1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድምፅ ብክለት ሕግ በአዲስ አበባ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 3 2016

በአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ ተቋማትና ከኢንዱስትሪዎች ከደረጃ በላይ የሚወጣውን የድምፅ ብክለት ለመቆጣጠር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እየተፈለገ መሆኑ ተገለጸ።

https://p.dw.com/p/4i76O
Äthiopien Addis Abeba Stadtansicht
መሀል አዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

የድምፅ ብክለት ሕግ በአዲስ አበባ

 የድምፅ ብክለቱ ልዩ ልዩ ችግሮችን አስከትሏል በመባሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተሰጠው ኃላፊነት የድምፅ ብክለቱን  ለመከላከል የሚያስችል ሕግ ወጥቶ እየሠራበት መሆኑን አመልክቷል። 

ከደረጃ በላይ የሚወጡ ድምፆችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚያካሂደው እንቅስቃሴ ባሻገር፣ በርካታ የሕዝብ አቤቱታ በጉዳዩ ላይ እየተቀበለ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አመለከተ። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ብዙ ሰዎች በድምፅ ብክለት መቸገራቸውን በባለሥልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር እየደወሉና በአካልም እየቀረቡ እሮሮአቸውን እንደሚያሰሙ ነው የተናገሩት። «ማኅበረሰቡ ማታ፣ ማታ ልንተኛ አልቻልንም።« «ቀን በሥራ የደከመውን አዕምሮአችንና በአጠቃላይ አካላችንን የምናሳርፍበት ቦታ ተቸግረናል።» በተለይ «መዝናኛና ጭፈራ ቤቶችና የእምነት ተቋማትን ተጎራብተን የምንገኝ ሰዎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገናል» ማለታቸውንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።  

«በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሃይማኖት ተቋማት በአደባባይ የማምለክ እና የማክበር ለዘመናት የቆየ ባህል አላቸው ፣ ማንም ሰው ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ መኖር እንዳለበት ሁሉ እንደ ሀዝብ ለማኅበረሰብ ትርጉም ያላቸው ክንዋኔዎችም አብረው በጥንቃቂ መታየት ይኖርባቸዋል»’ሲሉ  የሕግ ባለሙያው አቶ ካፒታል ክብሬ ለ DW ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥትና የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አዋጅ ቁጥር 229/2002 እና የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/2002 ድንጋጌ መሠረት ከድምፅ መቆጣጠሪያ መለኪያው የመኖሪያ ቤቶች 55፣ የንግድና ቦታዎች 65 እና የኢንዱስትሪ ቦታዎች ደግሞ ከ75  ዴሲቤል በላይ ማድረግ እንደማይቻሉ ተርነግሯል።

ይህንን ግዴታቸውን ያልተወጡ አካላት በወንጀል መጠየቅን ጨምሮ የተለያየ ዓይነት ቅጣት ይጠብቃቸዋል እንደ ኃላፊው ገለፃ። ለድምፅ ብክለትመንስዔ ናቸው ተብለው ከተለዩት መካካል የሃይማኖት ተቋማት፣ የጭፈራና መዝናኛ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ኢንዱስትሪዎች እና የግንባታ ሥራዎች ተጠቅሰዋል።

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