የደቡብ ሱዳን፤  8ተኛ ዓመት የነፃነት ቀን | አፍሪቃ | DW | 13.07.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን፤  8ተኛ ዓመት የነፃነት ቀን

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ደቡብ ሱዳን ስምንተኛ ዓመት የነፃነት ቀንዋን አስባለች።  በጎርጎረሳዊው 2011 ሰኔ ወር ነፃነትዋን የተጎናፀፈችዉ ደቡብ ሱዳን ከነጻነት በኋላ 54 ኛዋ አፍሪቃዊት ሃገርም ናት። ከነጻነት በኋላ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀችዉ ሀገር ደቡብ ሱዳን የፕሬስ ነጻነት አደጋ ላይ ወድቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:43

ጋዜጠኞች ደቡብ ሱዳን ጥለዉ ሲሰደዱ አይተናል

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ደቡብ ሱዳን ስምንተኛ ዓመት የነፃነት ቀንዋን አስባለች።  በጎርጎረሳዊው 2011 ሰኔ ወር ነፃነትዋን የተጎናፀፈችዉ ደቡብ ሱዳን ከነጻነት በኋላ 54 ኛዋ አፍሪቃዊት ሃገርም ሆናለች። ከነጻነት በኋላ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቀችዉ ሀገር ደቡብ ሱዳን የፕሬስ ነጻነትና የመገናኛ ብዙኃን ገለልተኛነትን በተመለከተ በጎርጎረሳዊው 2014 ዓ.ም ሕግ አርቅቃ እና አፅድቃ  የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን ብትመሠርትም፤ ነፃ ፕረስ በግሩ ለመቆም ገና በመውተርተር ላይ ነዉ። ግድያ፣ አፈና እንግልትን የፈሩ አንዳንድ ጋዜጠኞች ሀገሪቱን ጥለዉ መውጣታቸውን ቀጥለዋል፤ መፍትሄ ያጡ ሌሎች ደግሞ ለመንግሥት እንዲመቸዉ አድገዉ ለመጻፍ ተገደዋል። ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ግን ሥራቸዉን እየለቀቁ ነዉ። እንድያም ሆኖ ይላሉ በሀገሪቱ የሚገኙ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንድያም ሆኖ በደቡብ ሱዳን የጋዜጠኞች እስር ቁጥር በመቀነሱ ትንሽ መሻሻል የታየ መስሎአል። ደቡብ ሱዳን የህትመትና ሚዲያን በተመለከተ ጋዜጠኞች ሚዛናዊ ዘገባን እንዲያሰራጩና በገለልተኝነት እንዲተዳደሩ ሕግ አርቅቃ ካፀደቀች አምስት ዓመት ግድም ሆናት። በደቡብ ሱዳን የሚታተመዉ ኧል-ሞዲፍ የተሰኘዉ አርብኛ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ማቲያንግ ኪሪሎ እንደገለፀዉ ከሆነ ላለፉት አራት ዓመታት በሀገሪቱ ጋዜጠኞች በደሕንነት ኃይላት በቀጥታ ለእንግልትና እስር በመዳረጋቸዉ በደቡብ ሱዳን የሚገኘዉ የጋዜጠኛ ቁጥር ቀንሷል። በሕትመት ሚዲያዉ የሚገኙ ጋዜጦች ከደህንነት ኃይላት ጋር በየዕለቱ የሚጋፈጡት ትግል እና ማሳደድ ቀላል እንዳልሆነ ገልፆአል። ካሮ እንደተናገረዉ ጋዜጠኞች በየቀኑ ከደህንነት ኃይላት ከሚደርስባቸዉ እንግልት በተጨማሪ  የማተሚያ ቤት ሠራተኞች፤ ምን ማተም እንዳለባቸዉ የሚደርሳቸዉ ትዕዛዝ ብሎም ዛሬ አታሳትምም የሚል መልስ ሲደርሳቸዉ ያለዉ ችግርን ዘርዝሯል። 

« ብዙ እንዳታዳርጉ፤ እንዳትሰሩ የሚባልበት በግልፅ መነገር የማይፈቀድበት ብዙ ቀይ መስመሮች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ ማካሄድም አይፈቀድልንም። ስለጉዳዩ መረጃ የሚሰጥ በወረቀት ላይ የተጻፈ ነገር ማግኘት እንኳ አንችልም። የሆነ ወረቀት ላይ የተፃፈ መረጃ ብናገኝ እንኳ ሁኔታዎች ጥሩ ስላልሆኑ ጉዳዩን አንስተን ለህትመት ማብቃት እንችልም። »   

ጋዜጠኛ ካሪሎ ፤ የፀጥታ ኃይላትን ባለስልጣናትን መተቸት አልያም ከባለስልጣናት ጋር የተገናኘ ሙስናን የተመለከተ መረጃ፤ እንዲሁም ፕሬዚደንቱን የሚተች ዘገባ እንዳትሠራ በማለት ያግዱኛል ሲል ተናግሮአል። በዚህ ዓመት ብቻ ይላል ካሪሎ፤ የፀጥታ ኃይላት በተለያዩ ጊዜያት ሊታተም የተዘጋጀ አምስት ዘገባዎች ታግደዉብኛል። በሥራችን ውስጥ የፀጥታ ኃይላት እጃቸዉን እንዳያስገቡ ገለልተኛ ተብሎ በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ሕግጋት ቢፀድቅም፤ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ኃይላት ርምጃ ለነፃ ፕረሱ ቀስ በቀስ ማሽቆልቆልና ብሎም ሕልውናውብ የሚፈታተን ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ በሀገሪቱ የዛሬ አምስት ዓመት የጀመረዉ የእርስ በርስ ጦርነት በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገዉን አፈና እና ጭፍለቃ እንዲባባስ አድርጎታል። ኢሪነ አያ በደቡብ ሱዳን የመገናኛ ብዙኃን ማሕበር ፤ የመገናኛ ብዙኃን እድገት ባለሞያ እና የፕረስ ነፃነት ተቆርቋሪ ማሕበር  ድጋፍ ሰጭ ናቸዉ። 

« የማሸማቀቅና ማስፈራራት አካሄድን ፈርተዉ ጋዜጠኞች ራሳቸዉ አስቀድመው ምርመራን ያደርጋሉ  የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሳይቀር አንዳንድ ርዕሶቻቸዉን እንዲሁ አስቀድመው ይመረምራሉ፤ ለህትመትም አያበቁም ። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማቸዉን እንዳይዘጋባቸዉ በመፍራት ነዉ። ጋዜጠኞችም ቢሆኑ የገዛ ዘገቦቻቸዉን አስቀድመው የሚመረምሩት እስርና እንግልትን ለመሸሽ ነዉ። በዚህም ምክንያት በጎርጎረሳዊው 2104 2015 እና 2016 ዓም በርካታ ጋዜጠኞች ደቡብ ሱዳን ጥለዉ ሲሰደዱ አይተናል» ፓውል ዮኔ በደቡብ ሱዳን ምክር ቤት የመረጃ ኮሚቴ ዋና ተጠሪ እና ሕግ አርቃቂ ናቸዉ። ፓውል በደቡብ ሱዳን የመገናኛ ብዙኃን ዓለም ውስብስብ ችግር እና ከፍተኛ ተጽኖ እንዳለበት ቢያምኑም በቅርቡ ይህን ችግር ለመፍታት በሀገሪቱ ጥቂት የሚባሉ የባለሥልጣን መሥርያ ቤቶች ብቻ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ አልሸሸጉም።  

«ሁኔታውን በጥቅሉ ማየት ይጠበቅብናል። ምናልባት በጋዜጠኞች የሚቀርቡ አንዳንድ የመረጃ ጽሑፎች በደቡብ ሱዳን የፀጥታ ኃይላት ዓይን የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ይጥላል በሚል አስተሳሰብ ስለሚታይ ነዉ» የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ፍሰት በተመለከተ በቅርቡ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ባወጣዉ ዓመታዊ መዘርዝር ከ 180 ሃገራት መካከል ደቡብ ሱዳን 139 ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ባለፈዉ የጎርጎረሳዊ ዓመት 2018 ይፋ በሆነዉ መዘርዝር ደቡብ ሱዳን 144 ደረጃ ላይ ተቀምጣ ነበር። ባለፉት ዓመታት በደቡብ ሱዳን የጋዜጠኞች ግድያ፤ እስር ፤ ማሰቃየት እና ማስፈራራት እንደሚደርስባቸዉ የሚሳይ እጅግ አሳዛኝ ዘገባዎች ለአንባብያን መቅረቡ የሚታወቅ ነዉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ  

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች