የዳርፉርን ችግር ለማስቆም የተካሄደዉ ሰልፍ | አፍሪቃ | DW | 30.04.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዳርፉርን ችግር ለማስቆም የተካሄደዉ ሰልፍ

በዳርፉር የሚፈፀመዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዲቆየም የጠየቀ ሰላማዊ ሰልፍ በትናንትናዉ ዕለት በበርካታ ሀገራት ከተሞች ተካሄደ።

የሎንዶኑ ሰልፍ በከፊል

የሎንዶኑ ሰልፍ በከፊል

እዚህ ጀርመን በርሊን ከተማ በተካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተካፈሉት ለእኩለ ሌሊት አምስት ደቂቃ ብቻ ቀርቷል፤ ማንቂያዉን ደወል ይዘን መጥተናል የሚል ባለ ደውል ሰዓት ያለበት መፈክር ይዘዉ ነበር የታዩት። በዳርፉር ‘የታየ ያለዉ ሰብዓዊ ቀዉስ የማይታጠፍ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችልም በአፅንዖት አሳስበዋል። የተገፉ ማህበሰቦች የመብት ተሟጋች በሆነዉ ድርጅት የአፍሪቃ ጉዳይ ተንታኝ ዑልሪሽ ዴሊዩስ የዘር ማጥፋትና የጎሳ እልቂት በምዕራባዊ ሱዳን ግዛት በዳርፉር እየተፈፀመ ነዉ ይላሉ


«የዘር ማጥፋት፤ አንድን ጎሳ ነጥሎ መፍጀት እንዲሁም መጠነሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ናቸዉ በአሁኑ ሰዓት በምዕራባዊ ዳርፉር በእርግጥ እየተፈፀሙ የሚያገኙት ችግሮች።»

በለንደን ደግሞ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰልፈኞች ወደጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ፅህፈት ቤት በመሄድ ጥሪያቸዉን ያካተተ ደብዳቤ ሰጥተዋል። የመብት ሰሟጋቾችም በዉስጡ ደም መሰል ፈሳሽ ያለበት ሁለት ሜትር ርዝማኔ ያለዉ ብርጭቆ አቁመዋል። እርምጃቸዉን በመደገፍም ከአገሪቱ ገዢ ሌበር ፓርቲ ስምንት ፖለቲከኞች መግለጫ አዉጥተዋል። ፖለቲከኞቹ ብሌየር በያዝነዉ ዓመት መገባደጃ የስልጣን ዘመናቸዉ ሲያከትም ለመሪነትና ለረዳትነት የሚወዳደሩ ይሆናሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ በተመሳሳይ መልኩ የተካሄደዉን ሰልፍ የመራችዉ ታዋቂዋ አርቲስት ማያ ፋሮዉ በኋይት ሃዉስ ደጃፍ በመቆም የአገሪቱ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ የመንግስታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይሉን ወደዳርፉር ባስቸኳይ እንዲልክ ድጋፋቸዉን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አሰምቷል። የመብት ተሟጋቿ አርቲስት ዳርፉርን አድኑ የሚል ፅሁፍ የተፃፈበት ቲ-ሸርት በመልበስ የመንግስታቱን ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሰማያዊ ክብ ኮፍያ ላጠለቁት ተሰላፊዎች ባደረገችዉ ንግግር ቡሽና ቻይና በዳርፉር የሚፈሰዉን ደም ማስቆም አልቻሉም ስትል ወቅሳለች።

በዳርፉር በሚገኙ መጠለያ ስፍራዎችና መንደሮች ሰላምን ጥበቃ አሁን ሊደረግ የሚገባዉ ተገቢ ምላሽ ነዉ። የስነምግባር ማሳያም ነዉ ብላለች። ጨምራም ፕሬዝደንት ቡሽ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸዉ ጥቀዋል፤ ያን እሳት ዉስጥ ልጆቿ ለገቡባት እናት የሚሰጥ ምላሽ ነዉ ስትልም ጠይቃለች። የዘር ማጥፋት ኦሎምፒክ የሚል ፅሁፍ ያለበት ቡናማ ቲ-ሸርት ለብሳ የታየችዉ ይቺዉ አርቲስት በቤጂን የሚካሄደዉ የ2008ዓ.ም ኦሎምፒክ ቻይና ሱዳን ላይ ማዕቀብ እንድትጥል ጫና የሚያሳድር አንድ መንገድ መሆኑን ገልፃ ወቅቱ ለዚህ ቅስቀሳ እንደሚዉል ተናግራለች። ቻይና ለልማት እድገቷ በከፍተኛ ደረጃ የምትፈልገዉ የነዳጅ ምርት በዳርፉር ለሚካሄደዉ የሰዉ ዘር ማጥፋት ድርጊት ጆሮ እንዳትሰጥ እንዳደረጋትም ጠቅሳለች።

ተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፎችም በብራስልስ፤ በስኮሆልምና በቡዳፔስት ከተሞች ተካሂደዋል። አዘጋጆቹ እንደሚሉት በናይጀሪያ ሌጎስና በሜልቦርና አዉስትራሊያም ይቀጥላል። እለቱን በማስመልከትም ኤልቶን ጆን፤ ጆርጅ ክሎኒ፤ ቦብ ጌልዶፍ፤ ማይክ ጃገር እና ሁግ ግራንት ከሌሎች አርቲስቶችና የሙዚቃ ባለሙያዎችና በመሆን ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ግጭቱን ከማስቆም ወሳኝ እርምጃ ይዉሰድ የሚል መግለጫ አዉጥተዋል።

እስራኤሉ ያድ ቫሽም የሆሎኮስት እልቂት መታሰቢያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባን ጊ ሙን በላከዉ ደብዳቤ ወደዳርፉር ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመላክ ተጨባጭ እርምጃ መሰድ እንዳለበት አሳስቧል። ጨምሮም በሆሎኮስት ላለቁት የአይሁድ ህዝቦች መታሰቢያ የቆመ ማዕከላዊ ድርጅትነቱ ሆሎኮስት ሲፈፀምና የሰዉ ዘር ሲጠፋ ዓለም ዝም ብሎ እንደነበር በማስታወስ፤ በዳርፉር የሚፈፀመዉ እንዲቆም ማስጠንቀቂያ የማሰማት ሃላፊነት አለብን ብሏል።

በቅርብ ሳምንታት ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታያን ለሱዳን ኦማር አልበሺር አስተዳደር ያሳዩት ትዕግስት እያለወ መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን በያዝነዉ ወር መጀመሪያ ገደማ ቡሽ ባን ጊ ሙን ለሚያደርጉት የዲፕሎማሲ ጥረት ጊዜ ለመስጠት ማዕቀቡ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አድርገዋል። ምንም እንኳን ባሺር በአሁኑ ሰዓት 3ሺ የሚደርሱ የመንግስታቱን ባለ ሰማያዊ ቆብ ወታደሮች የተዳከመዉን የአፍሪቃ ህብረት ኃይል እንዲያጠናክሩ ቢፈቅዱም መሰረታዊ የተባሉ ነጥቦችን መቃወማቸዉ ይታወሳል።

የዳርፉር ቀዉስ እልባት ያግኝ በሚል በበርካታ ሀገራት ከተሞች የተካሄደዉ ሰላማዊ ሰልፍ የተዘጋጀዉ ለሰብዓዊ መብት በሚሟገቱት ሁለት ድርጅቶች ማለትም Amnesty International እና Human Rights Watch አስተባባሪነት ነዉ። ሎንዶን የሚገኘዉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ካቴ አለን በቃ ማለት በቃ ነዉ! አሁን ሌላዉ የዓለም ህብረተሰብ ትርጉም ያለዉ እርምጃ መዉሰድ ያለበት ሰዓት ላይ ነን ማለታቸዉ ተጥቅሷል።