የዳርፉር ግጭት፣ ዲፕሎማሲዉና አለም አቀፉ ፍርድ ቤት | አፍሪቃ | DW | 26.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዳርፉር ግጭት፣ ዲፕሎማሲዉና አለም አቀፉ ፍርድ ቤት

መከረኛዉ ሕዝብ መከራ እየተዘራለት-ይታጨድበታል።

የቻይና ወታደሮች በዳርፉር

የቻይና ወታደሮች በዳርፉር


በሱዳን ማዕከላዊ መንግሥት የሚደገፉት የጃንጃዊድ ሚሊሺያዎችና የዳርፉ አማፂያን የለየለየት ዉጊያ ከጀመሩ ዛሬ ስድስተኛ አመቱን ያዘ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ እስካሁን ባልበረደዉ ዉጊያ ሁለት መቶ ሺሕ ሰዉ ተገድሏል።በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተሰዷል ወይም ተፈናቅሏል።የግጭቱ ስድስተኛ አመት ሲታወስ የዩናይትድ ስቴትስና የቻይና ልዩ መልዕክተኞች ሱዳንን በመጎብኘት ላይ ናቸዉ።አለም አቀፉ የጦር ወንጀሎች ፍርድ ቤት ደግሞ በዳርፉር ሕዝብ ላይ ለተፈፀመዉ ግፍ ተጨማሪ ተጠርጣዊዎች ለመክሰስ አቅዷል።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝሩን አጠናክሮታል።

ለዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ በተደጋጋሚ እንዳስታወቁት «ዘር-ማጥፋት ነዉ።ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ አሳዛኝ ሰብአዊ ድቀት።የጦር ወንጀለኞችን የሚዳኘዉ ፍርድ ቤት በፋንታዉ በሕዝብ ላይ ለተፈፀመዉ በደል ተጠርጣሪዎች ካልተያዙ ሠላም አይኖርም ባይ ነዉ።

የሐገራት ሚንስትሮች፣ የአለም አቀፍ ድርጅት ዲፕሎማቶች፣ የርዳታ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ የፊልም ተዋኞች ሳይቀሩ ካርቱም፣ ዳርፉር፣ አዲስ አበባ፣ እንዣሚና፣ ስም የሌለዉን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ተመላልሰዉበታል።መከረኛዉ ሕዝብ መከራ እየተዘራለት-ይታጨድበታል።

የሱዳን መንግሥትና የግዛቲቱ አማፂያን የፈረሙትን የተኩስ አቁም ዉል ለማስከበር ዳርፉር የሰፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ሠላም ለማስከበር የገንዘብ፤ የሰዉ ሐይል፤ የሥልጠና አቅምና ብቃት የለዉም ከተባለ ለሁለት አመት ጥቂት ቀረዉ።ሠራዊቱ ከአፍሪቃና ከተቀረዉ አለም ሠራዊት በሚዉጣጣ ሌላ ቅይጥ ሠራዊት እንዲተካ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ከወሰነ ከረመ።ሰላም የለም።ቢኖርም የሚያስከብረዉ አልተገኘም።

አንዳድ ምዕራባዉያን ሐገራት እንደሚሉት አለም አቀፉ ሠራዊት ዳርፉር እንዳይሰፍ የካርቱም መንግሥት እያከላከለ ነዉ።የፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አልበሽር መንግሥት የሠራዊቱን መሥፈር እንቢኝ ለማለት የልብ ልብ የሰጠችዉ ደግሞ ተቺዎቹ እንደሚሉት የሱዳን የንግድ ሸሪክ ቻይና ናት።ትችት ወቀሳዉ ያየለባት ቤጂንግ ልዩ መልዕክተኛ ሊዩ ጉዩጂንን ወደ ካርቱም ልካለች።ከተቺ ወቃሾቹ የግንባር ቀደሟ የዋሽንግተን ልዩ መልዕክተኛ ሪቻርድ ዊሊያምሰንም እዚያዉ ካርቱም ናቸዉ።

ለዳርፉር ሠላም የቅርቡ ተስፋ የሁለቱ ሐገራት ልዩ መልዕክተኞች ካርቱም ምናልባትም ዳርፉር የሚሉ የሚያደርጉት ነዉ።መልዕክተኞቹ ከቤጂንግና ዋሽንግተኝ ከመነሳታቸዉ በፊት የአለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ሉዊስ ሞሬኖ-ኦካም ከአርጀንቲና ለዳርፉሩ ጥፋት ተጠርጣዊዎች ካልታሰሩ ሰላም አይኖርም ይላሉ።

አለም አቀፉ ፍርድ ቤት በዳርፉር ሕዝብ ላይ ለተፈፀመዉ ግፍ ግንባር ቀደም ተጠርጣሪ ያደረጋቸዉ የሱዳን የሰብአዊ ጉዳይ ሚንስትር ደ ኤታ አሕመድ ሐሩን፣ የጃንጃዊድ ሚሊሺያ መሪ አሊ ኮሸይብና አንድ ሌላ ሹም ለፍርድ እንዲቀርቡ የእስራት ዋራንት የቆረጠዉ ባለፈዉ አመት ግንቦት ነበር።እስካሁን ማንም አልያዛቸዉም።ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሞሬኖ-ኦካም ሌሎች የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለማስያዝ ሌላ የእስር ደብዳቤ እያዘጋጁ መሆናቸዉ አስታዉቀዋል።የመጀመሪያዎቹ ሳይያዙ ሁለተኞቹ መከሰሳቸዉ እንዳነጋገረ-ዳርፉሮች የጥፋት አመት ሸኝተዉ ሌላ አመት ተቀበሉ።ዛሬ።