1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድጂታል ወያነ እንቅስቃሴ ወዴት ይወግናል?

ዓርብ፣ መስከረም 2 2012

'ድጂታል ወያነ' የትግራይ ወጣቶች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። የእንቅስቃሴው ተሳታፊዎች ዘመቻቸው በዋነኛነት ከፓርቲ ፖለቲካ ነፃ በሆነ መንገድ ትግራይን ማእከል ባደረገ መልኩ የሚካሄደ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ እንቅስቃሴ ይሉታል። በሌላ በኩል የአንድ ፓርቲ የማሕበራዊ ሚድያ ክንፍ በማለት የሚወቅሱትም አልጠፉም፡፡

https://p.dw.com/p/3PZKD
Äthiopien Stadtansicht Mekele
ምስል DW/M. Hailessilasie

ድጂታል ወያነ በአብዛኛው ወጣቶች የሚሳተፉበት የማኅበራዊ ድረ-ገፆች እንቅስቃሴ ነው

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፅእኖው እያየለ የመጣው በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በኩል የሚደረገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በርካታ ወጣቶች የሚያሳትፍ ነው፡፡ ይኽ እንቅስቃሴ በአብዛኛው በተናጠል ሌላ ግዜ በመደበኛና ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ፈጥሮ ይፈፀማል፡፡

'ዲጂታል ወያነ' የትግራይ ወጣቶች በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ መደበኛ ያልሆነ አደረጃጀት ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ፈጥሮ የሚደረግ ዘመቻ መሆኑ የሚነገርለት ይህ 'ዲጂታል ወያነ' የሚል ስያሜ የተሰጠው እንቅስቃሴ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ይሳተፉበታል፡፡

በዚህ ዙርያ ከሚንቀሳቀሱ መካከል አንዱ የሆነው ሀፍቶም በርሀ 'ዲጂታል ወያነ' በተመረጡ አጀንዳዎች ዙርያ ተጋሩ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች የሳይበር የሚያደርጉት የጋራ ዘመቻ ነው ይለዋል፡፡

በእንቅስቃሴው የክልሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳዮይ ዙርያ ውይይት ይደረግበታል፣ ትግራይ ላይ ያነጣጠሩ ያልዋቸው የሀሰት ወሬዎችና ዘመቻዎች መልስ ይሰጣል፣ መረጃ የማቀበል ስራ ይከወንበታል፣ አጀንዳዎች እየቀረፁ ይመከርበታል፡፡

ለዚህ መደበኛ ያልሆነ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አደረጃጀት ስያሜ የወጣለት በትግራይ ክልል ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣናት መሆኑ ይነገራል፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከወራት በፊት በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት የትግራይ ወጣቶች የማሕበራዊ ሚድያ እንቅስቃሴ ካደነቁ በኋላ እንቅስቃሴው 'ዲጂታል ወያነ' ወይም 'ዲጂታል ትግል' ማለት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይኽ ዲጂታል ወያነ የሚል መጠርያ የተሰጠው የማሕበራዊ ሚድያ እንቅስቃሴ ከትግራይ ክልል መንግስትና ህወሓት ጋር አያይዘው የሚያነሱትም አልጠፉም፡፡ የዓረና ህዝብ ግንኙነት ሐላፊ አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ 'ዲጂታል ወያነ' የተባለው እንቅስቃሴ የህወሓትና ትግራይ ክልል መንግስት ባለስልጣናት አጀንዳ ቀርፀው በጀትና የሰው ሐይል መድበው የሚያካሂዱት ዘመቻ ይለዋል፡፡

በሌላ በኩል ይህንኑ እንቅስቃሴ ከፓርቲ ይሁን መንግስት ጋር ግንኙነት የለውም በማለት የእንቅስቃሴው አካል መሆኑ የሚገልፅ 'ልፍዓተይ ተስፋ' ተብሎ የሚታወቅ ፀሐፊ ይናገራል፡፡ ትክክለኛ ስሙ መግለፅ ያልፈለገው በፌስቡክ 'ልፍዓተይ ተስፋ' በሚል የሚታወቀው ፀሐፊ እንደሚለው ዲጂታል ወያነ ከየትኛውም የፖለቲካ ሐይል ወገንተኝነት የራቀ ኢ- መደበኛ የማሕበራዊ ሚድያ አደረጃጀት መሆኑ ይሞግታል፡፡

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

እሸቴ በቀለ