የደቡብ ሱዳን ግጭትና ኤኮኖሚያዊዉ ተፅዕኖ | አፍሪቃ | DW | 15.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን ግጭትና ኤኮኖሚያዊዉ ተፅዕኖ

የደቡብ ሱዳን የተራዘመ ጦርነት በሀገሪቱ እና በአጎራባች ሃገራት ላይ የሚያስከትለዉን የኤኮኖሚ ወጪ የመዘነ ዘገባ ቀረበ። እንደዘገባዉ የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት በዚህ ይዞታ ከአንድ እስከ አምስት ዓመታት ከቀጠለ ከ22,3 እስከ 28 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር አዲሲቱን ሀገር ያሳጣታል።

ዘገባዉን ትናንት ናይሮቢ ዛሬ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ቀርቧል። «ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ያለዉ ግጭት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ደቡብ ሱዳን ግጭት ዉስጥ በቆየችባቸዉ ጊዜያት ከልማት እድሎች ልታገኝ ስትችል ያመለጣትን ወጪ መዝነናል። በተጨማሪም ጦርነቱ ቢራዘም ልታጣ የምትችለዉንም እንዲሁ አስልተናል። እናም ዓመታቱ በረዘሙ ቁጥር የምታጣዉ በ15 እና ሃና ቢሊዮኖች የሚቆጠር ነዉ። ምክንያቱም ጦርነቱ የሀገሪቱ ልማት አዝጋሚ እንዲሆን ነዉ የሚያደርገዉ። እና ግጭቱ ደቡብ ሱዳንን ብዙ ወጪ ይጠይቃታል። ይህ ደግሞ በደቡብ ሱዳን ብቻ አያበቃም የአካባቢዉንም ሃገሮች ይነካል።»

አማር ብሪከንሪንጅ መቀመጫዉን ሎንዶን ያደረገዉ ፍሮንትይር ኤኮኖሚስት ታዋቂ የኤኮኖሚ ባለሙያ ናቸዉ ። በዛሬ ዕለት አዲስ አበባ ላይ ይህንኑ ዘገባ ለጋዜጠኖች፣ ለመንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ለተመድ ድርጅቶች አቅርበዋል። እሳቸዉ እንደሚሉትም

Straßenbau in Juba Südsudan

የመንገድ ግንባታ በጁባ

የደቡብ ሱዳን ግጭት በቀጣይ ለአምስት ዓመታት የሚቀጥል ከሆነም የአካባቢዉን ሃገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳና ታይንዛንያን ስደተኞችን ለማስተናገድ፤ ለፀጥታ ማስከበሪያ እና ለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በጥቅሉ 53 ቢሊዮን ዶላር ሊያስወጣቸዉ እንደሚችል ነዉ ጥናቱ ያመለከተዉ። በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ለምታስተናግደዉ ኢትዮጵያ ይህ ምን ማለት ይሆን? አማር ብሪከንሪንጅ ያስረዳሉ።

«የተለያዩ ተፅዕኖዎች ይኖሩታል። በመጀመሪያ ከሰብዓዊ አኳያ እጅግ በርካታ ከቀያቸዉ የተፈናቀሉ ስደተኞች ወደኢትዮጵያ ገብተዋል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ለእነሱ መጠለያ በመስጠትም ሆነ የሚገኙበትን አካባቢ ፀጥታ በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሸክም ነዉ። በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ባላት ፍላጎት በማስተናገድና አንዳንድ አገልግሎቶች በሰፊዉ እየተሳተፈች በመሆኑ ግጭቱ በዚህ በኩልም ተፅዕኖ ያደርስባታል። ባጠቃላይ እንደኬንያ እና ዩጋንዳ ያሉ ሃገራት በደቡብ ሱዳን ያለዉ ግጭት ቢነካቸዉም ጦርነቱ ቢራዘም ተፅዕኖዉ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚጠና ማየት ይቻላል።»

ዘገባዉ እስካሁን የተካሄደዉ የእርስ በርስ ግጭት ጦርነትም የነዳጅ ሽያጩን አደናቅፎ የደቡብ ሱዳንን ኤኮኖሚ በ15 በመቶ እንዲቀንስ እንዳደረገዉም ዘርዝሯል። ካለፈዉ ዓመት ታኅሳስ ወር አንስቶ እስካሁን በዘቀለዉ ጦርነትም ከ10 ሺህ ሰዎች በላይ ሕይወት ጠፍቷል። ወደአንድ ሶስተኛ ገደማ የሚሆነዉ የሀገሪቱ ሕዝብ የረሃብ አደጋ አንዣቦበታል። ግጭት አለመረጋጋቱ በዚህ መልኩ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በጀመረዉ መንገድ የሚቀጥል ከሆነም ደቡብ ሱዳን ከኤኮኖሚ እንደገቷ 28 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ልታጣ ትችላለች።

Ärzte ohne Grenzen Médecins Sans Frontières MSF

የድንበር የለሽ ሃኪሞች ለተፈናቃዮቹ ርዳታ ሲያደርጉ

በሀገሪቱ ግጭቱ ያስከተለዉ የሰብዓዊና ኤኮኖሚዊ ወጪና ጉዳትም ጦርነቱ እንዲቆም አፋጣኝ ዓለም ዓቀፍ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆኑም በዘገባዉ ተጠቅሷል። ጥናቱ መካሄዱ መልካም ዘገባዉ መቅረቡ ብዙ ነገሮች አስቀድሞ እንዲታሰብባቸዉ ያደርጋልና ጥሩ ነዉ። ግን ለሸምጋዮች አስቸግረዉ ለዘመናት በእርስ በርስ ጦርነት ሲሰቃይ ኖሮ የራስ ሀገር ከተመሠረተ በኋላ ብዙም እፎይ ሳይል ለዳግም ጦርነት፤ ሞትና ስደት ለዳረጉት ሆኖም ተጋደልንለት ለሚሉት ሕዝባቸዉ እጅግም የሚጨነቁ የማይመስሉት ተቀናቃኞቹ አንጋፋ ፖለቲከኞች ለዘገባዉ ቁብ ይሰጡ ይመስሎታል? ብያቸዉ ነበር።

«ይህ ዘገባ የተባለዉ ወጭ ከቁጥጥር ዉጭ ከመሄዱ በፊት ግጭቱ በተቻለ ፍጥነት መቆም እንደሚኖርበት ለሁለቱም የደቡብ ሱዳን መሪዎችም ሆነ ለአካባቢዉ ሃገራት መሪዎች ምልክት ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ዘገባዉ በግልፅ እንዳመለከተዉ ደቡብ ሱዳን ብቻ ሳትሆን አካባቢዉ ባጠቃላይ ብዙ ገንዘብ ያጣል። እናም ጦርነቱ ባስቸኳይ መቆሙ ለሁሉም የተሻለ ነገር ነዉ የሚሆነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic