1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሮን ጥቃት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 21 2017

“ በአጠቃላይ ወታደራዊ ድሮኖች ለአፍሪካ መንግስታት አማጽያንና አሸባሪዎችን ለማጥቃት ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸዋል” ሚስተር ዊም ዝዌንበርግ መንግስታዊ ያልሆነውና በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ፓክስ (PAX) የተስኘው የዳች የሰላም ድርጅት ተመራማሪ

https://p.dw.com/p/4nbQA
Ukraine Kramatorsk 2024 | Ukrainisches Militär trainiert mit VTOL-Drohnenprototyp nahe der Front
ምስል Andre Luis Alves/Anadolu/picture alliance

የድሮን ጥቃት በስቪሎች ላይ


በኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሴሜናዊው የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት፤ ባአሁኑ ወቅት ደግሞ በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎችና በኦሮሚያ ክልል  መንግስት ኦነግ ሸኔ ብሎ ከሚጠራው የኦኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶችና ጦርነቶች፤ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች በጥቅም ላይ እንደዋሉና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ በሰፊው ይነገራል። በአሁኑ ወቅት መንግስታት ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖችም ድሮኖችን እንደሚጠቀሙ የሚገለጽ ሲሆን ይህም የዘመኑን ጦርነት በእጅጉ እንደቀየረው ነው የሚነገረው።
እያደገ የሄደው የድሮን ፍላጎት
ዲደብሊው የድሮን ቴክኖሎጂ በዘመናችን  የሚካሄዱ ጦርነቶችን ምን ያህል እየለወጣቸው እንደሆነና በኢትዮጵያም በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተካሄዱ ባሉ  ጦርነቶችና ግጭቶች ምን ያህል በስራ ላይ እንደዋሉ እንዲያስረዱት ሚስተር ዊም ዝዌየንበርግን በስልክ አነጋግሯል። ሚስተር ዊም ዝዌንበርግ  መንግስታዊ ያልሆነውና በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ፓክስ (PAX) የተስኘው የዳች የሰላም ድርጅት ተመራማሪ ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያና በሌሎችም የአፍርካ አገሮች በጥቅም ላይ የሚውሉ ድሮኖችን በማጋለጥ  ይታወቃሉ። ። በአፍሪካ፤ በሊቢያ፤ ማሊ፤ ኒጀር፤ ናይጀሪያና በሌሎችም አገሮች ለወታደራዊ ጥቃት እንደሚውሉ የተናገሩት  ሚስተር ዊም፤ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ድሮኖችን ለወታደራዊ ኢላማ እየተጠቀመች እንደሆነ አስረድተዋል። የድሮን ቴክኖሎጂ፤ መንግስታት አማጺያንን ለመዋጋት አመቺና ቀላል ዘዴ እንደሆነላቸው  ሲገልጹም፤ “ በአጠቃላይ ወታደራዊ ድሮኖች ለአፍሪካ መንግስታት አማጽያንና አሸባሪዎችን ለማጥቃት ትልቅ አቅም ፈጥሮላቸዋል” በማለት ይህም ድሮኖች ለረጅም ሰአታት በሰማይ ሊበሩ ስለሚችሉና መረጃዎችንን የሚያሰባስቡና ኢላማዎችን የሚያሳዩ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙላቸው በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአፍሪካ፤ በሊቢያ፤ ማሊ፤ ኒጀር፤ ናይጀሪያና በሌሎችም አገሮች ለወታደራዊ ጥቃት እንደሚውሉ
በአፍሪካ፤ በሊቢያ፤ ማሊ፤ ኒጀር፤ ናይጀሪያና በሌሎችም አገሮች ለወታደራዊ ጥቃት እንደሚውሉምስል Diego Herrera Carcedo/Anadolu/picture alliance


የኢትዮጵያ መንግስት ተጠቅሞባቸዋል የሚባሉት ድሮኖች
በኢትዮጵያ፤ በስሜን የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት በጥቅም ላይ የዋሉድሮችንና ያስከተሉትን ጉዳት ያጋላጡ መሆኑን በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅትም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተፈጸሙ ነው ስለሚባሉት ጥቃቶች አስተያየታቸውን ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ በአማራ ክልል በጥቅም ላይ የዋሉት ድሮኖች የቱርክና ኢራን ሰራሽ ናቸው” በማለት  በአካባቢው ዘልቆ ምርመራ ለማድረግ የማይቻል በመሆኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፤ ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎች ግን መኖራቸውን ተናግረዋል።
ድሮኖች ኢላማቸውን ሊስቱ የሚችሉባቸው ምክኒያቶች
ሚስተር ዊም ድሮኖች ምንም እንኳ ካሜራ የተገጠመላቸውና ኢላማ ጠቋሚ መሳሪያዎችም ያሏቸው ቢሆንም፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ግን ተደጋግሞ የታየ መሆኑን በመጥቀስ፤ ሰው አልባ መሆናቸው፤ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ የተሳሳተ የመረጃ ንባብና የፓይለቶች ስልጠና ወይም አቅም ማነስ ለሚፈጠሩ ስህተቶችና ለሚደርሱ ጉዳቶች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የድሮኖች አጠቃቀምና ዝውውር ህግ ሊበጅለት የሚገባ ስለመሆኑ
 በአሁኑ ወቅት መንግስታት ወታደራዊ ድሮኖችን እንዳይታጠቁ ማድረግ ባይቻልም የድሮኖችን ዝውውርና አጠቃቀምን በሚመለክት ግን ህግና አሰራር  ሊበጅለት የሚገባ መሆኑንም ሚስተር ዊም አሳስበዋል።
 
በድሮኖች የመተማመን ዝንባሌ አደጋ
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግስታት ድሮንን ተቃሚዎቻቸውን ማጥፊያና  ችግሮቻቸውን መፍቻ አድርገው የመውሰድ አዝማሚያ እያሳዩ መሆኑንም  ሚስተር ዊም ጠቁመዋል፤ “ ድሮን ጠላትን አድኖ ለመምታትና ጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል ሊመስል ይችላል፤ ግን ግጭቶች እንዲራዘሙ ነው የሚያደርገው” በማለት የግጭቶች መፍቻ ምንግዜም ለግጭት ምክንያት  የሆኑትን ችግሮች ማወቅና መፍታት እንጂ ሀይል አለመሆኑን በማስገንዘብ፤ በሌላውም ወገን  ቢሆን የመሳሪያ ሀይል የፍላጎት ማስፈጸሚያ ሊሆን እንደማይገባና እንደማይቻልም ተመልክቷል።
ገበያው ንጉሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር