የዳርፉር ሠላም፣የ ሱዳንና የቻድ ዉዝግብ | የጋዜጦች አምድ | DW | 07.02.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የዳርፉር ሠላም፣የ ሱዳንና የቻድ ዉዝግብ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዳርፉር ሊያሠፍረዉ ያቀደዉ ሠራዊት እስካሁን ለአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ከሚወጣዉ ከአራት እስከ አምስት እጥፍ የሚደርስ ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል።


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ግጭት ባየለባት የምዕራባዊ ሱዳን-ግዛት ዳርፉር እንዳይሰፍር ሥትቃወም የነበረችዉ ሱዳን አቋሟን እያለሳለሰች ነዉ።የሱዳን ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀዉ የካርቱም መንግሥት አለም አቀፍ ሠራዊት ዳርፉር ሥለሚሰፍርበት ሁኔታ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር መደራደር ይፈልጋል እንጂ ሠራዊት መስፈሩን አይቃወምም። በሌላ በኩል በዳርፉር ግጭት ሰበብ እየከፋ የመጣዉን የሱዳንና የቻድን ጠብ ለማርገብ የአካባቢዉ ሐገራት መሪዎች ነገ ትሪፖሊ-ሊቢያ ዉስጥ ይነጋገራሉ።

የዳርፉር ተፋላሚ ሐይላት የተፈራረሙትን የተኩስ አቁም ሥምምነት ለማስከበር አለም አቀፍ ሠራዊት እንዲዘምት ምዕራባዉያን ሐገራት በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችዉን ጥያቄ የካርቱም መንግሥት አጥብቆ ሲቃወመዉ ነበር።የሱዳን መንግሥት የደቡባዊ ሱዳንን ጦርነት ለማስቆም ከዋነኛዉ አማፂ ቡድን ጋር የተፈራረመዉን የሠላም ዉል የሚያስከብር አለም አቀፍ ሠራዊት ደቡብ ሱዳን መስፈሩን ተቀብሎ ምዕራባዊ ሱዳን መስፈሩን መቃወሙ ለዉጪዉ ታዛቢ እንቆቆልሽ እንደሆነ ነበር።

የሱዳን ባለሥልጣናት ግን በቂ ምክንያት አለን ባዮች ናቸዉ።የዳርፉር ዉጊያ እንደ ደቡቡ ባለመክፋቱ፤ የዉጪዉ ሠራዊት በገለልተኝነት ሠላም ከማስከበር በላይ ለአማፂያኑ ብርታትና ጥንካሬ የሚሆን እርምጃ ይወሰዳል ብለዉ መጠርጠራቸዉ አሳማኝ ከሚሏቸዉ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸዉ።ወይም ነበሩ።የአፍሪቃ ሕብረትም ራሱ ያፈራረመዉን ዉል ለማከበር ከሕብረቱ ሠራዊት ሌላ አለም አቀፍ ሠራዊት ማዝመት እንደማያስፈልግ ሲከራከር ነበር።

እስካሁን ዳርፉር የሠፈረዉን ሰባት ሺሕ የአፍሪቃ ሠራዊት ወጪ የሚሸፍኑት ግን አለም አቀፍ ሠራዊት እንዲዘምት የሚገፋፉት ለጋሽ ሐገራት ናቸዉ።ለጋሾቹ ወትሮም ሳይፈልጉ ለተቀበሉት ለአፍሪቃ ሠራዊት የሚሠጡን ገንዘብ በሰበብ አስባቡ አጓትተዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራዊት እንዲያዘምት ዳግም እየገፋፉ ነዉ።የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናንም ድርጅታቸዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ተልዕኮን እንዲረከብ በቅርቡ ጠይቀዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት በኮፊ አናን በኩል የቀረበዉን ጥያቄና ግፊት በመርሕ ደረጃ መቀበሉን ሰሞኑን አስታዉቋል።የመጨረሻ ዉሳኔ የሚሰጠዉ ግን በመጪዉ መጋቢት ነዉ።እስካሁን ድረስ አለም አቀፍ ሠራዊት እንዳይሰፍር ለመቃወሟ የአፍሪቃ ሕብረት ድጋፍ ያልተለያት ሱዳን ጥያቄዉን ሕብረቱ ወደመቀበሉ ሲያዘነብል ተቃዉሞዋን ከማለሳለስ ሌላ ምርጫ የላትም።የሱዳን የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አል-ሰማኒ አል ዋሲያላሕ ትናንት እንዳሉት መንግስታቸዉ አለም አቀፍ ሠራዊት ሥለሚሰፍርበት ሁኔታ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ለመደራደር ይፈልጋል።የሱዳን መንግስት እንደራደር ማለቱ ዋሲያላሕ እንዳሉት አለም አቀፉን ሠራዊት አልቀበልም ማለት ግን አይደለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዳርፉር ሊያሠፍረዉ ያቀደዉ ሠራዊት እስካሁን ለአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ከሚወጣዉ ከአራት እስከ አምስት እጥፍ የሚደርስ ተጨማሪ ወጪ ይጠይቃል።ትንሹን ወጪ ለመክፈል የሚያቅማሙት ለጋሽ ሐገራት በአራት-አምስት እጥፍ የሚበልጥ ገንዘብ ለማፍሰስ የፈለጉበት ምክንያት ለብዙ ታዛቢዎች በርግጥ ግራ ነዉ።ለሱዳኖች ደግሞ ሚንስትር ዴኤታ ዋሲያላሕ እንዳሉት «ለጋሾች ሌላ አለማ እንዳላቸዉ» ቢያንስ የሚጠቁም ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሞበታል ባለችዉ በዳርፉር ጦርነት ሰወስት መቶ ሺሕ ያሕል ሕዝብ መገደሉ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ መፈናቀል ወይም መሰደዱ ይታመናል።የዳርፉር መዘዝ በርካታ ሥደተኞችን በምታስተናግዳዉ ቻድና በሱዳን መካካል አዲስ ጠብ ቀስቅሷል።ካርቱም፣ ቻድ የዳርፉር አማፂያንን ትረዳለች በማለት ስትወነቅስ፣ ኢንጃሚና ባንፃሩ ሱዳን የቻድ መንግስት ተቃዋሚዎችን ታስጣቅለች በማለት ትወነጅለለች።መወነጃጀሉ ተካርሮ ሁለቱን ሐገሮች በቀጥታ ጦር እንዳያማዝዝ የፈሩት የተጎራባች ሐገራት ባለሥልጣናት ትሪፖሊ-ሊቢያ ዉስጥ ሽምግልና ተቀምጠዋል።

በሊቢያ ጋባዥነት ትናንት በጉዳዩ ላይ የተነጋገሩት የራስዋ የሊቢያ፣ የቡርኪናፋሶ፣ የወቅቱ የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር የኮንጎ ሪፐብሊክ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ከቻድና ከሱዳን አቻዎቻቸዉ ጋር ያደረጉት ዉይይት፣-የሊቢያ ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አብድል ሠላም ትሪኪ እንዳሉት ገንቢ ነዉ።ሚንስትሮቹ ጥሩ ባሉት ዉይይት ዉጤት ላይ ለመነጋገር የአምስቱ ሐገራት መሪዎች ነገ-እዚያዉ ሊቢያ ለመሰብሰብ ቀጠሮ አላቸዉ።