የደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ ዉዝግብ | አፍሪቃ | DW | 30.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ ዉዝግብ

ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የፖለቲካ ዉዝግቡ ንሯል። ገዢዉ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በፕሬዝደንቱ ጄኮብ ዙማ የሙስና ቅሌት ምክንያት እየተተቸ ነዉ። በየቀኑ የተቃዉሞ ሰልፎች ይካሄዳሉ። ዜጎች ተቀባይነት ያጡት የሀገሪቱ መሪ ስልጣን እንዲለቁ ይጠይቃሉ። አጋጣሚዉን ተቃዋሚዎች ተጠቅመዉ በዙማ ላይ የመተማመኛ ድምጽ ምክር ቤቱ እንዲሰጥ ገፍተዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:02

በስድስት ቀኑ ጉባኤ ፓርቲዉ የሕዝቡን ቀልብ ለመሳብ አልሟል፤

በደቡብ አፍሪቃዉ ገዢ ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (ኤ ኤን ሲ)  ዉስጥ የተፈጠረዉ ዉዝግብ ፓርቲዉ የነበረዉን ዝና እያሳጣዉ ይሄዳል የሚል ስጋት አለ። ዛሬ የሚካሄደዉ የፓርቲዉ ጉባኤም ሊፈነዳ በተቃረበ የፖለቲካ አዉድ የታጀበ ነዉ። 3 ሺህ የሚሆኑት የኤ ኤን ሲ አባላት ከዛሬ ጀምረዉ እስከ ፊታችን ረቡዕ ድረስ ስለፓርቲዉ የፖለቲካ ሂደር ይወያያሉ። ይህም የሀገሪቱን ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዉ ሽግግር ይመለከታል። የሥራ አጡ ቁጥር 27,7 በመቶ ከፍ ብሏል፤ የሀገሪቱ ኤኮኖሚም በመጀመሪያዉ ሩብ ዓመት በ0,7 በመቶ ቀንሷል። 

ኤ ኤን ሲ ከዝቅተኛዉ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር የነበረዉ ግንኙነት ቀንሷል፤ «ሕዝቡ በፓርቲዉ ላይ ያለዉ እምነት በጣም ወርዷል፤ ይህም በምርጫዉ ዉጤት እና በይፋ በሚሰነዘሩት ትችቶች ይገለጻል።» ይላሉ በፕሬዝደንቱ ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ጄፍ ራደቤ ለጉባኤዉ በተዘጋጀዉ መወያያ ሰነድ ላይ። ኤ ኤን ሲም ልክ ራደቤ እንደሰጉት፤ ፕሬዝደንት ዙማን በተመለከተ ክርክሩ ቀጥሎ የተለያዩትን አንጃዎች ይበልጥ ይከፋፍላል  በሚል ሰግቷል። እናም በዚህ ጉባኤ ፓርቲዉ  አንድነቱን  ለማጠናከር አልሟል። የቀድሞዉ የነፃአዉጪ ንቅናቄ ሥርነቀል ኤኮኖሚያዊ ለዉጦችን በማድረግ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2019ዓ,ም በሚካሄደዉ ምርጫ  የሕዝቡን ድምጽ መልሶ ለማግኘት ይፈልጋል። የዙማም ሁለተኛ የስልጣን ዘመን ያከትማል።  የፖለቲካ ተንታኙ ዳንኤል ሲልኬ የስድስት ቀኑ የ ኤ ኤን ሲ ጉባኤ ወሳኝ የፖሊሲ ጉዳዮች የሚታዩበት ነዉ ይላሉ፤

«በጣም ወሳኝ የፖሊሲ ስብሰባ ነዉ ምክንያቱም የትኛዉ የፖለቲካ አንጃ በኤ ኤንሲ ዉስጥ ወደ ላይ እንደሚወጣ፤ የየትኛዉ ፖሊሲስ የበለጠ ተቀባይነት እንደሚኖረዉ፤ የትኛዉስ ድምጹ ላይሰማ እንደሚችል፤ ወይም በጣም ግልፅ ሆኖ ለሰፋ ትርጓሜ ሊጋለጥ እንደሚችል ምልክት ይሰጠናል። እናም እኔ እንደማስበዉ ከዚህ ከፖሊሲ ጉባኤ የሚወጣዉን መተንተን ከቻልን የትኞቹ አንጃዎች በበላይነት በዓመቱ ማለቂያ ማን የኤ ኤን ሲ ፕሬዝደንት ሊሆን እንደሚችል ጫና ያደርጋሉ የሚለዉን ፍንጭ ይሰጠናል።»

በቀጣይ ለፓርቲዉ ፕሬዝደንት ምክትል ፕሬዝደንቱ ሲሪል ራምፎሳ እና የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ዶክተር ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ ግንባር ቀደም ተፎካካሪዎች ናቸዉ። የቀድሞዉ የየሠራተኞች ማኅበር መሪ ራምፎሳ አሁን የሀገሪቱ የናጠጡ ነጋዴ ወጥቷቸዋል። ተቀናቃኛቸዉ የቀድሞዋ የፕሬዝደንቱ ባለቤት ዙማም ሆኑ ራምፎሳ ባላቸዉ ተቀባይነት ባይበላለጡም፤ ራምፎሳ ፓርዉን አድሳለሁ በሚለዉ ንግግራቸዉ ሚዛን የደፉ መስለዋል።

ከደቡብ አፍሪቃ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በዛሬዉ ዕለት የኤ ኤን ሲ ግዙፍ የፖሊሲ ጉባኤ  ጆሃንስበርግ ላይ ሲጀመር በፕሬዝደንት ዙማ ላይ በቀረቡት የሙስና እና የአስተዳደር ብልሽት ስጋቶች ምክንያት አንዳንድ አንጋፋ የፓርቲዉ አባላት አልተገኙም። ሌላኛዉ የፖለቲካ ተንታኝ ቲዮ ቬንተር እንደሚሉት ፓርቲዉ የአባላቱን ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም ያጣዉን ተዓማኒነት ለማግኘት ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል።

«ባጠቃላይ ብዙ ማለት የሚቻላል ይመስለኛል፤ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ከፕሬዝደንቱ ጋር በተገናኘ በርካታ ነገሮች ተከናዉነዋል። ያ ደግሞ ባለፈዉ ዓመት ነሐሴ ከተካሄደዉ ምርጫ ዉጤት ጋር ይያያዛል። ይህ ሁለት አካሄዶችን በግልፅ ያመለክታል፤ አንደኛዉ ሰዎች ከኤ ኤን ሲ ወደ ሌሎች ፓርቲዎች እየሄዱ ነዉ፤ ሁለተኛዉ ደግሞ ሰዎች የተቃዉሞ ድምጽ በሚመስል መልኩ በምርጫ ከመሳተፍ እየራቁ ነዉ። ይህ ደግሞ  የለዉጥ ርምጃ ሂደት እንዳለ በግልፅ ያሳያል። ያ ነዉ ይህ የፖሊሲ ጉባኤ አዉድ እንዴት መሆን እንዳለበት ያመላከተዉ፤ ኤ ኤንሲ የነበረዉን ተቀባይነት ለማግኘት እየጣረ ነዉ።»

እንዲያም ሆኖ የፕሬዝደንት ዙማ አስተዳደር አመጣለዉ ያለዉን መሠረታዊ የኤኮኖሚ ለዉጥ ማምጣት መቻሉን የሚያረጋግጥለት ተቸባች ማስረጃ ለህዝቡ ማቅረብ ይኖርበታል። ምንም እንኳን ከድኽረ አፓርታይድ ዘመን አንስቶ የደቡብ አፍሪቃ ገዢ የሆነዉ ፓርቲ ኤ ኤን ሲ የሚቀርቡበት ትችቶች እና የዉስጥ ዉዝግቡ ጎልቶ ቢታይይም የፓርቲዉ ዋና ፀሐፊ ጌዉድ ማንታሼ ለስድስት ቀናት የሚካሄደዉ ጉባኤ ይደናቀፋል ብለዉ እንደማይጠብቁ ተናግረዋል።

ሸዋዬ ለገሠ/  ማርቲና ሽቭኮቭስኪ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች