የድረ-ገፅ አምደኛው ከእስር በኋላ | ኢትዮጵያ | DW | 23.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የድረ-ገፅ አምደኛው ከእስር በኋላ

አቶ ስዩም እንደተናገሩት ወሊሶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩ ከ20 ቀናት በኋላ የወሊሶ ወረዳ ፍርድ ቤት የተያዙበት ጉዳይ ህዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳት እንደማያስከስሳቸው ወሰኖላቸው ነበር ።ይሁን እና ከዛ በኋላ ኪሳቸው ውስጥ በተገኘ ጽሁፍ ምክንያት ወደ ጦላይ እንዲወሰዱ ተደረገ ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:46
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:46 ደቂቃ

ከጦላይ የተለቀቁት የድረ-ገፅ ፀሀፊ

 
የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም ማብቂያ ላይ በደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተለያዩ የማቆያ ማዕከላት ካሰራቸው መካከል የተወሰኑትን በዚህ ሳምንት ለቋል ። የተሀድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው በዚህ ሳምንት ከተለቀቁት ውስጥ ፖለቲከኞች እና የድረ ገጽ አምደኞች ይገኙበታል ። ከመካከላቸው በጦላይ የማቆያ ማዕከል ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ታስረው ትናንት የተለቀቁት መምህር እና የድረ ገጽ አምደኛ አቶ ስዩም ተሾመ አንዱ ናቸው ። 
የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር አቶ ስዩም ተሾመ በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ በሚያወጧቸው መንግሥትን በሚተቹ ጽሁፎቻቸው ይታወቃሉ ። ከዚህ ሌላ ዶቸቬለን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን  በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሃሳቦቻቸውን ከሚያካፍሉ ምሁራን አንዱ ናቸው ።አቶ ስዩም  ከመታሰራቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ዶቼቬለ ባካሄደው ውይይት ላይ ተሳትፈው ነበር ። አቶ ስዩም እንደተናገሩት ወሊሶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩ ከ20 ቀናት በኋላ የወሊሶ ወረዳ ፍርድ ቤት የተያዙበት ጉዳይ ህዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳት እንደማያስከስሳቸው ወሰኖላቸው ነበር ።ይሁን እና ከዛ በኋላ ኪሳቸው ውስጥ በተገኘ ጽሁፍ ምክንያት ወደ ጦላይ እንዲወሰዱ ተደረገ ። ጽሁፉ ጦላይ ታይቶ እንደማያስጠይቃቸው ተረጋግጦ ወደ ተሀድሶ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል ። ሆኖም አቶ ስዩም በጦላይ በምርመራ ወቅት፣ ስቃይ እና በደሎች ደርሰውብኛል ይላሉ ። በጦላይ ቆይታቸው የተሀድሶ ስልጠናም ለወሰዱት ለአቶ ስዩም ፣ የምርመራው እና የሥልጠናው ሂደት በግልጽ የተለየ አልነበረም ። ከዚህ ሌላ በርሳቸው አስተያየት በስልጠናው ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብትን የሚጋፉ ትምሕርቶችም ነበሩ ። አቶ ስዩም ተሀድሶው ለተነሳው የነፃነት እና የመብት ጥያቄ መፍትሄ ይሆናል ብለው አያስቡም ።የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ካሰራቸዉ ከ12ሺሕ 500 ሰዎች መካከል አስር ሺሕ ያሕሉን ባለፈዉ ሮብ መልቀቁን አስታዉቋል።ሌሎች ቢያንስ ሰወስት የአምደ መረብ ፀሐፍት፤ የፖለካ አቀንቃኞችና ፖለቲከኞች መለቀቃቸዉ ተዘግቧልም።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ 
 

Audios and videos on the topic