የድሃና የሃብታም ልዩነት መስፋፋት | ኤኮኖሚ | DW | 12.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የድሃና የሃብታም ልዩነት መስፋፋት

ያለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት አዳጊ እየተባለ በሚጠራው የዓለም ክፍል ከመቼውም የበለጠ የኤኮኖሚ ዕድገት የታየባቸው ናቸው። በተለይ በእሢያ ክፍለ-ዓለም ጠንካራ የልማት ዕርምጃ ሲታይ በአፍሪቃም ባለፉት አሥር ዓመታት ያልተቋረጠ ዕድገት ሲደረግ ቆይቷል።

default

ይሁን እንጂ ከሚሊያርድ የሚበልጥ የዓለም ሕዝብን አንቆ የያዘው ድህነት መወገዱ ቀርቶ በረባ ሁኔታ እንኳ መለዘቡ ዛሬም አይታይም። በአንጻሩ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ በዓለም ሃብታሞችና ድሆች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየጨመረ መሄዱን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። እንግዲህ ጥቂቱ ሃብታሞች ይበልጥ እየካበቱ ብዙሃኑ ድሆች ደግሞ ይብስ ድሃ እየሆኑ መሄዳቸው ቀጥሏል ማለት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ ተቋም ዩ.ኤን.ዲ.ፒ. በቅርብ ጥናቱ እንዳመለከተው ከሆነ ሁኔታው በጣሙን ነእ የሚያሳስበው። በጥናቱ መሠረት ከዓለም አጠቃላይ ሃብት አብዛኛው፤ ማለትም 80 ከመቶው ተይዞ የሚገኘው 25 በመቶ በሚሆነው የሕዝብ ክፍል ብቻ ነው። ሶሥት-አራተኛው ሕዝብ እንግዲህ የጸጋው ተጋሪ አይደለም። ይህ ሁኔታ እርግጥ በአፍሪቃ ብቻ አይደለም ጎልቶ የሚታየው። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት አገሮችም የሃብታምና የድሃው ልዩነት መጠን ይበልጥ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። የገቢው ልዩነት እየጨመረ ሲሆን ትምሕርትን የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ዛሬ ለብዙዎች የሚደረስባቸው አይደሉም። እርግጥ በታዳጊውና በበለጸገው ዓለም ያለውን ሁኔታ እንደየአቅሙና ፍላጎቱ በንጽጽር ማየት ያስፈልጋል። የሆነው ሆኖ ግን ሁሉም የዓለም ክፍል እንደየሁኔታው የሚለው አለው።

“ሕንድ ውስጥ በሃብታምና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት ትልቅና እየሰፋ የሚሄድ ነው። ታውቃላችሁ፤ 55 በመቶው የሕንድ ሕዝብ የሚኖረው በአገሪቱ ሃብታም ከተማ በሙምባይ ውዳቂ ሰፈሮች ነው”

“ካሜሩን ውስጥ በወር ሃያ ኤውሮ በምትሆን ገቢ የሚተዳደሩ አሉ። ይህ መሆን የሌለበት ነገር ነው። ተቀባይነት የለውም”

እነዚህ ሁለት ምሳሌዎች የታዳጊውን ዓለም አጠቃላይ ሃቅ የሚያንጸባርቁ ናቸው። እርግጥ የድህነቱ መጠን የተለያየ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው በበለጸገው የዓለም ክፍልም የሃብታምና የድሃ ልዩነት መስፋት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ በጀርመን ለምሳሌ ዜጎች የማሕበራዊ ፍትህ ጥያቄን እንዲያነሱ እየገፋፋ ያለ ጉዳይ ነው።

“በሃብታሙና በድሃው መካከል ያለው ልዩነት ግዙፍ ነው። ግን መንግሥት ሁኔታውን ለማለዘብ ምንም አያደርግም። በመሠረቱ አሁን በብዙ ነገሮች እንደልባቸው ነጻ ሆነው ከሚንደላቀቁት ሃብታሞች የበለጠ ግብር መጠየቅ አለበት። እኛ በሞኝነታችን የበኩላችንን ግብር እንከፍላለን፤ እነርሱ ግን ሁሉ ቦታ አስተያየት ይደረግላቸዋል። ይህን ተገቢ አድርጌ አልመለከተውም’”

ሶሥቱም ከተለያዩ ክፍለ-ዓለማት፤ ከተለያዩ ሃገራት፤ ከሕንድ፣ ከካሜሩን፣ ከጀርመን የመነጩ ይሁኑ እንጂ ብሶታቸው አንድ ዓይነት ነው። በሃብታምና በድሆች መካከል ባለው ልዩነት መስፋት፤ ፍትሃዊ ባልሆነ የገቢ ክፍፍል ምሬታቸውን ይገልጻሉ። ዕውነትም ባለፉት ሃያ ዓመታት ሂደት የገቢ አለመመጣጠን በመላው ዓለም ይበልጥ እየጨመረ ነው የመጣው። እርግጥ ሁኔታው ከአገር አገር ይለያያል። በአንድ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ ተቋም በ ዩ.ኤን.ዲ.ፒ. ዘገባ መሠረት በሁኔታው ይበልጥ የሚጎዱት የታዳጊው ዓለም ነዋሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ጀኔቫ ላይ ተቀማጭ የሆነው ተቋም ሃላፊ ሤሢል ሞሊኒየር እንደሚያስረዱት ይህ ዓለምአቀፍ ግምት እንጂ ጭብት መረጃ አይደለም። ሃቁን በትክክል ማስቀመጥ ያዳግታል ባይ ናቸው።

“ዩ.ኤስ.አሜሪካ የገቢ አለመጣጣምን በሚያመለክተው ሰንጠረዥ ውስጥ በ 171ኛው ቦታ ላይ ነው የምትገኘው። ነገር ግን ቡርኪና ፋሶን፣ ማላዊን፣ ወይም ታንዛኒያን በመሳሰሉት ታዳጊ አገሮች ያነሰ ልዩነት ነው ያለው”

እርግጥ በሃብታምና በድሃ መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ለዓይን ጎልቶ የሚታየው በታዳጊ አገሮች ነው። ምክንያቱም ድህነት በዚያ የጠነከረ በመሆኑ! ነገር ግን በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት አገሮችም ሁኔታው በአጠቃላይ ከሚታሰበው በላይ የከፋ እየሆነ ነው የመጣው። እነዚሁ አገሮች ሰፊ ከሆነ የገቢ ክፍፍል ገና ብዙ የራቁ መሆናቸው በወቅቱ ጎልቶ እየታየ ነው። ቀድሞ በበለጸገው ዓለም አንድ አማካይ ገቢ አራት ሰዎችን ላቀፈ ቤተሰብ መተዳደሪያ ይበቃ ነበር። ግን ከሰላሣ ዓመታት ወዲህ ሁኔታው ተለውጧል። በሃብታምም ሆነ በድሆች አገሮች የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ዛሬ በደሞዛቸው የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን አይችሉም። በዓለምአቀፍ ደረጃ ለኑሮ የሚያስፈልገው ወጪ መጠን በመጨመር ላይ ነው የሚገኘው። የበለጸገውን ዓለም ብንወስድ የማሕበራዊው ዋስትና ወይም የድጎማ ዘርፍ መዳከም ለሁኔታው መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉም አልቀረም። በዚህ በጀርመን ለምሳሌ ይህ ለብዙዎች ጎልቶ የሚታይ ሃቅ ሆኗል።

“የምመኘው ይበልጥ ፍትህ እንዲሰፍን ነው። በቀላሉ ገንዘብ በሚያስፈልግበት ቦታ ገንዘብ እንዲኖር እሻለሁ። ለሕጻናት፣ ለድሆች፣ ለሆስፒታሎችም ተጨማሪ ነርሶችን እንዲቀጥሩ! በአጭሩ ለማሕበራዊው ዘርፍ ገንዘብ እንዲኖር ነው የምመኘው። ግን ሃቁ ይህ አይደለም። ሰው ዛሬ ብዙ መሥራት አለበት። እንዲያውም በቅርብ ምናልባት ሁለት ሥራ በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ማረፉ የተለመደ ሊሆን ይችላል። ከአሁኑም አዘውትሮ እየታየ ነው”

በጥቅሉ ለጤና ጥበቃ፣ ለትምሕርትና ለድሆች ድጎማ ተጨማሪ ገንዘብ ማስፈለጉ ነው የተነገረው። ግን ለመሆኑ ይህ ድህነትን ለማለዘብ ምን ያህል ድርሻ ይኖረራል? ሤሢል ሞልኒዬር አንደሚሉት ከሆነ ዕርምጃው በአንዳንድ አገሮች ፍሬ ሳይሰጥ አልቀረም።

“ሊወሰዱ የሚችሉ አንዳንድ ዕርምጃዎች አሉ። ለምሳሌ የገቢ ግብር ታሪፍን በተመለከተ ግብርን በገቢ መጠን ከፍ ማድረግ አንዱ ነው። ከዚሁ ሌላ በተለይ ችግረኛ የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት የተወጠኑ ፕሮግራሞች አሉ። በዚህ ረገድ ታዋቂዎቹ ለምሳሌ በብራዚል ለቤተሰብ የሚሰጥ ድጋፍ “ቦልሣ ፋሚሊያ” ወይም በሜክሢኮ ድሃ ቤተሰቦች ልቻቸውን ትምሕርት ቤት እንዲልኩና እናቶችም ከወሊድ ቀድመው እንዲመረመሩ የሚደረግ ዕርዳታ “ኦፖርቱኒዳዴስ” ናቸው”

