የዴሞክራሲ ባህል - ጀርመን | ባህል | DW | 11.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የዴሞክራሲ ባህል - ጀርመን

«ጀርመኖች እዚህ ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት ቁጭ ብለዉ በመነጋገርና በመወያየታቸዉ ነዉ። ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ ከአፈር ከረሜላ ሰርተዉ ሃገራቸዉን እዚህ ደረጃ ላይ አድርሰዋል። ከጀርመን የምንማረዉ ተነጋግሮ መግባባት ላይ በመድረስ፤ ከሁሉ በላይ ሃገራዊ ጉዳይን ከፓርቲ ማስቀደምን ነዉ።»        

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:27

የጀርመን የዴሞክራሲ ባህል በኢትዮጵያዉያኑ እይታ

«የፖለቲካ ባህል ዳበረ ሲባል በዴሞክራሲ ይታመናል፤ ዴሞክራሲም ተግባራዊ ይደረጋል ማለት ነዉ። በዴሞክራሲ የሚታመን ከሆነ ዛሬ በሚደረግ ምርጫ ብቻ ዴሞክራሲን መካድ እንደማይቻል ማኅበራዊ መገናኛ መድረክ በተስፋፋበት በያዝነዉ በ 21 ኛዉ ክፍለዘመን በተለይ እለት ተዕለት የፖለቲካ ተፅኖ በመደረጉ እንደፈለግነዉ መቀጠል አንችልም። ስለዚህ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ተቃቅፎ የመተኛት አልያም ነገሮችን የማለሳለስ ነገር ሳይሆን፤ ራዕይ ኖሮት ለዕለት ጥያቄ ለወደፊቱም ለዛሬም ምላሽን የሚሰጥ ኃሳብን የማያመነጭ ከሆነ ለሌሎች ፖለቲከኞች ቦታዉን መልቀቅ ይኖርባቸዋል ማለት ነዉ። ይህን ቦታ ይዘዉ ያለዱላ ያለጥይት መፋጨትና መወያየት የሚፈልጉ በርካታ ወጣቶች አሉ። » 

በጀርመን ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸዉን ያካፈሉን በጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ ናቸዉ። ባሳለፍነዉ መስከረም 24፤ 2017 የጎርጎረሳዉያን ዓመት ጀርመናዉያን የምክር ቤት ተወካዮቻቸውን ቢመርጡም የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም መግባብያ ኃሳብ ላይ ደርሰዉ  መንግሥትን መመስረት አልቻሉም።  ጀርመን ውስጥ አዲስ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የተጀመረው ድርድር ዛሬም በክርስቲያን ዲሞክራቶቹ፣ በክርስቲያን ሶሻል ኅብረት እና በሶሻል ዲሞክራቶቹ መካከል እንደቀጠለ ነው። ከዛሬ ሦስት ወራት በፊት አጠቃላይ ምርጫን ያካሄደችዉ ጀርመን እስከዛሬ ለምን መንግሥትን መመሥረት ተሳናት?! የመራጬ ሕዝብ ብሎም የፖለቲካ ፓርቲዎች ርምጃስ ምን ይመስላል? የጀርመን የፖለቲካና የዴሞክራሲ ባህል በኢትዮጵያዉያኑ እይታ ምን ይመስላል ስንል ቅንብር ይዘናል።

የዴሞክራሲ ባህል ያለመዳበር፣ ሕገ - መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልግ ኃይል መኖር፣ ለህዝብ ውሳኔ ያለመገዛት፤ የራስን የውስጥ ችግር በሚገባ አይቶ ውስጣዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ውጫዊ ሽፋን መስጠት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰናከል መሆኑ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል። በለፀጉ በሚባሉ ሃገራት በርግጥ ይህ ጉዳይ አይከሰትም፤ በአንፃሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት ለመራጩ ሕዝብ የገቡትን ቃል ለመፈፀም ከፍተኛ ትግልን ያካሂዳሉ።

በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የተገኘዉ ያልተጠበቀ ዉጤት የሃገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ቀይሮታል። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ሕብረት «CDU» እና እህት ፓርቲዉ የባቫርያዉ ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት «CSU» በጥምረት አብላጫ ድምፅን ቢያገኙም መንግሥትን ለመመስረት ግን በቂ አልሆነላቸዉም። በሌላ በኩል ባለፉት 12 ዓመታት ከነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ጋር በጥምረት ሃገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረዉ የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ «SPD» በምርጫ ዉጤት ማግስት  ጥምር መንግሥቱን እንደማይቀላቀልና ተቀናቃኝ ሆኖ እንደሚቀጥል ቢገልፅም አዲስ ጥምር መንግሥትን ለመመስረት ከአለፈዉ እሁድ ጀምሮ ልዩ ዉይይት ላይ ይገኛል። መስከረም ላይ በተካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫ ዉጤት መሠረት ቀኝ አክራሪው «AFD»  ወደ ምክር ቤት መግባቱ የሃገሪቱን የፖለቲካ ምሕዳር ቀልብሶታአል። በፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ እንደሚሉት ከሆነ የጀርመን ዴሞክራሲ የዳበረ መሆኑ ቢታወቅም አሁን ከምርጫ በኋላ መንግሥት ለመመስረት በተደረገዉ ጥረት ላይ ስህተት ተፈጥሮአል።

«በመጀመርያ ደረጃ በድርድር ዉስጥ ስህተት ነዉ ብዬ የማምነዉ፤ ሶሻል ዴሞክራቶች ከሁለቱ ፓርቲዎች ጋር በተመጣጣኝ ቁጥር እና ይዘት ለድርድር አለመቅረባቸዉ ነዉ። «CSU» እና «CDU» ማለት ሁለቱ እህትናማች ፓርቲዎች 50 % ይዘዉ ሶሻል ዴሞክራት «SPD» ም 50% ይዘዉ መደራደርና መከራከር ይኖርባቸዋል። ለምን ቢባል እህትናማቾቹ ፓርቲዎች መስከረም 24 ቀን በተደረረገዉ ሃገር አቀፍ ምርጫ በምረጡኝ ዘመቻ ላይ በጥምረት ወጥተዉ የምርጫ ዉጤትን አግኝተዋል። በዚህ ዉይይት ላይም የሁለቱን ፓርቲዎች የሕዝብ ተወካዮች ይዘዉ ነዉ የቀረቡት።

እዚህ ላይ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ስህተት ሁለቱ እህትናማች ፓርቲዎች የዉስጥ ችግራቸዉን ተነጋግረዉና ፈተዉ ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር እንዲወያዩ ማድረግ እንጂ ሶሻል ዴሞክራቶች ሁለቱ ፓርቲዎች አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ አድርጎ መደራደሩ የመጀመርያ ስህተት ነዉ፤ ብዬ አምናለሁ። ይህ አቅዋም ለሶሻል ዴሞክራቶች ዉድቀት ይመስለኛል። ይህ በጀርመን ለምን እስካሁን መንግሥት መመስረት አልተቻለም ለሚለዉ ጥያቄ፤ ትልቁ የችግር ምንጭ ነዉ። ይህ የችግር ምንጭ እንዴት ሊመጣ ቻለ የሚለዉን ለማብራራት ያህል፤  «CSU» የሚባለዉ በባቫርያ ዉስጥ የሚገኘዉና ግዛቱን የሚaseተዳድረዉ የፖለቲካ ፓርቲ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ወዲህ የባቫርያን ግዛት ከጎርጎረሳዉያኑ 1948 /49 ጀምሮ ብቻዉን ያስተዳድራል። የክርስትያን ዴሞክራቲክ ሕብረት ፓርቲ «CDU» የክፍልሃገር ምርጫ በሚያካሄድበት ወቅት ባቫርያ ሄዶ አይወዳደርም። ይህ እንደምሳሌ ለመግለፅ የክፍለሃገር ምርጫ ሲሆን አንተጋ መጥቼ አልቀናቀንህም፤ የሃገር አቀፍ ምርጫ ሲካሄድ ግን በጥምረት እንወዳደራለን፤ የተባበረ ኃይል ይኖረናል ብሎ መስማማት ማለት ነዉ። ሁለቱ እህትማማች ፓርቲዎችም በዚሁ ስምምነታቸዉን ለዘመናት ቀጥለዋል። ይሄ ሲንከባለል የመጣ መሠረታዊ ስህተት ነዉ። ለዚህም ነዉ ሕዝብ መስከረም 24 በተካሄደዉ ምርጫ ላይ ድምፁን አልሰጥም ያላቸዉ። አሁንም ለዚህ ጥያቄ መልስ እስካልሰጡ ድረስ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት በድብቅ እንስማማ ወደ ዉጭ ዜናን አናወጣ፤ ምርጫ ከተካሄደ አራት ወራት ሞላዉ እንዴት ያለ አዲስ መንግስት ይህን ያህል ጊዜ እንቆያለን፤ እኛ የበለፀግን ሃገር ነን ቶሎ ብለን፤ መንግሥት እንመስርት እያሉ በፍጥነት ለጥያቄዉ መልስ በቀላሉ የሚገኝ አልሆነም። እንደ ጀርመኖች አባባል ከፍጥነት ይልቅ መሠረት ያለዉ መልስ መገኘት አለበት ነዉ። እንደዉም ጀርመን አዲስ ምርጫ የሚያስፈልጋት ይመስለኛል። »      

ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን ዓመት መስከረም ላይ በተካሄደዉ ምርጫ በርካታ መራጮች ሜርክል ለሚመሩት ፓርቲ ድምፃቸውን ያልሰጡት ሜርክል በያዙት የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት ነዉ ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። በአንፃሩ በጀርመን የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ለመቀነስ የሚታገለዉ መጤ ጠሉ ፓርቲ «AFD» ከአጠቃላዩ ድምፅ 13 % ድምፅን አግኝቶ የፓርላማ ወንበርን ለማግኘት መብቃቱ ነዉ። በጀርመን ሲኖሩ 40 ዓመታትን ያስቁጠሩት ሲስተር መሠረት አለፈለገሰላም እንደሚሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መንግሥት ለመመስረት እስከዛሬ ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉት ኃላፊነታቸዉን በማወቃቸዉ ሕዝብን በማክበራቸዉ ነዉ። 

«በወቅቱ በጀርመን የሚታየዉ ሁኔታ መንግሥት ለመመስረት አዳጋች እንደሆነባቸዉ እናያለን፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ፓርቲ በኃላፊነት ምክንያት ኃላፊነት ወስጄ እኔ እጠየቅበታለሁ በሚል አቋም ስላላቸዉ እና ዴሞክራሲያቸዉን በጣም ስለሚያከብሩት በተቻለ መጠን እኛ ሕዝብ የመረጠን ሥራ እንድንሰራለት ነዉ የሚል ዋናዉ መሰረታዊ አስተሳሰባቸዉን ነዉ የሚያንፀፀባርቀዉ። ይህ ሁሉ ንትርክና ይህ ሁሉ ትግል ቀላል እንዳልሆነ ነዉ። በጀርመን ፖለቲካ ዉስጥ በአለፉት ሁለት ዓመታት በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ታይተዋል። ከአስቸጋሪዎቹ ነጥቦች አንዱ የዉጭ ሃገር ሰዎች እየፈለሱ መምጣት ነዉ። በአጠቃላይ በብዙ ነጥቦች ላይ ዉይይት ይካሄዳል። ሆኖም ግን ይህ የሚያሳየን ለሕዝባቸዉ በጣም የቆሙ እና የሕዝቡን ጥያቄ ኮስተር ባለ ሁናቴ እያሰቡበት እንደሚሄዱ ነዉ የሚያሳየን። ይህ ታድያ ደካማ ጎናቸዉን ሳይሆን የሚያሳየዉ ጠንካራ ጎናቸዉን እና ለአገራቸዉ ያላቸዉን አቋም እና ለሕዝባቸዉ ያላቸዉን ክብር ነዉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝባቸዉ የሚጠይቃቸዉን ጥያቄ ለማሟላት ከልባቸዉ ቆመዉ ነዉ የሚዋጉት። መንግሥታቸዉን እንደሚመሰርቱም እርግጠኛ ነኝ።»     

የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ግንኙነት ዘርፍ አጠናቀዉ የዶክትሬት ማዕረጋቸዉን በመስራት ላይ የሚገኙትና እዚህ በጀርመን ኮለኝ ከተማ የሚገኘዉ ፋዉንዲንግ ዳይሬክተር የቻይና አፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ አቶ አሌክሳንደር ደምሴ፤ የጀርመን የመንግሥት ወቅታዊ ሁኔታ በጀርመን የፖለቲካ ባህል ያልተለመደ ቢሆንም፤ በሃገሪቱ ጠንካራ ተቋማት በመኖራቸዉ ከምርጫ በኋላ መንግሥት አለመመስረቱ ብዙም የሚያሰጋ ነገር አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

« ይህ ነገር የሚያሳየዉ ሁለት ነገሮችን ነዉ። አንደኛዉ እንደ ጀርመን ዓይነት ጠንከር ብለዉ ዴሞክራሲን የጨበጡ ሃገሮች ሃገርን ለማስተዳደር በግድ አንድ መንግሥት አያስፈልጋቸዉም። ምክንያቱን በሃገሪቱ ያሉት ተቋማት ጠንካራ ስለሆኑ ስልጣንን በይፋ ያላገኘ መንግሥት «ማለትም ጊዜያዊ መንግሥት» በጊዜዉ መፅደቅ ያለባቸዉን ሥራዎች ሁሉ በጊዜያዊነት የተቀበለዉን ስልጣን ተጠቅሞ ነገሮችን ተፈፃሚ እንዲሆኑ ዉሳኔዉን ማስተላለፍ ይችላላ። ይህ የሚያሳየን ተቋማቱ ጠንካራ በመሆናቸዉን፤ ይፋዊ ስልጣን ያልያዘ መንግሥት ቢኖርም ተፈፃሚ መሆን ያለበት ነገር ሁሉ ተግባራዊ መሆኑን ነዉ። ሁለተኛዉና አሉታዊ የሚባለዉ ግንዛቤ ግን እንደ ቀድሞ በአንድ በሁለት አልያም በአራት ፓርቲ ብቻ ሃገርን ለማስተዳደር ነጥቦብን ይዞ መቅረብ አለመቻሉ ነዉ። በአሁኑ ወቅት ትንንሽ ፓርቲዎችም የተለያዩ አስተያየቶችንና ነጥቦችን እየያዙ ወደ ፖለቲካዉ መድረክ እየገቡ ነዉ።»

ከጀርመን የፖለቲካ ባህል ልንቀስም የምንችለዉ፤ በዉይይት ማመናቸዉ ነዉ ያሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር ለማ ይፍራሸዋ « ጀርመን ታላቅ ሃገር ነች ሲሉ እንዲህ ይገልፃሉ።

« ጀርመን ታላቅ ሃገር ነች። በጀርመን ይህ አንድ ትዉልድ በጦርነት ሳይሆን በሠላም ተወልዶ በሠላም አድጎ በሠላም ጡረታ የደረሰ ኅብረተሰብን የያዘች ሃገር ናት። በኤኮኖሚ የበለፀገች ሃገር ናት። ጀርመኖች እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ቁጭ ብለዉ በመነጋገርና በመወያየታቸዉ ነዉ። ባለፈዉ ጊዜ በተለያዩ የዓለም እና የአዉሮጳ ፖለቲካ ሁኔታዎች በሚፈቅዱት መሠረት ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ ከአፈር ከረሜላ ሰርተዉ ሃገራቸዉን እዚህ ደረጃ ላይ አድርሰዋታል። ይህ ጥያቄ ዉስጥ አይገባም።

ያ ማለት ስለትናንትናዉ ፖለቲካ ብቻ ማየት የለብንም። ዛሬ በ 21ኛዉ ክፍለዘመን እንዴት አዉሮጳን አንድ አድርገን ማኖር እንችላለን የሚለዉ ላይ ነዉ። አዉሮጳ በቃላት ብቻ ሊቆይ አይችልም። አዉሮጳን እንዴት አድርገን በኅብረት ማስቀጠል እንችላለን። አዉሮጳ በዓለም ላይ እንዴት ተፅኖ ማሳረፍ እንዲችል ማድረግ እንችላለን ለሚለዉ ጥያቄ ላይ፤ ትክክለኛ መልስ መስጠት መቻል ይኖርባቸዋል። ከጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምንማረዉ አንደኛ ቁጭ ብለዉ በጥሞና መወያየት መቻላቸዉ ነዉ። ከጀርመን መማር የሌለብን ሌላዉ ነገር መራጭ ጋር እራስን ዉድ አድርጎ ለመሸጥ የሚደረገዉ ጉዞና ዘመቻን ነዉ። ይህ ያለፈ የፖለቲካ ልምድ ነዉ። ይህ በ21ኛዉ ክፍለዘመን፤ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ተንሰራፍቶ በሚገኝበት እና ትክክለኛ መረጃ በደቂቃ ዉስጥ እዉነቱ በሚታወቅበት በአሁኑ ወቅት፤ የዚህ ዘመን ፖለቲከኛ መሆን በጣም በጣም ጠንካራ ሆኖ መዉጣት ያስፈልጋል። ዋናዉ ግን ከጀርመን የምንማረዉ ተነጋግሮ መግባባት ላይ በመድረስ፤ ከሁሉ በላይ ሃገራዊ ጉዳይን ከፓርቲ ማስቀደምን ነዉ።»        

ጀርመን ውስጥ አዲስ ጥምር መንግሥት ለመመስረት በክርስቲያን ዲሞክራቶቹ፣ በክስርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት እና በሶሻል ዲሞክራቶቹ መካከል የጀመረዉ ድርድር በሳምንቱ መጠናቀቅያ ላይ እልባት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የፖለቲካና ዴሞክራሲ ባህል በጀርመን በሚል ርዕስ የጀርመንን ወቅታዊ የፖለቲካ መድረክ የቃኘንበት ሙሉ ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

 

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic