የዳቮስ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ መድረክ | ኤኮኖሚ | DW | 28.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የዳቮስ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ መድረክ

በስዊትዘርላንድ ተራራማ መዝናኛ ስፍራ በዳቮስ በየዓመቱ የሚካሄደው የዓለም ኤኮኖሚ መድርክ ጉባዔ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል።

የዳቮስ የጉባዔ ማዕከል

የዳቮስ የጉባዔ ማዕከል

በርካታ የመንግሥታት መሪዎች፤ እንዲሁም አያሌ የፊናንስና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጠሪዎች በሚሳተፉበት ጉባዔ ላይ ዓበይት ርዕስ ሆኖ የሚሰነብተው በተለይ እየተባባሰ የሄደው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሁኔታ ነው። በዳቮስ ለአራት አሠርተ-ዓመታት ያህል ሲካሄድ የቆየው የኢንዱስትሪው ዓለም የመድረክ ጉባዔ የዛሬውን ያህል ከባድ ቀውስ ጋርዶት የተካሄደበት ጊዜ አይታወስም። ታዲያ አምሥት ቀናት በሚፈጀው ጉባዔ ባለፉት ወራት ዓለምን ወጥሮ ያያዘውን የፊናንስ ቀውስና አቆልቁዋዩን የኤኮኖሚ ጉዞ ለመግታት ጭብጥ ሃሣቦችን ዕውን ለማድረግ መቻሉ እስከምን ይሆን?
የዳቮስ መድረክ ተሳታፊዎች የዓለምአቀፉን የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ዕድሜ ቢቀር ለማሳጠር ዘዴዎችን ለማመንጨት ያልተቆጠበ ጥረት የሚያደርጉ ሲሆን እስከ ሣምንቱ መጨረሻ የሚዘልቀውን ጉባዔ በንግግር የከፈቱት የቻይናና የሩሢያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ዌን ጂያባዎና ቭላዲሚር ፑቲን ናቸው። የነዚህ ሁለት መንግሥታት መሪዎች በኢንዱስትሪው ዓለም መድረክ ላይ መገኘትና፤ መገኘት ብቻም ሣይሆን ግንባር ቀደም ተሳትፎ ማድረግ ችግሩ ዓለምን ያዳረሰና በመፍትሄ ፍለጋው ረገድም በአንድ ያስተሳሰረ መሆኑን እንደገና የሚያመለክት ነው።

በጉባዔው ላይ ቀውሱን ለመታገል በብዙ መቶ ቢሊዮን የሚቆጠር የግብር ከፋይ ሕዝብ ገንዘብን ያፈሰሱት ቀደምት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ መንግሥታት የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል፣ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውንና የጃፓኑ የሥልጣን አቻቸው ታሮ አሶም በሣምንቱ ሂደት በመድረኩ ላይ ንግግር ከሚያሰሙት ሃምሣ ገደማ የሚጠጉ የመንግሥታት መሪዎች መካከል ይገኙበታል። የመድረኩ መሥራች ክላውስ ሽዋብ በዋዜማው እንዳሉት የወቅቱ ጉባዔ ፈታኝና ምናልባትም የተለየ ክብደት የሚሰጠው ነው።

“ዘጠና ሃገራትን ሰብስበናል። ሃምሣ ገደማ የሚጠጉ የመንግሥታት መሪዎች ይመጣሉ። ቁልፉ ጉዳይ የተባበረ ድምጽን፤ የስብዕና ድምጽን ማስፈን ይሆናል። ምክንያቱም አሁን የተደቀነው የመጀመሪያው ዕውነተኛ ዓለምአቀፍ ቀውስ ነው። ከዚህ ለመላቀቅ ከፈለግን ችግሩን ልንወጣው የምንችለው በዓለምአቀፍ ደረጃ በተቀናበረ ዘዴ ብቻ ነው። ይህን መወጣቱ ደግሞ ታላቁ የዳቮስ ፈተና ይሆናል”
የዳቮሱን መድረክ በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ ችግር የደረሰባቸው አንዳንድ መንግሥታት የዕርዳታ ጥሪ ለመሰንዘር የሚጠቀሙበት መሆኑም ነው የሚጠበቀው። ለምሳሌ ያህል የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሬቼፕ-ታይፕ-ኤርዶሃን ከዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም ከ IMF ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት ሁለቱ ወገኖች በብድር አቅርቦት በኩል ያላቸውን የሃሣብ ልዩነት ለመፍታት ያቅዳሉ።
አንድ የምንዛሪው ተቁዋም የልዑካን ቡድን በቱርክ ያካሄደውን የ 12 ቀናት የሥራ ጉብኝት ባለፈው ሰኞ ሲፈጽም ብድሩን የማጓተቱ ሂደት ለኤርዶሃን አልተዋጠላቸውም። የቱርኩ መሪ የፊናንሱ ድርጅት ተግባር ዓባል መንግሥታት ችግር ሲገጥማቸው ድጋፍ መስጠት መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዩ መጓተቱን ከቀጠለ የአገራቸውም ትዕግሥት ወሰን እንዳለው ነው ወደ ዳቮስ ከመጓዛቸው በፊት ያስገነዘቡት። እርግጥ የምንዛሪው ተቁዋም በበኩሉ ለችግሩ ተጠያቂ የሚያደርገው ቱርክን ነው።
ያም ሆነ ይህ በዳቮስ የተሰበሰቡት የመንግሥታት መሪዎች፤ የፊናንስ ሚኒስትሮች፣ የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎችና የንግዱ ዘርፍ ተጠሪዎች አብዛኛውን ትኩረት የሚሰጡት ለዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት ፈውስ በማፈላለጉ ጉዳይ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። በሌላ በኩል በአዲሱ የዋሺንግተን መስተዳድር ላይ ዓለምአቀፉን ቀውስ የማለዘብ ታላቅ ተሥፋ ቢጣልም አሜሪካ በዳቮሱ መድረክ ላይ በከፍተኛ ባለሥልጣን አለመወከሏ ጥቂትም ቢሆን ቅር ማሰኘቱ አልቀረም።
ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለብሄራዊው ሸንጎ ያቀረቡት የ 825 ቢሊዮን ዶላር የኤኮኖሚ ማገገሚያ ዕቅድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የያዙት ትግል መሳካት አለመሳካትም ለስጋት መንስዔ የሆነ ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ውድቀት ወዲህ የከፋው የሆነውን ቀውስ ለማሽነፍ የበለጠ ትግል ለማድረግ ቁርጠኝነት መኖሩ የተሰወረ አይደለም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከሺህ የሚበልጡ የኩባንያ አስተዳዳሪዎችን አስተያየት በማጠናቀር ዳቮስ ላይ በመድረኩ ጉባዔ ዋዜማ የቀረበ የጥናት ውጤት እንዳመለከተው አንዱ የቀውሱ ትልቅ ችግር የዓመኔታ መጥፋት ነው። በፊናንሱ ገበዮች ይህን መልሶ ማስፈኑም እጅግ ጠቃሚነት ይኖረዋል ነው የተባለው።

አብዛኞቹ ኩባንያዎች የመጪዎቹን ሶሥት ዓመታት የኤኮኖሚ ዕድገት ተሥፋ በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት። የዝንባሌ መለኪያ መጠይቅ ውጤቶች እንደጠቆሙት በሚቀጥሉት ወራት የገቢ ዕድገት የሚጠብቁት ቀደምት የኩባንያ አስተዳዳሪዎች ቁጥር ከሩብ ዝቅ ያለ ነው። ይህም ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር 50 በመቶ ያነሰ ይሆናል። በወቅቱ በርካታ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ ገበያ እያጡና ቀውስ ላይ እየወደቁ ሲሆን ሠራተኞችን የሚያሰናብቱት ወይም ምርት በመቀነስ ላይ የሚገኙትም ጥቂቶች አይደሉም።

በአውሮፓ ያለፉት ዓመታት ለዘብተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ቢቀር በዚህ ዓመት ባለበት መቀጠሉ አይታሰብም። የሥራ አጡ ቁጥር መልሶ የመጨመር ሂደት እየታየበት ነው። ከዚህ አንጻር የሚቀጥሉት ዓመታት በቀላሉ የሚገፉ አይሆኑም። በተለይ በምዕራቡ ዓለም ቀውሱን ለመወጣት መዓት ገንዘብ ቢፈስም ይህ ብቻውን ፈውስ ሊሆን መቻሉ ያጠያይቃል። ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት በአዲስ መልክ ማቀናጀቱ ቁልፍ ነው የሚሆነው። ለዚሁ ዓላማ ባለፈው ታሕሣስ በዋሺንግተን የተጀመረውና በፊታችን ሚያዚያ የሚቀጥለው የቡድን-20 መንግሥታት የዓለም የፊናንስ ጉባዔ የአዳጊውን ዓለም ጥቅም ያጣመረ ለውጥን ለማስፈን ወደፊት መራመድ ይጠበቅበታል።
የሚፈለገው አቅጣጫ ወይም አዝማሚያ እንግዲህ ከቀውሱ በኋላ የሚኖረውን ስርዓት በአግባብ መቅረጽ ሲሆን የዳቮሱ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ መድረክ መሥራች ክላውስ ሽዋብ እንዳሉት የመድረኩ ጉባዔ ምናልባት የአሁኑን ያህል እጅግ ጠቃሚ የነበረበት ጊዜ የለም። እርግጥ የዳቮስ መድረክ አሣሪ ውሣኔዎች የሚተላለፉበት ቦታ አይደለም። ለወደፊቱ ዕርምጃዎች ጠቃሚ ሃሣቦችን ለማፍለቅ ግን አመቺው መድረክ ሊሆን ይችላል። የሆነው ሆኖ በዚህ በአዲሱ ዓመት የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ከመካሄዱ ከሶሥት ወራት በፊት ስርዓቱን በጥቂቱም ቢሆን ለማሻሻል አስተዋጽኦ ካደረገ ሽዋቭ እንደሚሉት ይህ ራሱ ትልቅ ዕርምጃ ነው የሚሆነው።

“ሁለት ጉዳዮችን ማከናወን ይኖርብናል። አንደኛው የቀውሱ አያያዝ ራሱ ሲሆን ሁለተኛው ከቀውሱ በኋላ የምትኖረውን ዓለም ይዞታ መቅረጽ ነው። ዓመኔታን መልሰን ልናሰፍን የምንችለው ከረጅም ጊዜ አንጻር ስናስብና ስንራመድ ብቻ ይሆናል። በኤኮኖሚ ስርዓታችንና በወደፊቱ ግባችን ላይ!”

በመድረኩ ላይ ትልቅ ተሥፋ የጣሉ ወገኖች ባይታጡም ጭብጥ ፍሬ መገኝቱን የሚጠራጠሩትም ጥቂቶች አይደሉም። የጸረ-ግሎባላይዜሺን ቡድን ባልደረባ የሆኑት አሌክሢስ ፓሣዳኪስ ለምሳሌ ከነዚሁ አንዱ ናቸው።

“ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ እንዴት እያደገ እንደመጣ ሲመለከቱት አሁን በዳቮስ የሚሰበሰቡት ወገኖች በትክክል የቀውሱ ተጠያቂዎች ናቸው። ሽክሙን በብልጽግናው ዘመን እንደነበረው ሁሉ አሁንም የዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ስርዓት ተጎጂ በሆኑት የሕብረተሰብ ቡድኖች ላይ የሚጭን መፍትሄ ለማግኘት ነው የሚጥሩት”

የዳቮሱ ኤኮኖሚ መድረክ ከወቅቱ የፊናንስ ቀውስ አንጻር የረባ ግፊት ሊያደርግ አይችልም ከሚሉት መካከል የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ድርጅት ቀደምት የኤኮኖሚ ባለሙያ ሃይነር ፍላስቤክም ይገኙበታል። የፊናንሱስ ቀውስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደርሳቸው አስተሳሰብ ጥብቅ የባንኮች ቁጥጥር ዘዴ ማስፈንንና ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ስርዓት ማረጋጋቱን ይጠይቃል። ግን ይህ በዳቮስ መድረክ የሚዳሰስ ሆኖ አይታያቸውም። “ከዳቮስ የሚወጣ አንዳች ነገር አይኖርም። የሚገባውም እንዲሁ ጥቂት ነው ለማለት እችላለሁ” ነው ያሉት።

ለማንኛውም የዳቮስ መድረክ ብዙ አስተያየቶች የሚንሸራሸሩበት እንደሚሆን አያጠያይቅም። ከተፈጥሮ ጥበቃ አንስቶ ቀጣይነት እስካለው ልማት ድረስ በርካታ ርዕሶች የሚነሱባቸው 57 ዙር የተለያዩ ውይይቶች ይካሄዳሉ። በተለይ በወቅቱ የኤኮኖሚ ሁኔታና በነጻው የገበያ ኤኮኖሚ ስርዓት ዕሴቶች ላይ የሚካሄዱት ሁለት የመድረክ ውይይቶች የጊዜውን ተጨባጭ ችግር በመታገሉ ረገድ ቁልፍ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው የሚችሉ እንደሚሆኑ ነው የሚታመነው። በታዛቢዎች አነጋገር በነዚህ መድረኮች ላይ ለሚነሱት ጥያቄዎች ጥሩ ምላሽ መስጠት ሲቻል ብቻ ነው የዳቮሱ መድረክ ዘንድሮ ለፊናንሱ ቀውስ መፍትሄ ቢቀር በጽንሰ-ሃሣብ ደረጃ አስተዋጽኦ አደረገ ለማለት የሚያስደፍረው።