እርግጥ እነዚህን የመሰሉት ማሕበራዊ ፕሮግራሞች ዛሬ ገና ብዙዎችን ያዳረሱ አይደሉም። አሁንም አርባ በመቶው የዓለም ሕዝብ መጸዳጃ የለውም። አንድ ሚሊያርድ ሕዝብም ገና ረሃብተኛ ነው። በድህነት የተነሣ ብዙ ሕጻናት በታዳጊ አገሮች፤ በተለይም በገጠር አካባቢዎች ከትምሕርት ቤት ቀድመው ነው የሚወጡት። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለምም የትምሕርት ዕድል ማግኘቱ በብዙዎቹ አገሮች ፍትሃዊ ሆኖ አይገኝም። ኦ.ኢ.ሢ.ዲ. በሚል አሕጽሮት የሚታወቀው የኢንዱስትሪ አገሮች የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት እንደሚለው መሠረታዊ የሆነው ማሕበራዊ ድጋፍና ትምሕርት መጠናከሩ በዓለም ላይ እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለውን የገቢ ልዩነት ወይም አለመጣጣም ለመቋቋም ፍቱንነት ያለው ነው። በነዚህ ቁልፍ ማሕበራዊ ዘርፎች ተሳትፎው ቀላልና ፍትሃዊ እንዲሆን ካልተደረገ በሃብታምና በድሃ መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ የሚቀጥል ነው የሚሆነው።

ታዳጊውን ዓለም በተመለከተ ድህነትን በመታገሉ ረገድ በወቅቱ ሌላው ችግር የምግብ ምርቶች ዋጋ መናርና መዋዠቅ ጭምር ነው። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ ትናንት ባወጣው የረሃብ ዘገባ በዓለም ዙሪያ በምግብ እጥረት የሚሰቃየው ሕዝብ ብዛት ባለፈው 2010 ዓ.ም. 925 ሚሊዮን ደርሶ እንደነበር አመልክቷል። ይህም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በ 75 ሚሊዮን መጨመሩ ነው። የድርጅቱ ባልደረባ ዮዜፍ ሽሚድሁበር ከሮማ እንደገለጹት ከሆነ ሁኔታው በቅርብ መለወጡም የሚጠበቅ አይሆንም።

“የምግብ ምርቶች በዛሬው ጊዜ ውድ ናቸው። ሂደቱ በአማካይ ጊዜ ሊቀየር መቻሉን በወቅቱ ለመናገር የሚያስችለን ሁኔታም የለም”

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከፊታችን 2015 ዓ.ም. ድረስ ረሃብን በዓለም ላይ በግማሽ ለመቀነስ ታላቅ ግብ ማስቀመጡ ይታወቃል። ከዚሁ የሚሌኒየም ግብ ለመድረስ ከተፈለገ በተጨባጭ አሃዝ የድሃውን ሕዝብ ቁጥር ከአንድ ሚሊያርድ ወደ 600 ሚሊዮን ለመቀነስ መቻል ማለት ነው። ይህ ግን አሁን ካለው አካሄድ እንደታሰበው መሳካቱ ብዙ ያጠራጥራል።

ዘገባችንን በሰሞኑ የኖቤል ሽልማት አሰጣጥ ስነ ስርዓት ለማጠቃለል የዘንድሮው የኤኮኖሚ ኖቤል ተሸላሚዎች ትናንት አሜሪካውያኑ ክሪስቶፈር ሢምስና ቶማስ ሣርጀንት ሆነዋል። ሽላሚው ኮሚቴ እንደገለጸው ሁለቱ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ለሽልማቱ የበቁት በብሄራዊ ኤኮኖሚ ሂደት ውስጥ ስላለው መንስዔና ተጽዕኖ፤ እንዲሁም በኤኮኖሚ ፖሊሲና የዋጋ ንረትን፣ የስራ ገበያን፣ አጠቃላይ ማሕበራዊ ምርትን በመሳሰሉ የኤኮኖሚ ዳታዎች መካከል ባለው ትስስር ላይ ባካሄዱት ምርምር ነው። ሢምስና ሣርጀንት የምጣኔ-ሐብቱ ዘርፍ በፖለቲካ፣ በማሕበራዊና በኤኮኖሚ ለውጦች ወቅት የሚይዘውን ባህርይ ለማብራራትም ሞክረዋል። የምርምራቸው ውጤትም የወቅቱን የኤኮኖሚ ችግር ባሕርያት ቀረብ ብሎ ለመመልከት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ዕምነት አለ።

በተረፈ በስዊድኑ ራይሽስባንክ የኤኮኖሚ ሣይንስ የኖቤል መታወሻ ሽልማት የአሜሪካን የምጣኔ-ሐብት ጠበብት የመምረጥ ያልተጻፈ ሕግ ያለ ነው የሚመስለው። ሽልማቱ መሰጠት ከጀመረ ከ 60ኛዎቹ ዓመታት ወዲህ ከጥቂት ጣልቃ-ገቦች በስተቀር ተሸላሚዎቹ በአብዛኛው አሜሪካውያን ነበሩ። ይም ሆነ ይህ ሁለቱ ጠበብት ምናልባትም ለወቅቱ የፊናንስና የኤኮኖሚ ችግር በቀላሉ ጭብጥ ምላሽ ለመስጠት አይድፈሩ እንጂ የምርምራቸው ውጤት አራማጅ እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic