የዲፕሎማሲ ድል | ዓለም | DW | 18.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የዲፕሎማሲ ድል

ከኦቦማ እስከ ኬሪ፤ ከሩሐኒ እስከ ዛሪፍ፤ ያሉ መሪ እና ዲፕሎማቶች እንደመሠከሩት ጠመንጃ ያማዘዘዉ ጠብ በዲፕሎማሲ መርገቡ ሠላም ለማያዉቀዉ የዓለም መሪ፤የጦር አዛዥ ዓለምን በሠላማዊ መንገድ ከሠላም ማስተዋወቅ እንደሚቻል ጥሩ አብነት ነዉ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:41

የዲፕሎማሲ ድል

«ኢራን ግዴታዋን በመወጣትዋ ከኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር ጋር የተገናኙ የወል እና የተናጥል የምጣኔ ሐብት እና የገንዘብ ማዕቀቦች ዛሬ ተነስተዋል።»

የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ሐላፊ ወይዘሮ ፌደሪካ ሞግሔሪኒ-ቅዳሜ።ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ለማቋረጥ የገባችዉን ቃል ገቢር ማድረጓ ተረጋገጠ።በኑክሌር መርሐ-ግብሩ ሰበብ በኢራን ላይ ተጥሎ የነበረዉ ማዕቀብም ተነሳ።የቴሕራን፤ ዋሽግተን፤ ብራስልስ ጠላቶች እኩል ተደሰቱ።ከእንግዲሕስ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

የኢራኑ ንጉስ መሐመድ ሬዛ ሻሕ ፓሕላቪ ዙፋናቸዉን ከሐይማኖት መሪዎች ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ ለማለቀቅ በ1963 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሮሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) «ነጩ አብዮት» ያሉትን የለዉጥ ደንብ ሲያዉጁ ዘዉዳዊ አገዛዛቸዉን ወደ ፍፃሜዉ እየገፉት መሆኑን የተረዳ ብዙ አልነበረም።ነጩ አብዮት ያስነሳዉ አቧራ ሳይረጋ፤ ኢራን የሠፈሩ የአሜሪካ ወታደሮች ኢራን ዉስጥ እና በኢራናዉያን ላይ ወንጀል ቢፈፅሙ አሜሪካ ጦር ሠፈር እና በአሜሪካ ሕግ እንዲዳኙ ንጉሱ ተስማሙ።

ሻሑን ወትሮም «ደካማ፤ ችግር ፈጣሪና አድርባይ» እያሉ የሚቃወሟቸዉ የኢራን ብሔረተኞችና መንፈሳዊ መሪዎች ሻሑ ለአሜሪካኖች መንበርከካቸዉን የጥንታዊቱን ሐያል፤ሥልጡን ሐገር ክብርን ያዋረደ፤ልዑላዊነቷን አሳልፎ የሰጠ እና ሕዝቧን የናቀ አድርገዉ ነዉ ያዩት።

«ለሐይማኖት ያልወገኑ» በሚባሉት ንጉስ አገዛዝ የተማረረዉ፤የሐገሪቱ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ልሒቅ ሻሑ «ነጩ አብዮት» ያሉትን ደንብ እና የ"capitulations" ሕግ ወይም «የጦር ሐይላት ይዞታ የተሰኘዉን ሥምምነት አከታትለዉ ሲያዉጁ ሕዝቡን በአጋዛዙ ላይ ለማሳመፅ ጥሩ አጋጣሚ ነበር የሆነዉ።

ተቃዉሞዉ ከሻሑ አጋዛዝ አልፎ ሻሁን ለሥልጣን ባበቁት በዩናይትድ ስቴትስና በብሪታንያ ላይም ያነጣጠረ ነበር።ጠንካራዉ ተቃዉሞ እና ዉግዘት የተሰማዉ ደግሞ ከኢራን ዑለማዎች (የሐይማኖት አዋቂዎች) ማሕበር ነበር።

የዑለማዎቹ መሪ የኋላዉ አያቱላሕ ሩሆላሕ ሙስተፋቪ ሙሳቪ ኾሚኒ ጥቅምት 26 1964 ሻሁን የኢራንና «ጠላት»፤ ዩናይትድ ስቴትስን ደግሞ የ«ኢራን አጥፊ» በማለት አወገዙ።ኾሚኒ ስድስት ወር ታስረዉ ሲፈቱ ከጠቅላይ ሚንስትር ሐሰን መንሱር ፊት ቀርበዉ ይቅርታ እንዲጠይቁ ቢጠየቁ ዉግዘቱን ደገሙት።

ያኔ 62 ዓመታቸዉ ነበር።በኾሚኒ አፀፋ የተናደዱት ጠቅላይ ሚንስትር አዛዉንቱን መንፈሳዊ መሪ በጥፊ አጮሏቸዉ።ሻሕ ፓሕሌቪ የያኔዉን የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ፈይሰልን ለማስተናገድ ቴሕራንን ሲያፀዱ ጠቅላይ ሚንስትራቸዉ በጥይት ተደብድበዉ ተገደሉ።ሆሚኒም በሻሑ አገዛዝ፤ በዩናይትድ ስቴትስና በተባባሪዎችዋ ላይ እንዳቄሙ መጀመሪያ ወደ ቱርክ፤ ቀጥለዉ ወደ ኢራቅ አሰልሰዉ ወደ ፈረንሳይ ተሰደዱ።

ኾሚኒ ከተሰደዱበት ሆነዉ የመሩና ያቀነባበሩት እስላማዊ አብዮት የሻሑን ዙፋናዊ አገዛዝ ሲገረስስ ዩናይትድ ስቴትስ ለቀድሞ ታማኝ አገልጋይዋን ጠንካራ ድጋፍ ስትሰጥ ወትሮም በጠላትነት በፈረጇት እስላማዊ አብዮተኞች ዘንድ «ታላቅዋ ሰይጣን» የሚል እርግማን አተረፈች።

ባለፈዉ ዓመት የተደረገዉ የኑክሌር ጉዳይ ስምምነት ስር የሰደደዉን የኢራንና የዩናዩናይትድ ስቴትስን ጠብ፤ ግጭት፤ ተዘዋዋሪ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ያስወግደዋል ማለት በርግጥ የዋሕነት ነዉ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ እንዳሉት ግን የሠላሳ ስድት ዓመቱን ፍጥጫ ያረገበ፤ የጦርነት ሥጋትን የቀነሰ ነዉ።

«ብዙ ጊዜ እንዳልኩት የኑክሌር ስምምነቱ ከኢራን ጋር ያለንን ልዩነት በሙሉ አይፈታዉም።ይሁንና ከብዙ አስረታት በኋላ ከኢራን መንግሥት ጋር በቀጥታ መደራደራችን የጎሎ ችግሮችን ለማስወገድ ልዩ እድልና መስኮት ከፍቶልናል።»

ከፕሬዝደንት ጂሚ ካርተን እስከ ሮናልድ ሬጋን፤ ከጆርጅ ሐዋርድ ቡሽ እስከ ጆርጅ ደባሊዉ ቡሽ የተፈራረቁት የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎችና ተከታዮቻቸዉ አያቶላሕ ሩሕላሕ ኾሚኒ የመሠረቱትን የእስላማዊ አብዮተኞች መንግሥት ለማስወገድ ያላደረጉት ሙከራ የለም።መፈንቅለ መንግሥት፤ የሽምቅ ዉጊያ፤የግድያ ሙከራ ወዘተ ተደርጓል።

ከሁሉም የከፋዉ «የኢራንና የኢራቅ» የተባለዉ ጦርነት ነበር።ከ1980 እስከ እስከ 1988 የዘለቀዉ ጦርነት የኢራንና የኢራቅ ይባል እንጂ ከሶሪያ እና ከከፊል ሊባኖስ በስተቀር የመላዉ አረብ እና የኢራን፤ የአሜሪካኖችና የኢራን፤ የኢራንና የመላዉ ምዕራባዉያን ጦርነት ነበር።ጦርነቱ እስከ 700 ሺሕ የሚገመት ኢራናዊ አልቋል።በኢራቅ በኩልም እንዲሁ።

የሚሊዮኖችን እልቂት ያስከተለዉ ጦርነት እንደታሰበዉ የቴሕራን እስላማዊ አብዮተኞችን ከሥልጣን አላስወገደም።እንዲያዉም በተገላቢጦሹ ሳዳም ሁሴይንን «አሳብጦ» ከዋሽግተን-ቴልአቪቮች ጋር በማላተሙ የመንግሥታቸዉን ዉድቀት፤የሐገራቸዉን ዉድመት፤ የሕዝባቸዉን እልቂት ነዉ ያስከተለዉ።

ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ ትናንት እንዳሉት ሐገራቸዉ ኢራንን ለበርካታ ዓመታት ማግለል፤ማዉገዝ፤ ለጥፋትዋ መዶልትዋ ኢራን የኑኬሌር ቦምብ ለመስራት እንድታደባ ከመግፋት ባለፍ ለአሜሪካ የጠቀመዉ ነገር።

ሩዘቬልት ከስታሊን፤ኬኔዲ ከክሪስቾቭ፤ ሬጋን ከጎርቫቾቭ ጋር ተነጋግረዋልእኔስ ለምን ዓይነት አከሉ ዘንድሮ ከሥልጣን የሚሰናበቱት ኦቦማ።

«ከኢራን ጋር ያለን ልዩነት መንግስቶቻችን ለብዙ አስርታት መኳረፋቸዉ ነዉ።ይሕ የአሜሪካንን ጥቅም አላራመደም።እንዲያዉም፤ በተቃራኒዉ ዓመታት ባለፉ ቁጥር ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመሥራት ይበልጥ እየተቃረበች ነበር።ፕሬዝደንቶቻችን ፍራንክሊን ሩዘቬልት እስከ ጆን ኤፍ ኬኔዲ እስከ ሮናልድ ሬገን፤ (በነበሩበት ዘመን) ዩናይትድ ስቴትስ ከጠላቶችዋ ጋር ዲፕሎማሲ መፍትሔ ለመፈለግ ፈርታ አታዉቅም።ሥለዚሕ እኔም እንደ ፕሬዝደንት ከኢራን መንግሥት ጋር መደራደር ብሔራዊ ደሕንነታችንን ያጠናክራል ብዬ ድርድሩ እንዲቀጥል ወሰንኩ።ዉጤቱን አየነዉ።»

ዉጤቱ፤ ዩንይትድ ስቴትስ፤ብሪታንያ፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመን እና የአዉሮጳ ሕብረት ባንድ ወገን፤ ሩሲያና ቻይና በሌላ ወገን ሆነዉ ከኢራን ጋር ለተከታታይ ዓመታት ከተደራደሩ በሕዋላ የደረሱበት ሥምምነት ነዉ።በሥምምነቱ መሠረት ኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብሯን ማቋረጥዋን ዓለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ድርጅት (IAEA) አረጋግጧል።የድርጅቱ ሐላፊ አኩዮ አማኖ እንዳስታወቁት ከ2003 ጀምሮ ዓለም አቀፉን ድርጅት ሲያባትል የቆየዉ የኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር አሁን ከፍፃሜዉ ደርሷል።

«IAEA የኢራንን የኑኬሌር መርሐ-ግብር መከታተል ከጀመረ ከ2003 ወዲሕ ብዙ ዉጣ ዉረዶችን አይቷል።እዚሕ ለመድረስ ብዙ ሥራዎች መከናወን ነበረባቸዉ።ይሕን ሥምምነት ገቢር ማድረግም ተመሳሳይ ጥረት ይጠይቃል።በኛ በኩል ዝግጁ ነን።»

ኢራን የኑክሌር ቦምብ ትሠራበታለች ተብሎ የተጠረጠረዉን ዩራኒየም ወደ ሩሲያ ልካለች።አደገኛዉን ቦምብ ለማምረት ይረዳል የተባሉ መሳሪያዎችን ነቅላለች።ከኢራን ጋር የተደረገዉን ድርድር የመሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ፤ኢራን በገባችዉ ቃል መሠረት የኑኬሌር መርሐ ግብሯን ማቋረጥዋን «አንፀባራቂ የማዕዘን ድንጋይ» አሉት።

«ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት የሚረዷት ሁሉም ሒደቶች በግልፅ ማረጋገጥ በሚቻልበት ደረጃ ተዘግተዋል።ይሕ ከዩራኒየም ይጀምራል።ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ኢራን የተብላላ የዩራኒየም ክምችቷን ዕለት በዕለት ያለምንም እንቅፋት እየጨመረች ነበር።ባለፈዉ ሐምሌ ባደረገችዉ ስምምነት መሠረት ግን ኢራን ክምችትዋን ወደ 300 ኪሎ ግራም ቀንሳለች።ቀሪዉ ሩሲያ ዉስጥ እንዲብላላ ወደዚያ ልካለች።»

ሥምምነቱ ገቢር መሆኑ ለኢራንም ሲበዛ ጠቃሚ ነዉ።ኢራን በሻሑ የአገዛዝ ዘመን ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ተቀምጦ የነበረ ገንዘቧ ይመለሥልታል።የኑክሌር መርሐ ግብሩ ዉዝግብ በተጀመረ ሰሞን የታገደባት ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብም ይሰጣታል።ከሁሉም በላይ የሐገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነዉ ነዳጅ ዘይት ሰፊ ገበያ ያገኛል።

የኢራን መንግሥት ዛሬ ባዘዘዉ መሠረት ሐገሪቱ እስካሁን ከምታምርተዉ ነዳጅ ዘይት በተጨማሪ በቀን አምስት መቶ ሺሕ በርሚል ነዳጅ ዘይት ለዓለም ገበያ ታቀርባለች።በዓመት ወደ ሐያ ሚሊዮን የሚጠጉ ሐገር ጎብኚዎች ታሪካዊቱን ሐገር ይጎበኛሉ።ከደለበዉ የኢራን ሐብት ለመቆነጣጠር የሚቋምጡት አዉሮጳና የሰሜን አሜሪካ ኩባንያ ባለቤቶች የቴሕራን ሆቴሎችን ማጨናነቅ የጀመሩት ገና ድርድሩ ሳይጋመስ ሐቻምና ነበር።

ሥምምነቱ ከምጣኔ ሐብታዊዉ ጥቅም ባለፍ ኢራን በዓለም የፖለቲካ መድረክ ያላትን ተቀባይነት የሚያጎላ፤ጦርነትና ግጭት ሞልቶ በተረፈዉ ምድር ተጨማሪ ጦርነትን የሚያሰወግድ ነዉ።የኢራኑ ፕሬዝደንት ሐሰን ሩሐኒ በኢራን ታሪክ «ወርቃማ ገፅ » ያሉት ያለ ምክንያት አይደለም።

«በከፍተኛዉ መሪያችን መመሪያ እና በሕዝባችን ትብብር የተደረገዉ የኑክሌር መርሐ-ግብር ድርድር የተሳካ ነዉ።ድርድሩ የመሳካት በእርግጥም በኢራን ታሪክ ወርቃማዉ ገፅ ነዉ።»

ስምምነቱ ገቢራዊነት ቅዳሜ ሲረጋገጥ ኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ የእስረኞች ልዉዉጥ አድርገዋልም። ከኦቦማ እስከ ኬሪ፤ ከሩሐኒ እስከ ዛሪፍ፤ ያሉ መሪ እና ዲፕሎማቶች እንደመሠከሩት ጠመንጃ ያማዘዘዉ ጠብ በዲፕሎማሲ መርገቡ ሠላም ለማያዉቀዉ የዓለም መሪ፤የጦር አዛዥ ዓለምን በሠላማዊ መንገድ ከሠላም ማስተዋወቅ እንደሚቻል ጥሩ አብነት ነዉ።ወይዘሮ ሞግሔሪኒ እንደሚሉት ደግሞ ለተራዉ የዓለም ሕዝብ በሚሰማት ትንሽ ጥሩ ዜና ላይ የሚደበል ጥሩ ዜና ነዉ።

«ይሕ ብዙም ጥሩ ዜና ለማይሰማዉ ዓለም ጥሩ ዜና ነዉ።ዛሬ እንደተከታተልነዉ ጉዳዮችን የሚቀይሩ ወገኖች አሉ።አስቸጋሪ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማሻሻል እንዲሚቻል አመልካች ነዉ።ዲፕሎማሲ እና በጋራ መሥራት ዉጤት ሲያመጡ ማየት አስደሳች ነዉ።አሁን የሆነዉ አዉዳሚ ጦር መሳሪያን የሚቀንስ መሆኑ በራሱ አስደሳች ነዉ። በሌላዉ መስክም ቢሆን የጋራነት እና ዲፕሎማሲ መዳበሩ ሲበዛ ጠቃሚ ነዉ።»

እስራኤል ግን ሥምምነቱንም፤ የስምምነቱን ጥቅምም አልተቀበለችዉም።ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ እስካሁን የነበረችበትን የአሜሪካኖችን ጉያ ቴሕራኖች ሊሻሙኝ ነዉ በሚል የሩቅ ሥጋት ከቴሕራን ጋር እሰጥ አገባ ገጥማለች።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሠ

 

 

Audios and videos on the topic