የዳዳብ ስደተኞች እጣ ፈንታ | አፍሪቃ | DW | 29.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የዳዳብ ስደተኞች እጣ ፈንታ

ከዓለም በትልቅነቱ በሚታወቀው ምሥራቅ ኬንያ በሚገኘው የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ከ320 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ ።መጀመሪያ ዳዳብ የመጡት በጎርጎሮሳዊው 1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሶማሊያውን አስከፊ ጦርነት ሸሽተው የተሰደዱ ሶማሊያውያን ናቸው ። እጅግ በከፋው ጊዜ የስደተኞቹ ቁጥር ከ450 ሺህ በላይም ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:56

ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ

የኬንያ መንግሥት ይህን መጠለያ ጣቢያ እንደሚዘጋ ከተወሰኑ ጊዜያት በፊት አስታውቋል ። ባለፈው ቅዳሜ የኬንያ የሶማልያ እና የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ተደራዳሪዎች ስደተኞቹ ወደ መጡበት ስፍራ በሚመለሱባቸው ሁኔታዎች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። «ዳዳብ መዘጋት አለበት ዳዳብ ይዘጋል ።»የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና ሞሀመድ መንግስታቸው ዳዳብ የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞችን ወደ መጡበት ለመመለስ የያዘው አቋም እንደማያጠራጥር የገለጹበት አባባል ነው ።ከዚያ በፊት እስከ ጎርጎሮሳዊው 2016 መጨረሻ የስደተኞቹን ቁጥር ቢያንስ በግምሽ የመቀነስ እቅድ እንዳለ ኬንያ ሶማሊያ እና የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR የሚገኙበት ኮሚቴ አስታውቋል ። ኬንያ በአንድ ወቅት ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች መጠለያ የነበረውን የዳዳብ ጣቢያ እዘጋለሁ የምትለው ጣቢያው የሶማሊያን መንግሥት የሚወጋው አሸባብ በኬንያ ጥቃት ለመጣል ሰዎችን የሚመለምልባቸው ስፍራ ሆኗል በሚል ምክንያት ነው ። ሆኖም ኬንያ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ሶማሊያ እንዳትመለስ ዩናይትድ ስቴትስ እና የተመድ ተማጽነዋታል ። የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው ስለ ሚመለሱባቸው ሁኔታዎች በወጣው እቅድ

ውስጥ ይኽው መካተቱን ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።
«ለአንዳንዶቻችሁ እንደተናገርኩት ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንቱን ባገኘኋቸው ጊዜ ሁላችንም እቅዱን እንድናቀርብላቸው ጠየቁን ። እቅዱም የፈቃደኝነት የደህንነት እና የክብርን መርሆችን እና በተጨማሪም በትክክል መተግበር የሚችል መሆኑን መሠረት ያደረገ ነው ።»
የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለው ዳዳብ የሚገኙ ስደተኞች በማንኛውም ሁኔታ ያለፍላጎታቸው ወደመጡበት አይመለሱም ። ይህንንም የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብድሰላም ኦመር አረጋግጠዋል ።
«እንዳትሳሳቱ በግዳጅ የሚደረግ መመለስ አይኖርም ።ወደ መጡበት መመለስ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነው የሚሆነው ።ይህ ደግሞ ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበት ዋና መርህ ነው ።ስደተኞቹን መመለሱ ሰብዓዊ ክብርን በጠበቀ መንገድ እና በሦስቱ ወገኖች ስምምነት መሠረት መከናወን አለበት ። እንደሚገባኝ ይሄ በጊዜ ሊገደብ አይችልም ከዚህ ይልቅ በሁኔታዎች የሚወሰን ነዉ የሚሆነው ። አሁን በተደረገው ለውጥ ደስተኞች ነን ።
የኬንያ የዳዳብን መጠለያ በጎርጎሮሳዊው ህዳር 30 ይዘጋል ነበር ያለችው ።ፊሊፖ ግራንዲ እንዳሉት ደግሞ እስከ 2016 መጨረሻ ድረስ 150ሺህ የሚሆኑ ሶማልያውያን በፈቃደኝነት ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ይህ ቁጥርም

አሁን ዳዳብ ከሚገኙት ወደ ግማሽ ያህል የሚጠጋ ነው ። የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሀመድ ማንም ወደ ሃገሩ አልመለስም እንደማይል አይጠራጠሩም ።
«ካካሄድናቸው ንግግሮች ውስጥ አንመለስም የሚል አልሰማሁም ። የሰማሁት ቢኖር ሰዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ነው ። ብቸኛው ፈተና ወደ ሃገራቸው የሚወስዷቸው ንብረቶች ጉዳይ እና የሚመለሱባቸው ቦታዎች ደህንነት ነው ። »
ይሁንና ሚኒስትሯ አንመለስም የሚሉ ሰዎች ግን ምን እንደሚደረጉ አልተናገሩም። የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት መንግሥት ለተመላሾቹ መሬት አዘጋጅቷል ። UNHCR ደግሞ ለትምህርት ለሆስፒታል እና ለመሳሰሉት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ያደርጋል ። ሆኖም ግራንዲ እንደሚሉት ድርጅታቸው የለጋሾችን ድጋፍ ይፈልጋል ።
«ገንዘብ ያስፈልገናል ። ለጋሾች ለዚህ እቅድ መሳካት የሚያስፈልጉ በቂ መዋጮዎችን እንዲያደርጉ እንማፀናለን ።ምክንያቱም ካለ ገንዘብ ድጋፍ የወጣውን እቅድ በተገቢው መንገድ ተግራባራዊ ማድረግ አይቻልም ። »
ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው የመመለሱ ሥራ እየተካሄደ ሲሆን እስከ መጪው ዓመት ጥቅምት ይቀጥላል ተብሏል ። ከዚያ በኋላ ኬንያ ሶማልያ እና UNHCR የተከናወነውን ሥራ ለመገምገም በጥቅምት ለመሰብሰብ ተስማምተው ተለያይተዋል ።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic