችሉምና።

ሶስትዓመታትን ፊልሙን ለመቅረፅ ሲሉ የገበሬዎቹን ዕለታዊ ኑሮ የተከታተሉት ሲርጋር እንደሚሉትም ከእርሻ ምርት በሚገኙት ገቢ ኑሯቸዉን ለመምራት ያዳገታቸዉ አርሶ አደሮች፤ ወደአቅራቢያቸዉ ወደሚገኙ ከተሞች በመፍለስ በየግንባታ ስፍራዉ ተቀጥረዉ በመስራት ቤተሰባቸዉን ለመደጎም ተገደዋል። የግሪን ፒስ የተሰኘዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ ማርቲን ቤከር ደግሞ በዚች ሀገር ዉስጥ በአየር ንብረት ለዉጥ ክፉና የተጎዱት አነስተኛ ገበሬዎች፤ ዓሣ አጥማጆች፤ ኑሯቸዉ ከደን ጋ የተቆራኘ ወገኖች፤ የሀገሬዉ ነባር ጎሳዎች፤ ሴቶችና ሕፃናት ናቸዉ።  የደን መራቆት፤ ጎርፍ፤ የመሬት መንሸራተት፤ የአየሩ እና የዉሃዉ ጥራት መበላሸት እነዚህን ወገኖች ኑሮ አዳጋች አድርገዉታል። በተቃራኒዉ ታዲያ የኢንዶኔዢያ መንግስት ለትላልቅ ኩባንያዎች በሚሰጠዉ ድጋፍ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሃብቶች ለችግር አጋልጧል ሲሉ ግሪን ፒስም ሆነ ሌሎች የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ይወቅሳሉ። የፊልም ባለሙያዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚደርሰዉን ጉዳት በማሳያ ለማስረዳት ያደረጉት ጥረት ምን ያህል ተሳክቶ እንደሆነ የሚታየዉ ወደ200 መንግስታትን የወከሉ፤ እንዲሁም የኃይልና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተገኙበት የዶሀዉ ጉባኤ ዉጤት ይሆናል። ሳምንቱን ሙሉ የወጡ ዘገባዎች የትንትናዎቹን ጨምሮ ማለት ነዉ ግን የጠቆሙት አዎንታዊ ነገር የለም። ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ዕለት የተመድ እንዳሳሰበዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ፍጥነትን ለመቀነስ ከጉባኤዉ ተሳታፊዎች ፈጣን ምላሽ ይጠበቃል።

ይልቁንም የዓለም የኤኮኖሚ እድገት ፍጥነቱ መቀነሱ ነዉ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረታቸዉን የሳበዉ። ክርስቲያና ፊጎርስ የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ ዋና ፀሐፊ ከዶሀዉ ጉባኤ የሚጠበቀዉን መጠነኛ ዉጤት በማመላከት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሹ ቢያመለክቱም፤ ባለ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ባለቤቶቹ ሀገሮች የበካይ ጋዞችን በዚህ መጠን ለመቀነስ ተነስተናል የሚል ምንም አዲስ ፍንጭ አልሰጡም። ዋና ፀሐፊዋ ቢቸግራቸዉ ይመስላል የየሀገራቱ ህዝብ እንዲሁም የንግዱ ዘርፍ አባላት መንግስታት የዓለም አየር ሙቀትን የሚያባብሱ ጋዞችን ለመቀነስ ቆራጥ ርምጃ እንዲወስዱ እንዲያደርጉ ጥሪ ያስተላለፉት።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic