የድሬስደን ድብደባ 70ኛ ዓመት | ዓለም | DW | 13.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የድሬስደን ድብደባ 70ኛ ዓመት

የብሪታኒያና የዩናይትድ ስቴትስ የጦር አውሮፕላኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የምስራቅ ጀርመንዋን የድሬስደን ከተማ እንዳልነበረች ያደረጉበት የቦምብ ድብደባ ልክ ዛሬ 70 ዓመት ደፍኗል ።በአየር ድብደባው 25 ሺህ ሰዎች እንደሞቱ ሲገመት አብዛኛዎቹ የከተማዋ ውብ ህንፃዎችና የስነ ጥበብ ቅርሶችም ወድመዋል ።

የድሬስደኑ ድበደባ ከዚያን ጊዜው የብምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎች በተገኙበት በከተማዋ ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዛሬ በተካሄደ ስነ ስርዓት ታስቧል ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተለያዩ የጀርመን ከተሞች በተባባሩት ተጓዳኝ ኃይሎች የጦር አውሮፕላኖች ሲደበደቡ ውብ ህንፃዎች ያሏት ታሪካዊቷ ድሬስደን ይህ ዓይነቱ እጣ ይገጥማትል የሚል ግምት አልነበረም ። ሆኖም የያኔው የናዚ ጀርመን መሪ አዶልፍ ሂተለር በአውሮፓ ባስፋፋው ጦርነት ሰበብ ልክ የዛሬ 70 ዓመት ድሬስደን ጦስ ሆነች ። እ.ጎ.አ የካቲት 13 ፣1945 ላንካስተር የተባሉት የብሪታኒያዎቹ ባለ 4 ሞተሮች ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከእንግሊዝ በመነሳት ዒላማችው ወደ ሆነችው ወደ ድሬስደን አቀኑ ።ከጠዋቱ 2:39 ሲል የከተማዋ የማስጠንቀቂያ ጥሬ አስተጋባ ። ብዙም ሳይቆይ አውሮፕላኖቹ በከተማዋ ቦምብ ያዘንቡ ጀመር ።በ23 ደቂቃዎች ተከታታይ ጥቃት ወደ 3ሺህ በሚሆኑ ከባድ ፍንዳታን በሚያስከትሉ ና

ከ400 ሺህ በላይ በሚሆኑ ተቀጣጣይ ቦምቦች ነበር ድሬስደን የተደበደበችው ።በአየር ድብደባው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 70 ሺህ አለያም 35 ሺህ ይሆናሉ የሚሉ የተለያዩ ግምቶች ነበሩ ። በመጨረሻ የድሬስደን ከተማ ምክር ቤት እ.ጎ.አ በ 2004 ያቋቋመው ኮሚሽን በቦምብ ድብደባው ህይወታቸው የጠፋው ሰዎች ቁጥር 25 ሺህ መሆኑን አስታውቋል ።ከያኔው ድብደባ በህይወት የተረፉ አንዲት ሴት የህዝቡን ሰቆቃና ጭንቀት ያስታውሳሉ ።
«ከምድር ቤት መውጣት አልቻልንም ። የነበርነበት ቦታ ጥሩ ቦታ አልነበረም ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ለደህንነት መሬት ላይ መተኛት ነበር የሚመከረው ።እናቴ እኔን ከልላ ከኔ በላይ ነበረች ።ሰዉ በፍርሃት ራደ ።አንዳንዱ ይፀልያል ፤አንዳንዱ ይዘምራል ፤ አንዳንዱ ይጮሃል አንዳንዱ ደግሞ ትንፍሽ አይልም ።»
በዚህ ጭንቀት ውስጥ ሆነው ከቦምብ ድብዳባው ራሳቸውን ለማዳን የሞከሩት የነዚህ ሰዎች መጨረሻ ግን አሳዛኝ ነበር ። ከመካከላቸው በህይወት የተሩፉት ዛሬ ታሪኩን የሚያወጉት ሴት ብቻ ነበሩ ።
« እኔ ጥሩ እድል ነበር የገጠመኝ ። ሁላችንም በሌሎች ቤቶች ውስጥ የሚኖሩትም ምድር ቤት ውስጥ ነበርን ። በአጠቃላይ 13 ሲሞቱ አንድ ሰው ብቻ በህይወት ተረፈ ። እርስዋም እኔ ነኝ »

በኢጣልያዋ ውብ ከተማ ፍሎረንስ አምሳያ «የኤልበዋ ፍሎረንስ» እየተባለች ትጠራ የነበረችው ድሬስደን በቦምብ ድብደባው ከመጠን በላይ ነው የጋየችው ። ለድብደባ የተሰማሩ የብሪታኒያ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ከ6700 ሜትር ከፍታ ከ320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተማዋ ስትነድ ይታያቸው ነበር ። ከከተማዋ 15 ካሬ ኪሎሜትር የሚሆነው ቦታ በድብደባው ዶግ አመድ ሆኖ ነበር ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የብሪታኒያና የአሜሪካን ጦር አውሮፕላን አብብራሪዎች የተሳተፉበት የቦምብ ዝናብ የፈጠረው እጅግ ከፍተኛ ሙቀት መስታወቶችን የሚያቀልጥ ነበር ።
«በኃይለኛው የእሳት ማዕበል ውስጥ ነበር የምንሄደው ። የአየር እጥረት ነበር ።ይህን መሰሉ ማዕበል እንዴት እንደሚከሰት አናውቅም ነበር ።ያኔ አየሩንም ጠላታችን ነበር ብለናል ።»
የያኔው የብሪታኒያ አየር ኃይል ማርሻል አርተር ሃሪስ በሰጡት ትዕዛዝ የተካሄደው የድሬስደን ድብደባ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በምዕራባውያን ኃያላንና በሶቭየት ህብረት መካከል የተካሄደ ወታደራዊ ትብብር ተደርጎ ይወሰዳል። በጎርጎሮሳዊው 1944 በምዕራብ ግንባር የተባበሩት ኃይሎች መንግሥታት የከፈቱት የማጥቃት ዘመቻ ከናዚ ጦር በኩል ጠንካራ ምከታ ሲገጥመው የሶቭየቱ ቀዩ ሠራዊት ግን በፍጥነት እየገሰገሰ ነበር ።እናም ተጓዳኞቹ ኃይሎች ድሬስደንን የደበደቡት ሞስኮን ለማስደሰት ብለው እንደሆነ ይነገራል ።በሌላ በኩል ቀደም ካለ ጊዜ አንስቶ ማዕከላዊ ጀርመን ለሶቭየት እንድትሰጥ አስቀድሞ ቃል ተገብቶ ነበር የሚሉም አሉ ።ምክንያቱ ይህም ይሁን ሃሪስ ግን በድሬስደን ላይ አይናቸውን ጥለው ነበር ። አስቀድሞም ቢሆን የእንግሊዝ ጋዜጦች እያንዳንዱ የጀርመን ከተሞች ሊደበደብ እንደሚችል ያስጠነቅቁ ነበር ።ድሬስደን ስትደበደብ የሶቭየቱ ቀዩ ጦር ከከተማይቱ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ የተካሄደው የድሬስደን ድብደባ እስካሁን ድረስ እንዳነጋገረ ነው ። ትዕዛዙን ያስተላለፉት ሃሪስ ማዕከላዊ ሎንዶን ውስጥ ሐውልት ቆሞላቸዋል ። ከዚያ የቦምብ ድብደባ የተረፉ 100 ያህል ሰዎች ዛሬ ድሬስደን ውስጥ ዕለቱን አስበዋል ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic