የደቡብ አፍሪቃ ማዕድን ሠራተኞች | አፍሪቃ | DW | 17.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደቡብ አፍሪቃ ማዕድን ሠራተኞች

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ፣ ፕላቲነም ማዕድን በሚወጣበት ሥፍራ ፤ የደመወዝ ጭማሪ በጠየቁ ሠራተኞች ላይ ፖሊስ ትናንት ከቀትር በኋላ፣ በከፈተው ሩምታ ተኩስ 18 ያህል ሠራተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል። ድርጊቱ፣ በሰፊው እያነጋገረ ነው ፣ በሥራው

መታጎል ሳቢያ ፤ የፕላቲነም ማዕድን ዋጋም አለቅጥ መናሩ እየተነገረ ነው። በዓለም ውስጥ ከሚገኘው የፕላቲነም ክምችት ¾ኛው የሚገኘው በደቡብ አፍሪቃ ነው። ፖሊስ የወሰደው እርምጃ ጭካኔ የተመላበት በመሆኑ ፤ በተቃዋሚው የፖለቲካ ድርጅትም ሆነው በገዥው ፓርቲ ድንጋጤን ነው ያስከተለው። ፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ፣ «እጅግ አስደንጋጭና ትርጉም የለሽ የኃይል እርምጃ፣» ተወስዷል ሲሉ «ዴሞክራቲክ አሊያንስ» የተሰኘው የተቃውሞው ፓርቲ፣ የፖሊሶቹን እርምጃ «ጭፍጨፋ » ብሎታል።

የፖሊስ ዋና አዛዥ ምትቴትዋ፣ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ፣ እስከ አፍንጫቸው ጦር መሣሪያ ታጥቀው ነበረና ፤ የተወሰደው እርምጃ ትክክል ነው ባይ ናቸው። ቢያንስ 12 ሰዎች በጥይት ሲገደሉ በአጠቃላይ በ 6 ቀናት ውስጥ ከ 20 በላይ ሠራተኞች ናቸው ህይወታቸውን ያጡት። ሃቻምና የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር፣ ከተካሄደባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው፣ በሩስተንበርግ፣ አንድ ጎጥ ላይ የመሸጉ ፤ 5,000 ያህል የሥራ ማቆም አድማ የመቱ ሠራተኞች በኃይል እርምጃ፤ 3 እጥፍ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ለማስገደድ ተነሳስተው ነበረ ይባላል። የማዕድንና የግንባታ ሠራተኞች ማኅበር (AMCU )እንደገለጠው፣ የሠራተኞቹ አማካይ የወር ደመወዝ 400 ዩውሮ ነው።

የ AMCU ፕሬዚዳንት ማቱንጅዋ--

«አንድ ሠራተኛ፤ ከ 20 ዓመታት ከባድ ሥራ በኋላ፤ አሁንም ደመወዙ 400 ዩውሮ ብቻ ከሆነ ፤ ማኅበራቱ በእርግጥ መነጋገር አለባቸው። ይህ ደግሞ ሃቅ ነው፤ ለፍጥጫው አስተዋጽዖ አድርጓል።»

በዛ ያሉ ሠራተኞች ፤ ለመንግሥት ይበልጥ ቀረቤታ እንዳለው ከሚነገርለት ጠንካራው ብሔራዊ የማዕድን ሠራተኞች ኅብረት(NUM) እየወጡ፤ የማዕድንና የግንባታ ሠራተኞች ማኅበር (AMCU)አባላት በመሆን ላይ ይገኛሉ። ይህ በፊናው በሙያ ማኅበራቱ መካከል የሥልጣን ፉክክር ያስነሳ ሲሆን፤የሚገደሉ ሰዎች በጽሑፍ እየተመዘገብ፤ ፖሊሶችና ዘበኞች በቆንጨራ ሳይቀር የእርምጃው ሰለባዎች ሆነዋል። ፕሬዚዳንት ዙማ ጉዳዩ በውይይት እንዲፈታ ቢያሳስቡም፤ ማኅበሩ NUM«ፍጹም አይሞከርም፤ ከወንጀለኞች ጋር ድርድር አይታሰብም »የሚል ግትር አቋም ሆኗል የመረጠው። የ NUM ቃል አቀባይ፣ ሴሾካ---

«አንድ ሰው፣ ቤተሰብህን ቢተናኮልብህ፣ አንዳች የምትደራደርበት ምክንያት አይኖርህም፣ ርምጃ ከመውሰድ በስተቀር። ምን የሚያደራድር ጉዳይ ይኖራል?የሚበጀው፤ ጠበቅ ያለ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይሆናል። በከርሠ- ምድር ማዕድን የማውጣት ሥራ ሰላም ያሻዋል፤ የሚደራደሩበት ጉዳይ አይደለም።»

«ሎንሚን » የተሰኘው የፕላቲኒየም ማዕድን ኩባንያ ፣ በዓለም ውስጥ ፣ በትልቅነቱ የ 3ኛነት ደረጃ የያዘ ሲሆን፤ ከሠራተኞቹ ጋር እከመጪው 2013 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፀንቶ የሚቆይ የአበል ውል ያለው መሆኑን ገልጾ፣ ህገ-ወጥ የሥራ ማቆም ካደረጉት 1/5ኛው ከሥራ ሊባረሩ ይችላሉ ሲል ማሥፈራራቱም ተጠቅሷል። ባለፉት 6 ቀናት ውስጥ 420,000 ግራም ያህል ፕላቲነም ባለመመረቱ ፤ 21 ሚሊዮን ዶላር ያህል ኪሣራ እንደደረሰበት ሎንሚን አስታውቋል።

ፕላቲነም፤ በጣም ተፈላጊ ማዕድን ሲሆን፤ በተለይ አውቶሞቢል ሠሪዎች፤ ለአደገኛ ጭስ ማጣሪያ ይጠቀሙበታል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 17.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15s8U
 • ቀን 17.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15s8U