የድንበር ቁጥጥር እና የንግዱ እንቅስቃሴ መቀዝቀዝ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 28.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የድንበር ቁጥጥር እና የንግዱ እንቅስቃሴ መቀዝቀዝ

ጀርመንና ኦስትርያን በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ የምትገኘው ደቡብ ጀርመናዊቷ የባየር ፌዴራዊው ግዛት የፍራይላሲንግ ከተማ ለብዙ ዓመታት በሸንገን ነፃ የቪዛ ዝውውር ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

የስደተኞች መብዛት እና መዘዙ

ይሁንና፣ ወደ ምዕራብ አውሮጳ የሚመጣው የስደተኞች ቁጥር ባለፉት ጊዚያት እጅግ ከጨመረ ወዲህ፣ በዚሁ ድንበር ላይ ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ የቪዛ ቁጥጥሩን እንደገና አስተዋውቀዋል። ይህ ርምጃም በፍራይላሲንግ ከተማ ላይ አሳሳቢ መዘዝ አስከትሎ፣ የከተማይቱ የንግድ እንቅስቃሴ ተንኮታኩቶዋል።


በትንሿ የባየር ፌዴራዊው ግዛት ከተማ «ፍራይላሲንግ» የሚኖሩት ሬጊና ፒኽለር በቀላሉ የሚደናገጡ ሰው አይደሉም፣ በቤተሰባቸው የተክል ቦታ የሚመረተውን አትክልት በመሸጡ ተግባር በመሰማራት ሕይወታቸውን ይመራሉ፣ እስከቅርብ ጊዜ በፊትም ድረስ ገበያቸው ጥሩ ነበር የሚካሄደው። ባለፉት ሳምንታት ግን በ50ኛዎቹ ዓመታት መጨረሻ የሚገኙት ፒኽለር ገበያው በመቀዛቀዙ ስጋት አድሮባቸዋል። ሁኔታዎች እንዲህ እንዳሁኑ ተበላሽተው እንደማያውቅ ነው የሚናገሩት።

Freilassing Familie Pichler

ሬጊና ፒልኸር እና ቤተሰባቸው

« በአሁኑ ጊዜ ለመሸመት የሚመጡት የኦስትርያ ዜጎች በጣም ጥቂት ናቸው። ስለዚህ ገቢያችን ከግማሽ በላይ ዝቅ ብሎዋል። »

ለገበያው መቀዛቀዝ ተጠያቂው በጀርመን እና በኦስትርያ መካከል እንደገና ስራ ላይ የዋለው የድንበር ቁጥጥር እና በሰበቡ የተከተለው መዘዝ ነው። ባለፈው መስከረም ወር ብቻ 225,000 ስደተኞች ጀርመን ሲገቡ፣ ከነዚህም ብዙዎቹ ጀርመንን ከኦስትርያ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ በምትገኘው 15,000 ገደማ ነዋሪ ባላት የፍራይላሲንግ ከተማ በኩል ነው። እና በየሳምንቱ መጨረሻ ወደ ከተማይቱ በአማካይ እስከ 15,000 ስደተኛ የሚገባበት ሁኔታ ከከተማይቱ አቅም በላይ በመሆኑ፣ ጀርመናውያኑ የከተማይቱ ባለስልጣናት ከፌዴራዊው መንግሥት ርዳታ መጠየቅ ነበረባቸው፣ ጥቂት ቆይቶም ከባየር አስተዳደር ግፊት ያረፈባቸው የጀርመን ሃገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዝየር ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ገደማ ጠንካራ ርምጃ በመውሰድ ከኦስትርያ ጋር በሚያዋስነው የሃገራቸው ድንበር ላይ የቁጥጥሩን ስራ እንደገና አስተዋውቀዋል።


Bildergalerie Flüchtlingsdrama in Freilassing

የቪዛ ቁጥጥር

የዚሁ ድንበር ቁጥጥር ዓላማ ወደ ጀርመን በመጉረፍ ላይ ያለውን ስደተኛ መመዝገብ እና በመላይቱ ሃገር በሚገኙ የመቀበያ ጣቢያዎች ማከፋፈል የሚቻልበትን ድርጊት በተግባር ላይ ማዋል ነው። ይኸው ቁጥጥር ግን ባካባቢው ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከባድ መዘዝ ነው ያስከተለው። ከድንበሩ ቁጥጥር በፊት በፍራይላሲንግ እና በኦስትርያ የዛልስቡርግ ከተማ መካካል በየአስር ደቂቃው፣ በጥድፊያው ሰዓት ላይ ደግሞ ከዛ ባነሰ የጊዜ ልዩነት ነበር የሐዝብ ማመላለሻ ባቡሮች የሚጓጓዙት። ዛሬ ያ የባቡር ግንኙነት ተቋርጦዋል፣ መቼ እንደገና እንደሚጀመርም አይታወቅም። ከዚህ ሌላም በፈጣኑ አውራ ጎዳና ላይ ተጠናክሮ በቀጠለው የቪዛ ቁጥጥር የተነሳ የትራፊኩ መጨናነቅ ተጨማሪ ችግር ማስከተሉን ስጋት ያደረባቸው የልብስ መሸጫ ሱቅ ያላቸው ነጋዴዋ ወይዘሮ አንከ ዴምሪኽ ገልጸዋል።

« በድንበሩ ቁጥጥር የተነሳ ወደ ሱቃችን የሚመጣው የደንበኛ ቁጥር በአንድ ሶስተኛ ቀንሶዋል። ይህም ትልቅ ክስረት አስከትሎዋል። ለነገሩ የዛልስቡርግ ደንበኞች አስተማማኝ ደንበኞች ናቸው፣ የምንኖረው በነሱ ነው። »

Freilassing Anke Demmrich

አንከ ዴምሪኽ

በድንበሩ ቁጥጥር እንደገና ስራ ላይ በዋለበት ደንብ ሰበብ ያካባቢው ገቢ በርግጥ እንደቀነሰ የፍራይላሲንግ የኤኮኖሚ መድረክ ባልደረባ ቶማስ ሻይድም አረጋግጠዋል። ለዚህ ግን የድንበሩ ቁጥጥር ብቻውን ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ አይደለም። ያካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ የመገናኛ ብዙኃንም በከፊል ተጠያቂ ናቸው። የስደተኞቹ ጎርፍ ባካባቢው ትልቅ ቀውስ አስከትሎዋል እያሉ ሁኔታውን እያባባሱ እንደሚዘግቡ እና ደንበኞችን እንደሚያስደነግጡ ነው ነጋዴዋ አንከ ዴምሪኽ እና ሬጊና ፒልኸር የሚናገሩት። ምንም እንኳን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ፍራይላሲንግ ከተማ ቢገቡም፣ ያካባቢው ነዋሪ ከከተማይቱ አስተዳደር ጋር በሚያደርገው ትብብር እና በሚሰጠው አገልግሎት፣ ችግር የተፈራው ቀውስ እንዳይፈጠር ድርሻ ማበርከቱን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ አባል ቤርንሃርት ሲመርማን አስረድተዋል።

« የከተማይቱ ሁኔታ አንድም ቀውስ አይታይበትም። በቅጡ የተደራጀ ነው። ፖሊስ፣ ግብረ ሠናዮቹ ድርጅቶች ካሪታስ እና ቀይ መሥቀል፣ እንዲሁም፣ ለመርዳት የተዘጋጁ በጎ አድራጊዎች ባንድነት በጥሩ የትብብር መንፈሥ እየሰሩ ነው። »

ዳንየል ሀይንሪኽ
አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic