የዲፕሎማቱ የማይቻል ተልዕኮ | ዓለም | DW | 14.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የዲፕሎማቱ የማይቻል ተልዕኮ

እንደ ጦርነት፤ ግጭት፤ሽብሩ ሁሉ ድርድር፤ ዉይይት፤የድርድር ዕቅድ ቃል ተስፋዉ በርግጥ ያን ምድር አልተለየዉም።የቤራንዲዶት ዕቅድ፤የሮጀር ዕቅድ፤የአሎን ዕቅድ፤የካምፕ ዴቪድ ዉል፤የፈሕድ ዕቅድ፤ የማድሪድ ጉባኤ፤የኦስሎ ስምምነት፤ እየተባለ በሥልሳ-ሰባት ዓመት ዉስጥ ሰላሳ-አንድ የሠላም ዕቅዶች፤ ሥምምነቶች ወይም የመፍትሔ ሐሳቦች ተሠንዝረዋል።

ዓለም ጎል ሲቆጥር-ኢራቅ፤ ሶሪያ ፍልስጤም አስከሬን፤ እስራኤል ሮኬት ይቆጥራሉ።ጋዛ እንደገና ትነዳለች።ነዳ፤ ከስል-አመድ ሆና ካለቀች-አንዳጆችዋ የሚያነዱት ሌላ እስኪያገኙ መቦዘን አይፈልጉም።ከሠሏን ሊያነዱእያነደዱ፤ አመድ ሆና እንዳታልቅ ይተዋታል።ቴል አቪቭ፤ እየሩሳሌምእንደገና ይተራመሳሉ።ተተረማምሰዉ ከተመሰቃቀሉ አተራማሾቻቸዉ-የሚያተረማምሱት ሌላ ሥለማያገኙ አተራምሰዉ ይተዋቸዋል።ፍልስጤም በርግጥ ያልቃል።አይሁድ ይሸማቀቃል።መካከለኛዉ ምሥራቅ ለዓመት ግብሩ የአረብደም ሲርከፈከፍለት፤ አይሁድ በድንጋጤ ሲደለቅለትተስፋ-የማያዉቀዉ ተስፈኛ ምድር ቢያንስ ለሶሪያ አዲስ ተስፋ ተነገረለት።የሠላም አደራዳሪ ተሾመላት።የእልቂቱ አዙሪት፤ የተሿሚዉ ማንነት፤የተስፋ-ቀቢፀ ተስፋዉ ተቃርኖው እንዴት ነው?

በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት መሐል-ጦርነቱ ካሰደዳቸዉ ቤተሰቦች-በስደት የተወለዱት አንጋፋ ዲፕሎማት ልክ-ከጦርነት እንዳልተለየዉ፤ ተስፋ-እንደማያዉቀዉ ግን ደግሞ እንደ ተስፋዉ ምድር ተስፈኛ ናቸዉ።ስቴፋን ዶሚንጎ ዲ ሚስትቱራ።«ከእያንዳዱ ቀዉስ ጀርባ በጎ ዕድል አለ» ይላሉ የሥልሳ-ሰባት አመቱ አዛዉንት።

«ከሙያዬ እንደተማርኩት ተስፈኛ ነኝ።እያንዳዱ ቀዉስ መልካም አጋጣሚም አለዉ»ንደ ሶሪያ ኢራቅ ጦርነት ሁሉ፤ዛሬ ለሰባተኛ ቀን ጋዛን-የሚያነደዉ፤ ደቡባዊ እስራኤልን የሚያስደነግጠዉ ጥፋት እንዲቆም የዋሽግተን ብራስልስ ፖለቲከኞች መጠየቅ ማሳሳባቸዉ አልቀረም።የአረብ-ዲፕሎማት ፖለቲከኞች ከካይሮ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መልዕክተኞች ከኒዮርክ ሥለጉዳዩ መከርን-ዘከርን ወይም እንመክራለን እያሉ ነዉ።

የሐያሉ ዓለም የፖለቲካ-ዲፕሎማሲ መልዕክት በጥቅም ሚዛን እየተለካ-የሚነገር፤ የደካሞቹ ምክር ዝክር በሀያላኑ ቁጣ-ፈገግታ እይተመጠነ በሥጋት ፍራቻ-የሚባል የሚደረግ መሆኑ እንጂ ቀቢፅ ተስፋዉ።ደፍሮ «ሐይ» የሚላቸዉ እንደሌለ እርግጠኛ የሆኑት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም ትናንት እንዳሉት እንደ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሚያዙት ጦር ጋዛ ላይ አዲስ የከፈተዉ ጥቃት የሚያበቀባትን ጊዜ አያዉቁትም።

«ይሕ ዘመቻ የሚያበቃበትን ጊዜ አናዉቅም።ረጅም ጊዜ ይጠይቅ ይሆናል።የናንተን (የሕዝቡን) ድጋፍና ዲሲፒሊን እንፈልጋለን።»ተስፈኛዉ ዲፕሎማት እንዳሉት ከያንዳዱ ቀዉስ ጀርባ መልካም እድል ይኖር ይሆናል።የመከከለኛዉ ምሥራቅ ጦርነት፤ ግጭት-ዉዝግብ፤ ቀዉስ ከዘመን ዘመን ዞሮ-የሚገጥም በመሆኑ ከቀዉሱ ጀርባ ያለዉን ተስፋ-ማየት ቀርቶ ቀዉሱ ራሱ ጀርባ የሌለዉ መሆኑ ቢያንስ መምሰሉ ነዉ ጭንቁ።የቀዉሱ አራማጆች ራሳቸዉ ቀዉሱ የሚቆምበት ሥልትና ጊዜ አለማወቃቸዉን ማሳወቃቸዉ ነዉ-ግራዉ።

ደ ሚስቱራ ጦርነትን ሽሽት ከተሰደዱ ኢጣላዊ አባት እና ሲዊድናዊት እናት ስቶክሆልም-ሲዊድን በተወለዱበት ዓመት፤ የስደተኞቹ ምድር በዩናትድ ስቴትስና በብሪታንያ ግፊት ኒዮርክ-ዩናትድ ስቴትስ ላይ «ተጠነሰሰች።» እስራኤል። ባመቱ ቴል አቪቭ ላይ ተወለደች።1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ)

ደ ሚስቱራ የጦርነት ትቢያዋን እያራገፈች-ከዘግናኝ ጦርነት ብዙ ተምራ ለጋራ ሠላም ብልፅግና በምትዳክረዉ አዉሮጳ መሐል ሲያድጉ አዲስ ሐገር የተወለደችለት መካከለኛዉ ምሥራቅ ባንፃሩ ባዲስ ጦርነት-ግጭት፤ዉዝግብ ሥደት ይሠምጥ ያዘ። ሕዝቡ በሳት ባሕር ይዋኝ ገባ።

እንደ ጦርነት፤ ግጭት፤ሽብሩ ሁሉ ድርድር፤ ዉይይት፤የድርድር ዕቅድ ቃል ተስፋዉ በርግጥ ያን ምድር አልተለየዉም።የካዉንት ቤራንዲዶት-የሠላም ዕቅድ፤የጄሪግ ተልዕኮ፤የሮጀር ዕቅድ፤የአሎን ዕቅድ፤የካምፕ ዴቪድ ዉል፤የሬጋን ዕቅድ፤ የፈሕድ ዕቅድ፤ የማድሪድ ጉባኤ፤የኦስሎ ስምምነት፤የዌይ ሪቭር መግባቢያ እየተባለ በሥልሳ-ሰባት ዓመት ዉስጥ ሰላሳ-አንድ የሠላም ዕቅዶች፤ ሥምምነቶች ወይም የመፍትሔ ሐሳቦች ተሠንዝረዋል።

ከሠላሳ አንዱ ዕቅድ-ወይም ሐሳቦች ከሰወስቱ በስተቀር ከሚዋጉ፤ከሚጋጩት ሐይላት የፈለቀ የለም።የተቀረዉ በሙሉ የአሜሪካኖች በአሜሪካኖች በኩል የአዉሮጶች ነዉ።ተፋላሚ ሐይላት እኩል የተደራደሩበት፤ ሠጥቶ መቀበል የተንፀባረቀበት፤ ምናልባትም እኩል የተቀበሉት የሚመስለዉ አንድ ብቻ ነዉ።የ1979ኙ የካምፕ ዴቪድ ሥምምነት።

ከባለ ጉዳዮች ያልፈለቀ ወይም ባለጉዳዮችን እኩል የማያስተናግድ፤ ሠጥቶ በመቀበል መርሕ ላይ ያልተመሠረት ሐሳብ፤ ድርድር፤ ዕቅድ፤ ሥምምነት በየዘመኑ የተነሱ ሕዝባዊ ጥያቄዎችንና ግፊቶችን ከማስተንፈስ ባለፍ ለዉጤት እንደማይበቃ በየዘመኑ ይታወቅ ነበር።ሥልሳ-ሰባት ዓመቱ።

የሥልሳ-ሰባት ዓመቱ ኢጣሊያዊ ዲፕሎማት ባለፈዉ ሳምንት የተሾሙት በሥልሳ-ሰባት ዓመቱ ጦርነት ግጭት -ያልተለየችዉን ያክል ባብዛኛዉ ድርድር፤ ዉይይት፤ የሠላም ዕቅድ ምዕራባዉያን ለሚያገልሏት ሐገር ሠላም እንዲያወርዱ ነዉ።ለሶሪያ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን የደሚስቱራን ሹመት ሲያውጁ እንዳሉት ለሶሪያዉ ቀዉስ መፍትሔ ለመፈለግ የዲፕሎማቶችን ልዩ ችሎታ፤ ጥበብና ክሂልን ይጠይቃል።

«ይሕ የልዩ መልዕክተኝነት ሐላፊነት ከኮፊ አናን እስከ ላሕዳር ብራሒሚ እስከ ስቴፋን ደ ሚስቱራ ላለ ለማንኛዉም ሰዉ በጣም የበሠለ ዲፕሎማሲያዊ ክሒሎትንና ጥረትን ይጠይቃል።እንደ ምታዉቁት ስቴፋን ደ ሚስቱራ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየሰሩ ነዉ።ኢራቅንና አፍቃኒስታንን በመሳሰሉ አስቸጋሪ አካባቢዎች ልዩ መልዕክተኛ ሆነዉ ሠርተዋል።»

ሰዉዬዉ በርግጥም-ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲን ጥራሳቸዉን ነቅለዉበታል።ዓለም አቀፉን ድርጅት ከተቀየጡ አርባ አመታቸዉ።በዚሕ ረጅም ዘመን ፓን ከጠቀሷቸዉ ሐገራት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ እስከ ቬትናም፤ ከሱዳን እስከ ቦልካን፤ ከሶማሊያ እስከ ሊባኖስ የነበሩና ያሉ ቀዉሶችን ለማርገብ ዓለም አቀፉን ድርጅት ወክለዉ ሠርተዋል።ሰባት ቋንቋ ይናገሩ።የብዙ አካባቢዎችን ባሕል ያዉቃሉ።

ይሁንና የፒለቲካ ተንታኞች እንደሚስማሙበት የሶሪያ፤ የኢራቅ፤ የሊባኖስ ይሁን የፍልስጤም እስራኤል ቀዉስ አንዱ ከሌላዉ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነዉ።የደ ሚስቱራ ይሁን የሌሎች ብጤዎቻቸዉ ጥረት ኢራቅና ሊባኖስን ከግጭት ጦርነት አለማላቀቁም የዚያ አካባቢ ቀዉስ አንዱ የሌላዉ ምክንያት ወይም ዉጤት መሆኑን አመልካች፤ ቀዉሱን ከመፍጠር-የቀዉስ ሰብብ እስከማዘጋጀት የሐያላኑ እጅ እስከ ጠገጉ ድረስ የተነከረበት መሆኑን መስካሪ ነዉ።

ባለፉት ሰወስት ዓመታት እንደታየዉም የሶሪያዉን ጦርነት ከእስራኤል-እስከ ፍልስጤም፤ ከሳዑዲ አረቢያ-እስከ ኢራን፤ ከኢራቅ-እስከ ቱርክ የሚገኙ ያካባቢዉ ሐገራት «ይምቦራጨቁበታል።» ከዋሽግትን እስከ ሞስኮ፤ ከብራስልስ እስከ ቤጂንግ የሚገኙ ተቀናቃኝ ሐያላን በቀጥታም በእጅ አዙርም ይዘዉሩታል።

ጀርመናዊዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ አጥኚ ሚሻኤል ሉደርስ ሥም-ሁነት ጠቅሰዉ እዉነቱን ይናገራሉ።

«ተፋላሚዎችን የሚረዱ የዉጪ ሐይላት ዝግጁ ሆነዉ ቢሆን ኖሩ ይሕን የሶሪያን ጦርነት በዲፕሎማሲ መፍታት በተቻለ ነበር።ዩናይትድ ስቴትስና ሩሲያ፤ ሳዑዲ አረቢያና ኢራን ግጭቱን ለመፍታት ዝግጁ ከሆኑ መፍቴሔዉ አይገድም።አሁን ግን የሚታይ ነገር የለም።እንዲሕ አይነቱን የተወሳሰበ ቀዉስ ለመፍታት የዉጪ አደራዳዳሪ ሊያደርግ የሚችለዉ (የቀዉሱን ዘዋሪዎች) ፍላጎት ማስናገድ ብቻ ነዉ።»

ኮፊ አናን እና ላሕዳር ብራሒሚ በየተራቸዉ የልዩ መልዕክተኝነቱን ሐላፊነት «በበቃኝ» የተወቱም የሶሪያዉን ጦርነት ከሌላዉ የአካባቢዉ ብጤዉ መነጠል ሥላልቻሉ፤ የቀዉሱ ዘዋሪዎችን ፍቃድና ይሁንታም ሥለተነፈጉ ነዉ።

ጋዛን ከሚያነደዉ፤ ቴል አቪቭን ከሚያስደነግጠዉ፤ ኢራቅን ከሚያሸብረዉ፤ ደቡብባዊ ሊባኖስን ከሚያሠጋዉ ጦርነት፤ ግጭት፤ ዉዝግብ፤ ሸፍጥ፤ ክሕደት፤ሴራ መሐል-የሶሪያን መርጦ ሠላም ማዉረድ ከባድ ነዉ። እስራኤል እየፎከረች፤ ሐማስ እየዛተ፤ ዋሽግተን፤ ብራስልሶች፤ ሪያድ፤ዶሐ አንካራዎች አማፂያንን፤ ሞስኮ-ቴሕራኖች የደማስቆ ገዢዎችን እያስታጠቁ የደ ሚስቱራ የሠላም ተልዕኮ፤ በደ ሚስቱራ ችሎታ፤ ፍላጎትና ምኞት ብቻ ለዉጤት ይበቃል ብሎ ማሰብ አንድም የዋሕነት አለያም ጅልነት ወይም ማጭበርበር ነዉ።

በፖለቲካ እጥኚ ሉደርስ አገላለፅ ደግሞ «ሚሽን ኢምፖሲብል»-የማይቻል ተልዕኮ።«ይሕ (ተልዕኮዉ) በመሠረቱ የማይቻል ተልዕኮ ነዉ።ያም ሆኖ ሰዎቹን የሚያነጋግር የሆነ ሰዉ መኖሩ፤ ከምንም ይሻላል።»

የግጭት ጦርነቱ ዘዋሪዎች የሠላም ተልዕኮዉን እንዲቻል እስኪያደርጉት የሶሪያ፤ የፍልስጤም፤ የኢራቅ ይሁን የሊባኖስ ሕዝብ ከምንም የሚሻል ቸሮታቸዉን እያደነቀ በተስፋ አለያም አስከሬን-ቁስለኛዉን እየቆጠረ-አንድም ቁስለኛ፤ እስከሬን ወይም ስደተኛ እስኪሆን በቀቢፀ-ተስፋ መጠበቅ ወይም ምንም የማይታወቅ ምርጫን ምንም በማይታወቅ ተስፋ መፈለግ ግዱ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ


Audios and videos on the topic