የዴንማርክ ስለኤርትራ ስደተኞች ዘገባና ማስተባበያዉ | አፍሪቃ | DW | 19.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የዴንማርክ ስለኤርትራ ስደተኞች ዘገባና ማስተባበያዉ

የዴንማርክ መንግሥት ስለ ኤርትራ ስደተኞች የሚከተለዉን መርሕ እንዲቀየር ሃሳብ የሚያቀርበዉን የሐገሪቱን የስደተኛ ጉዳይ ዘገባ «ጥልቅ ስህተት ያዘል ዘገባ ሲል» የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት «HRW» አጣጣለ።

ድርጅቱ ትናንት እንዳስታወቀዉ ዴንማርክ እና ሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት በኤርትራ ላይ ያለዉን ማንኛዉንም አይነት የስደተኛ ፖሊሲ ከመቀየራቸዉ በፊት በተመ የኤርትራ ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን፤ የሚያወጣዉን ምርመራና ግምገማ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት «HRW» «የአፍሪቃ ቀንድ የአዉሮጳ ስደተኝነት መንስኤ» በሚል የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝዉዉርን ለመግታት ኅዳር 19 ኢጣልያ ሮም በተካሄደዉ ጉባኤ ላይ፤ ገደብ የሌለዉን የኤርትራን ብሔራዊ አገልግሎትና ዉትድርናን ሸሽተዉ ሀገሪቱን ለቀዉ የወጡ ዜጎች፤ የኤርትራ መንግሥት የፖለቲካ ለዉጥ ስለሚያደርግ ያለምንም ችግር ወደ ሀገራቸዉ መመለስ ይችላሉ፤ ስትል ዴንማርክ ያቀረበችዉን ዘገባ በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ያልተደገፈ ሲል አጣጥሎሏል።

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ ትናንት ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ዴንማርክ ያቀረበችዉ ይህ ዘገባ «ከኤርትራ የሚፈልሱትን የፖለቲካ ስደተኞች በሰብዓዊነት ከመቀበል ይልቅ ፤ ጥገኝነት ላለመስጠት የታለመ፤ ፖለቲካዊ ግብ ያለዉ ይመስላል ሲል ያትታል። የ HRW የምሥራቅ አፍሪቃ የሰብዓአዊ መብት አጥኚ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሌስሊ ሌፍኮዉ ዴንማርክ ስለኤርትራ ያቀረበችዉ ዘገባ ሙሉ መረጃን እንዳልያዘ ገልፀዋል፤

« ዘገባዉ የተመሰረተዉ እጅግ ዉስን በሆኑ ማንነታቸዉ ባልተገለፀ ግለሰቦች ላይ በመሆኑ እጅግ የተወሳሰበ ችግር ያለበት ነዉ። መረጃዉን ካወጣዉና ለመረጃዉ ምስክርነት ከሰጡት ምንጮች የተገኘዉ ዝርዝርም እርስ በርሱ ይቃረናል። መረጃዉን የፃፈዉ ሰዉ አንድም ኤርትራዊ ተበዳይን አልያም አይን እማኝን አነጋግሮ የቀረበ አይመስልም። ከዚህ ሁሉ ነጥቦች በኋላ ታድያ ዘገባዉ ምን ያህል ታዓማኒ ነዉ የሚል ትልቅ ጥያቄን ያጭራል።»

የተመ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣዉ ዘገባ ባለፉት ዓመታት ኤርትራን እየሸሹ ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር እጅግ የጨመረ ሲሆን አብዛኞቹ ስደተኞች ደግሞ በአዉሮጳ ሃገራት የሰደተኝነት መብትን አልያም የልዩ እንክብካቤ ፈቃድን እንደሚያገኙ አስታዉቋል። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት «HRW» ባወጣዉ ዘገባ የኤርትራ መንግሥት በሃገሪቱ የፖለቲካ ማሻሻያ ለዉጥ ያደርጋል ብሎ ከመገመት ይልቅ በአዉሮጳ የሚገኙ ስደተኛ ተቀባይ መንግሥታት ይህ የተባለዉ ጉዳይ ተፈጻሚነት እስኪያገኝ ማየትና መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ሌፍኮዉም ይህንኑ ነዉ ያረጋገጡት፤

«በተመ የኤርትራ ጉዳይ አጣሪ ኮሚሽን በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትክክለኛና ጥልቅ ምርመራን የሚያርግ አካል ነዉ ብለን እናምናለን። በዚህም ምክንያት የአዉሮጳ መንግስታት ስለኤርትራ ስደተኞች ጉዳይና የሰብዓዊ መብት ችግሮች ላይ ያላቸዉን ፖሊሲ ከመቀየራቸዉ በፊት መርማሪ ኮሚሽኑ የሚሰጠዉን መልስ መጠበቅ እና ማየት እንዲሁም የኤርትራ መንግስት ከአጣሪ ኮሚሽኑ ጋር ትብብር ማሳየት አለማሳየቱን ማየት እጅግ አስፈላጊ ነዉ»

እንደ አንዳንዳ ታዛቢዎች የአዉሮጳ ሃገራት ፍላጎት የሚመጣባቸዉን የስደተኛ ቁጥር መቀነስ እንጂ ስደተኛ በሚፍፈልቅባቸዉ ሃገራት የፖሊሲ ለዉጥ አልያም ስለስደተኛ ፖሊሲ ግምገማ ማድረግ አለማድረግ ግድ አይሰጣቸዉም። እንደ ተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ዘገባ በጎርጎረሳዉያኑ 2014 ዓመት ወደ አዉሮጳ የገቡ የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር ከቀዳሚዉ ዓመት በሶስት እጥፍ አድጓል፤ ባለፉት 10 ወራት ብቻ 37 ሺህ ኤርትራዉያን አዉሮጳ መግባታቸዉ ነዉ የተመለከተዉ። ስለዚህም ይላሉ የ HRW አጥኚ ሌስሊ ሌፍኮዉ የዴንማርኩ የኤርትራ ስደተኞች ዘገባ ያልተሟላ ነዉ፤

« ከኤርትራ ወደ አዉሮጳ ለመግባትና ኤርትራን ለመልቀቅ የሚሞክረዉ የስደተኛ ቁጥር እጅግ መጨመሩ ግልጽ ነዉ። እንደኔ እምነት ትክክለኛና በቂ መረጃን ያልያዘዉ የዴንማርክ ዘገባ በኤርትራ ስለ ሰብዓዊ መብት ጉዳይ በትክክል ይመልከት አልያም ከኤርትራ የሚወጣዉን የስደተኛ ቁጥር ለማፈን የተደረገ ስለመሆኑ ግልፅ ባለመሆኑ በርግጥ በርከት ያለ ጥያቄን ያስነሳል።

ምክንያቱም ይላሉ ሌስሊ ሌቭኮ በገፍ እየፈለሰ ስላለዉ የስደተኛ ጉዳይን በተመለከተ በአዉሮጳ ሃገራትና በኤርትራ እንዲሁም በሌሎች የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት መካከል በተለያዩ ግዝያት ልዩ ልዩ ዉይይትና ንግግር በመካሄድ ላይ በመሆኑ ነዉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic