የደቡብ አፍሪቃው የስራ ማቆም አድማ አበቃ | አፍሪቃ | DW | 19.09.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደቡብ አፍሪቃው የስራ ማቆም አድማ አበቃ

ትንናት በተደረሰው ስምምነቱ መሰረት ሠራተኞቹ ከ 11 እስከ 22 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ይደረገላቸዋል ። በዚህ ሳምንት ሥራ የሚጀምሩ ደግሞ 2 ሺህ ራንድ ተጨማሪ ጉርሻ ያገኛሉ ።

የደብቡ አፍሪቃው የሎንሚን የፕላቲንየም ማዕድን ማውጫ ሠራተኞች ነገ ወደ ስራ ገበታቸው ለመመለስ ተስማሙ ። ሠራተኞቹ ለሳምንታት የዘለቀውን የሥራ ማቆም አድማ አብቅተው ነገ ወደ ሥራ የሚመለሱት የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄአቸው መልስ በማግኘቱ ነው ። ሰራተኞቹ ፣ የደሞዝ ጭማሪ ስምምነት ላይ በመደረሱ ዛሬ ደሰታቸውን ሲገልጹ ውለዋል ።
6 ሳምንት ያህል የዘለቀው የደቡብ አፍሪቃው የሎንሚን የፕላቲንየም ማዕድን ማውጫ ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ በስምምነት ማብቃቱ ሲነገር ሠራተኞቹ በመዝሙርና በዳንስ ነበር ደስታቸውን በህብረት የገለጹት ። የማዕድን ማውጫው በሚገኝበት በማሪካናው ስታድዮም በሺህዎች የሚቆጠሩ የድርጅቱ ሠራተኞች የደቡብ አፍሪቃን ብሔራዊ መዝሙር ሲዘምሩ ሲስቁና ሲደሰቱ ነው የዋሉት ።
ብዙዎቹ ነገ ሥራ መጀመራቸው አስደስቷቸዋል ። ትንናት በተደረሰው በዚሁ ስምምነቱ መሰረት ሠራተኞቹ ከ 11 እስከ 22 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ይደረገላቸዋል ። በዚህ ሳምንት ሥራ የሚጀምሩ ደግሞ 2 ሺህ ራንድ ተጨማሪ ጉርሻ ያገኛሉ ።


ይህ ጭማሪ ዝቅተኛ ከነበረው ደሞዝ 4500 ራንድ ከፍ ያለ ቢሆንም አስቀድሞ ከጠየቁት 12,500 ራንድ ግን ያንሳል ። የሠራተኖቹ ተወካይ ዞሊሳ ቦድላኒ ምንም እንኳን የተጠየቀውን ያህል የደሞዝ ጭማሪ ባይገኝም ስምምነቱ ተቀብለናል ብለዋል ። ይህን ያደረጉትም የማዕድን አውጭ ሠራተኞች ሥራቸውን እንዳያጡ በሚል ነው ። ሌላው ምክንያት ደግሞ አድማውን ለማስቆም ወታደሮችና ፖሊሶች የሚወስዱትን እርምጃም ለማስቀረት ነው ።
« የመንግሥት እርምጃ አስተዳደሩን የሚያግዝ ነው ። ሊከፋፍሉን ሞክረው ነበር ። ያን ለማስቀረት ወሰን ።ስለዚህ የተሻለው መንገድ የሰጡንን መቀበል ቢያንስ ወደ ሥራ እንመለስ ማንም ከሥራ አይባረርም ማንም ሥራውን አያጣም ። »
የሥራ ማቆም አድማው ሲጀመር በተነሳ ተቃውሞ የ 45 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል ። ከመካከላቸው 34 ቱ በፖሊስ ጥይት ነው ህይወታቸው ያለፈው ። ሌላው የሠራተኞች ተወካይ ጆሴፍ ማቱንጃዋ በሥራ ማቆም አድማው ምክንያት የጠፋውን ህይወት በማስታወስ ስምምነቱ ቀደም ብሎ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ህይወት ባልጠፋም ነበር ብለዋል ።
«ስምምነቱን ስትመለከት አንድም ህይወት ሳይጠፋ ከ 5 ሳምንት በፊት ሊደረግ ይችል ነበር ። ሆኖም የሆነው ና ያየነው ይህን ነው »


ስምምነቱ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ እፎይታን ቢያስገኝም ሌሎች ህገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማዎችን ሊያበረታታ ይችላል የሚል ፍራቻ ማስከተሉ አልቀረም ። ቶን ሃርሊ ከሠራተኞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አማካሪ ናቸው
« እጅግ አስቸጋሪ የነበረ ምዕራፍ መዘጋቱን ሁላችንም እናደንቃለን ። ይህ ምናልባትም ወደፊት አሁን ስምምነት ከተደረሰበትም በላይ ለተጨማሪ የደሞዝ ጥያቄ ህገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማዎችን ለማካሄድ መነሻ ሲሆን ልናይ እንችላለን ። ስለዚህ እኔ ይህ ሁለቱንም ወገን በጥሞና የሚያስማማ ሂደት ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም ። »
የሎንሚን ማዕድን ማውጫ ምክትል ፕሬዝዳንት ግን ስምምነቱን ማህበራዊ ሃላፊነት የተሞላበት መፍትሄ ብለውታል ። እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰውም እንደርሳቸው አባባል ድርጅቱንና 28 ሺህ የሥራ ገበታዎችን ለማዳን በህብረተሰቡ ውስጥ የሰፈነውንም ፍርሃት ለማስወገድ ነው ። ይሁንና አሁንም ቢሆንም አንዳንድ ስጋቶች መኖራቸው አልቀረም ። በተለይ ለደሞዝ ጭማሪው ማካካሻ ሠራተኞች ሊቀነሱ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች ይሰማሉ ። ሆኖም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ይህን መሰል እቅድ የለንም ብለዋል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic