የዲያስፖራዉ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ተቃውሞ | አፍሪቃ | DW | 08.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የዲያስፖራዉ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ተቃውሞ

የአስቸኳይ ጊዜ ከታወጀ ወዲህ መንግስት የሞባይል ኢንተርኔትና በርካታ የማህበራዊ ድረ-ገጾችን ዘግቷል፡፡ በርካቶች እርምጃውን ከጊዜው ጋር የማይሄድ ጨቋኝ መንግስት የሚከተለው የኃይል አካሄድ ነው ሲሉ ይተቹታል፡፡ መንግስት በበኩሉ እርምጃዎቹ ሀገሪቱን ለተጨማሪ አለመረጋጋቶች የሚዳርጉ አደገኛ አስተያየቶችን ለማስቆም አስፈላጊ እንደነበር ይሟገታል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:05
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:05 ደቂቃ

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ማኅበራዊ ድረ-ገጽና ዲያስፖራዉ

በሳምንቱ መጨረሻ ፒያሳ ትደምቃለች፡፡ ሱቆች እና መዝናኛዎችን በያዘው የአራዳ ገበያ ላይ ወጣቶች ተሰብስበው እየተዝናኑ ነው፡፡ ፊታቸው በፈገግታ ፈክቶ እስክስታ ይወርዳሉ፡፡ ምሽቱን በውዝዋዜ ያሳልፋሉ፡፡ የአዲስ አበባ እንዲህ አይነቱ ህይወት ሀገሪቱ ያለችበትን እውነት በቀላሉ የሚያስረሳ ነው፡፡ 

ስርዓትን ለማስከበር በሚል መንግስት ያወጀው እና ለስድስት ወር የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ሳምንታት ቢያልፉም መዲናይቱ አይሞቃት አይበርዳት ሆናለች፡፡ አዲስ አበባ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው እና በኋላ ላይም ወደ አማራ ክልል ከተዛመተው ተቃውሞ በአንጻራዊነት ራሷን ከልላ ቆይታለች፡፡

ከመስከረም ሃያ ዘጠኙ አዋጅ በኋላ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁንጥጫው የተሰማቸው ይመስላል፡፡ የኢንተርኔት እና የማህበራዊ ድረ-ገጾች መዘጋታቸው የቀን ተቀን እና የስራ ህይወታቸው ላይ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ማህበራዊ ድረ ገጾች ያላቸውን አመለካከት በይፋ ያወጡት አዋጁ ከመታወጁ አስቀድሞ ነው፡፡ 

በመስከረም በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዴት ተቃውሞዎችን እያቀጣጠሉ እንደሚገኙ ገልጸው ነበር፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል የተዛቡ መረጃዎች በማህበራዊ ድረ-ገጾች እየተዛመቱ በተለይ ወጣቶችን እያሳሳቱ ነው፡፡ “ማህበራዊ ድረ-ገጾች የህዝብን ጥያቄ ለራሳቸው መጠቀሚያ ማድረግ የሚፈልጉ ጽንፈኞችን እና ዝና ወዳዶችን የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል” ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ ተቃውሞዎችን አስመልክቶ  በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ አብዛኞቹ አስተያየቶች የሚጻፉት ከኢትዮ-አሜሪካ ዳያስፖራዎች ነው፡፡ እነዚህ ዳያስፖራዎች በኢንተርኔቱ ዓለም ከፍተኛ ተደማጭነት ያካበቱ እና በሀገር ቤት ባለው የፖለቲካ ሂደት ላይም ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ልደቱ አያሌው ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት የዳያስፖራው ተጽእኖ ያሳስባቸዋል፡፡ 

“በጣም አዋኪዎች ናቸው፡፡ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ አይደለም፡፡ ችግሩ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይጨቁናል፡፡ ህዝቡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ በጣም ተስፋ በመቆረጡ ከአትላንቲክ ባሻገር ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መስማት ጀምሯል፡፡ እነሱ የራሳቸው የሬድዮ፣ ቴሌቪዥን እና መገናኛ ብዙሃን ስላላቸው ህዝቡ ጋር በቀላሉ ይደርሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ይህ አይነት የመገናኛ ዘዴ የላቸውም፡፡ መንግስት እዚህ ያሉትን ህጋዊ እና ሰላማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ባዳከመ ቁጥር በውጭ ያሉ ጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ይበልጥ ያጠናክራል” ይላሉ አቶ ልደቱ፡፡ 

የማህበራዊ ድረ-ገጾች ተፅእኖ እንዲህ ሊጎላ የቻለው መንግስት ነጻ የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን እንዲያድጉ ባለመፍቀዱ እንደሆነ የሚጠቁሙ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ቢያደርግ ኖሮ ለዳያስፖራ አቀንቃኞች የተጋነኑ ትርክቶች አጸፋዊ ምላሽ ይኖር ነበር ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነታ እንደሚያመለክተው ግን የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ለማገናዘብ አልቻለም፡፡ ይልቁኑ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑን ወይ ብቻቸውን መተው አሊያም ሙሉ ለሙሉ መጠርቀም መርጧል፡፡ 

ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በሰፈነው ውጥረት መሀል ቁጣ፣ መራር ትችት፣ ስሞታ እና አሳዛኝ ሁነት ኢትዮጵያውያን ዘላቂ መፍትሄ እንዳይፈልጉ ምክንያቶች ሆነዋል፡፡ አቶ አበበ ኃይሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ጠበቃ ናቸው፡፡ የኃይለስላሴ መንግስትን የገረሰሰው የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበሩ፡፡ የመፍትሄ ፍለጋውን ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ እና ይትባህል ጋር ያዛምዱታል፡፡  

“አብሮ መብላቱን እንጂ አብሮ መስራቱን እናውቅበትም፡፡ ስለ ኢትጵያውያን አስተሳሰብ አንድ ነገር መገነዘብ አለብህ፡፡ ከ16ኛው ከፍለዘመን እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ  በመገለል ነው የኖርነው፡፡ ስለዚህ የራሳችንን ስነ ልቦና እና አስተሳሰብ አዳብረናል፡፡ የኢትዮጵያ አስተሳሰብ ክብ ነው፡፡ አብያተ ክርሰቲያናቱ ከብ ናቸው፣ መስጊዶቹ ክብ ናቸው፣ የምንበላው እንጀራም ክብ ነው፡፡ ሁሉ ነገር ክብ ነው፡፡ በክብ አስተሳሰብ በተመሳሳይ ነገር ላይ ዝም ብለህ ትከራከራለህ እንጂ ውሳኔ ላይ አትደርስም” ሲሉ አቶ አበበ፡፡

 ጄምስ ጄፍሪ/ተስፋለም ወልደየስ

ሒሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች