የደ. አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት በሙስና ከስልጣን መሰናበት | የጋዜጦች አምድ | DW | 15.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የደ. አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት በሙስና ከስልጣን መሰናበት

የደቡብ አፍሪካዉ ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ ምክትል ፕሬዝደንታቸዉ የነበሩትን ጃኮብ ዙማን በትላንትናዉ ዕለት በይፋ ከስልጣንና ከምክርቤት ስራቸዉ አሰናበቱ። ምቤኪ በምክትላቸዉ በዙማ ላይ ይህን ያደረጉት አፍሪካን ከሙስና ለማፅዳት ለሚደረገዉ ጥረት ደቡብ አፍሪካ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመዷን ለማሳየት ነዉ የሚሉ ብዙዎች ናቸዉ።

እርምጃዉ መደረግ ነበረበት የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም ዙማ በአገሪቱ ታሪክ ካበረከቱት ቀና አስተዋፅዖ በመነሳት በደቡብ አፍሪካ ብዙ ታሪክ ያስመዘገበዉ የኤኤንሲን ፓርቲ ለፈተና ዳርጎታል የሚሉም በርካታ ናቸዉ።
የፕሬዝደንቱ የቅርብ ወዳጅ በመባል ይጠሩ ለነበሩት ለጃኮብ ዙማ ከስልጣን የመናበታቸዉ ዜና አስደንጋጭም አስገራሚም ነበር የሆነባቸዉ።
በእርጋታቸዉና በብልህ አመራራቸዉ እንዲሁም በአፍሪካ ዉስጥ ለሚነሳ ግጭት ሁሉ ለመሸምገል በግንባር ቀደምትነት ለሚገኙት ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪ ቀኝ እጃቸዉ መሆናቸዉ የሚነገርላቸዉን ምክትላቸዉን ከስልጣን ለማሰናበት መወሰናቸዉን ለምክር ቤታቸዉ ማሳወቅም ቀላል አልነበረም።
በአጭሩ በሙስና ስለጠረጠርናቸዉ ከስልጣናቸዉ ተወግደዋል ከማለት ይልቅ ሁኔታዉን ለመግለፅ ያደረጉት የቃላት ምርጫም በእርግጥም ብስለታቸዉን ያሳየ መልካም አጋጣሚ ነበር።
በአገራችን በማበብ ላይ የሚገኘዉ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዳይጨናገፍ አሉ ምቤኪ ሙስናን ከራሳችን ጀምረን ለመታገል ቁርጠኛነታችንን ለማሳየት ባለኝ የፕሬዝደንትነት ስልጣንና ባለኝ የአገር ሃላፊነት የተከበሩ ምክትል ፕሬዝደንቱ ከሃላፊነታቸዉ እንዲነሱ ዉሳኔ ላይ ደርሻለሁ።
ምቤኪ እዚህ ዉሳኔ ላይ ለመድረስ ያስገደዳቸዉ አጋጣሚ በዚሁ ወር የዙማ የቀድሞ የገንዘብ ጉዳይ አማካሪ ሻቢር ሳይክ በሙስናና በማጭበርር ወንጀል መከሰስ እንደሆነ ይነገራል።
የዳኛዉ ዉሳኔም ዙማና የቀድሞ አማካሪያቸዉ ከነበራቸዉ ግንኙነት በመነሳት ጥንድ ሙሰኞች የሚል ትርጓሜ በመያዙ ይህን ጉዳይ የሰሙት ምቤኪ ለዙማ እንደድሮዉ ሊሆኑላቸዉ አልቻሉም።
በአንፃሩ በመጪዉ የፈረንጆቹ 2009 ላይ ምቤኪን ይተካሉ ተብለዉ የሚጠበቁት የታወቁት ፓለቲከኛ የጃኮብ ዙማ ከስልጣን መሰናበት በአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ማለትም ANC ዉስጥ ዉጥረት አንግሷል።
በANC ዉስጥ ዝናን ባላቸዉ ከፍተኛ ስልጣን ከፓርቲዉ ልዩ ልዩ አጋሮች ተቀባይነት ያተረፉት ዙማም ከስልጣን መወገዳቸዉን በቀላሉ አልተቀበሉትም።
ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግርም ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙና በህጋቸዉ መሰረት በፍርድ ቤት እንዳልተዳኙም ነዉ አበክረዉ ለመግለፅ የሞከሩት።
በአህጉሪቱ የሚገኙ ተንታኞች እንደሚሉት ግን እርምጃዉ ዓለም ዓቀፍ ለጋሾችና በአፍሪካ ምዋዕለ ንዋያቸዉን ለልማት ለማዋል የፈለጉ ኩባንያዎች እንደእንቅፋት የሚያዩት ሙስናን ለመዋጋት ምቤኪ ያሳዩት ቁርጠኝነት ዉጤት ነዉ።
በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ እንደሚሉት ጊዜዉ የደቡብ አፍሪካን ዲሞክራሲ የመከላከያዉና አገሪቱ የአፍሪካ ተስፋ መሆኗን የማረጋገጫዉ ወሳኝ ወቅት ነዉ።
በዚህም ይላሉ ምሁሩ ምቤኪ በእርምጃቸዉ ያላቸዉን የመሪነት ብቃት አሳይተዋል። በመጪዉ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት ስብሰባ ላይም ምቤኪ ያለምንም መሸማቀቅ መሪዎቹን ስኮትላንድ ላይ ለጉባኤ ሊያገኟቸዉ ይችላሉ።
ሌሎች የፓለቲካ ተንታኞችም በበኩላቸዉ ምቤኪ ለዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ የሚናገሩትን ማድረግ የማይሳናቸዉ መሪ መሆናቸዉን አሳይተዋል ይላሉ።
የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላም ለዙማ ከልብ ማዘናቸዉን ቢገልፁም በምቤኪ ዉሳኔ እንደሚስማሙ ነዉ በይፋ የተናገሩት።
ድርጅታችን፤ ህዝባችንና መንግስታችን አስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዝደንቱን ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን ሲሉም አቋማቸዉን ግልፅ አድርገዋል።
ተንታኞችም እንዲሁ የምቤኪ ወሳኝ እርምጃ ደቡብ አፍሪካ ያላትን ገፅታ ከማስጠበቁም በላይ ለአገራቸዉ የመገበያያ ገንዘብ ራንድም የሚያድገዉ አስተዋፅዖ ይኖራል ባይ ናቸዉ።
ለማንኛዉም ምቤኪ የዛሬ 6 ዓመት በዙሉ ኢንካታ የነፃነት ፓርቲና በANC መካከል የከረመዉን ደም መቃባት ማብረድ የቻሉትን ዙማን የሚተካዉን ግለሰብ ስም ይጠቁማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከሁለት አመት በኋላ ኤኤንሲ አዲስ የፓርቲ ፕሬዝደንት እስኪመርጥ ድረስም ምቤኪ የሚሾሙት ጊዜያዊ ምክትላቸዉን ይሆናል። ለጊዜዉ ግን ዙማ የኤኤንሲ ምክትል ፕሬዝደንት እንደሆኑ ይቆያሉ።
ዙማን ሊተኩ ይችላሉ ከተባሉት መካከልም የመከላከያ ሚኒስትር፤ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የኤኤንሲ ዋና ፀሃፊና የማዕድንና የሃይል ሚኒስትሩ እንዲሁም የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት የደቡብ አፍሪካ መንግስት ባለስልጣናት መካከል አንዱ ሳይሆኑ አይቀሩም የሚል ግምት አለ።