የዱልሚ ዲድ ንቅናቄ መሥራቾች በጅግጅጋ ታሰሩ | ኢትዮጵያ | DW | 25.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የዱልሚ ዲድ ንቅናቄ መሥራቾች በጅግጅጋ ታሰሩ

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድር ሙስጠፋ ዑመር ከሥልጣናቸው ሊለቁ ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል የተባሉ የዱልሚ ዲድ ንቅናቄ መሥራቾች በጅግጅጋ ታሰሩ። በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ኸድር ጅግሬና አቶ አብዲ ኑር ናቸው። የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አማካሪ ሁለቱ ግለሰቦች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድር አቶ ሙስጠፋ ዑመር ከሥልጣናቸው ሊለቁ ይገባል የሚል ጥያቄ አቅርበዋል የተባሉ ሁለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በትናንትናው ዕለት በጅጅጋ ከተማ ታሰሩ። ከአዲስ አበባ ተጉዘው ጅግጅጋ ሲደርሱ በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ኸድር ጅግሬ እና አቶ አብዲ ኑር ናቸው። ሁለቱ ግለሰቦች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚወተውተው ዱልሚ ዲድ የተሰኘ ንቅናቄ መሥራቾች ናቸው። የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ዑመር የሚዲያ አማካሪ ሰዎቹ መታሰራቸውን ለDW አረጋግጠዋል።

ከዱልሚ ዲድ ንቅናቄ ጋር በቅርበት ይሰራ የነበረው ወጣት ሑሴን አብዲ እንደሚለው በፌስቡክ ገፃቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት "የክልሉ ፕሬዝዳንት ለውጡን በተገቢው እና በተፈለገው እየመሩት አይደለም። ስለዚህ ስልጣኑን መልቀቅ አለበት" የሚል ጥሪ ያቀረቡት አቶ ኸድር ጅግሬ ጅግጅጋ ከተማ ሲደርሱ በክልሉ ልዩ ኃይል በቁጥጥር ሥር ውለዋል። 

አቶ ኸድር ጅግሬ እና አቶ አብዲ ኑር "አድማ ሊያደርጉ ነው፤ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርጉ ነው" በሚል መታሰራቸውን ሑሴን አብዲ ተናግሯል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር የሚዲያ አማካሪ አቶ መሐመድ ኦላድ ሁለቱ የዱልሚ ዲድ መስራቾች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አረጋግጠዋል። አቶ መሐመድ "ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር። [በቁጥጥር ሥር የዋሉት] የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ነው። ጉዳያቸው ገና እየተጣራ ነው" ሲሉ ለDW ተናግረዋል።

አቶ ኸድር ጅግሬ እና አቶ አብዲ ኑር ፍርድ ቤት አልቀረቡም። አቶ መሐመድ ኦላድ "በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሳምንቱ መጨረሻ ነው። ዛሬውኑ ወይም ነገውኑ ጉዳያቸው እንደተጣራ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ" ብለዋል። አቶ ከድር ጅግሬ አደም ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ሀገር ሲሆን በሚኒሶታ ግዛት በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩ። አብረዋቸው የታሰሩት አቶ አቶ አብዲ ኑር የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ

Audios and videos on the topic