የደቡብ ሱዳን የሠላም ድርድር ክሽፈት | አፍሪቃ | DW | 06.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን የሠላም ድርድር ክሽፈት

ጦርነቱ አላባራም።ሰዉም ያልቃል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከቦምብ፥ ጥይት የተረፈዉ ሕዝብ ይሰደዳል።ይፈናቀላል።ለሚሊዮን ጥቂት ቀረዉ።ተፈናቃይ፥ ስደተኛዉ ለከፋ ረሐብ ተጋልጧል።ሐገርም ይጠፋል።

ደቡብ ሱዳንን የሚያወድመዉን ጦርነት ለማስቆም የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች አዲስ አበባ ዉስጥ ያደርጉት የነበረዉ ድርድር ያለ ዉጤት አብቅቷል።ተፋላሚዎችን የሚያደራድረዉ የምሥራቅ አፍሪቃ በይነ-መንግሥታት የልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) እንደሚለዉ የተቋረጠዉ ድርድር መጋቢት አስራ-አንድ ዳግም ይጀመራል።የተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች ግን ለድርድሩ መቋረጥ አንዳቸዉ ሌላቸዉን እየወቀሱ ነዉ።ግጭት ጦርነቱም የመቆም አዝማማሚያ አይታይበትም።የዶቸ ቬለዉ ጄምስ ሺማንዩላ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።


ርዕሠ-ከተማ ጁባ የተጀመረዉ ዉዝግብ፥ ግጭት-ዉጊያ የአዲሱቱን ሐገር አብዛኛ ክፍለ-ግዛቶች አዳርሶ ትናንት ዳግም ወደ ርዕሠ-ከተማይቱ የተመለሰ መስሎ ነበር።ታሕሳስ አጋማሽ የመጀመሪያዉ ጥይት የጮኸበት ትልቁ የጁባ ጦር ሠፈር ትናንት ሲነጋጋ ጀምሮ በከባድ ተኩስ ሲናወጥ ነዉ ያረፈደዉ።የቱኩስ ሰበብ-ምክንያት እየደየተመልካቹ ለየቅል ነዉ።መንግሥት በወታደሮች የደመዝ ክፍያ ሠበብ የተነሳ ጊዚያዊ ግጭት በማለት ነገሩን አቃሎታል።ሌሎች ምንጮች ግን የፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር ታማኞች እና ኪርን ይቀናቀናሉ የሚባሉ የአንድ ጄኔራል ደጋፊዎች ያበቀሉት ጠብ ነዉ ባዮች ናቸዉ።

በትናንቱ ግጭት በትንሹ አምስት ወታደሮች መገደላቸዉን መንግሥትም አምኗል።ትናንት ለዛሬ አጥቢያም በሌሎች የጁባ አካባቢዎች ተኩስ መሰማቱ ተዘግቧልም።ተፋላሚ ወገኖች ከዚሕ ቀደም የፈረሙት ተኩስ አቁም ዉል ስቶ ጦርነቱ በየአካባቢዉ የሚያጠፋዉ ሕይወት፥ ሐብት ንብረት መናሩ ሲነገር፥ ጥፋቱን ያቆማል የሚል ተስፋ የተጣለበት ድርድርም ከሸፈ።የአማፂዎቹ መሪ የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ሪክ ማቼር ከተደበቁበት ሥፍራ ሆነዉ ለድርድሩ መክሸፍ ተጠያቂዉ መንግሥት ነዉ ባይ ናቸዉ።

«ገና ሲጀመር ችግር የተመላ ነበር።የተፈረመ ስምምነት እንኳን አልተከበረም።ከታሠሩ ፖለቲከኞች አራቱ አሁንም እንደታሰሩ ነዉ።በክሕደት ወንጀል በሐሰት ተከሰዋል።ሌሎቹ ሰባቱ (ሰባቱ) በኬንያ መንግሥት ሐላፊነት በዋስ ተለቀዋል።መንግሥት ከመጀመሪያዉ ዕለት ጀምሮ እንዳጠቃን፥ እንደዘመተብን ነዉ።ሥለዚሕ መሻሻል ባይታይ አያስደንቅም።»

የደቡብ ሱዳኑ ማስታወቂያ ሚንስትር ማይክል ማኩይ ሠላም ያመጣል ለተባዉ ድርድር መክሸፍ ከመንግሥታቸዉ አንጣዎች ይልቅ-አደራዳሪዎችን ነዉ የወቀሱት።

«ያሁኑ ዙር (ድርድር) የታለመለትን ግብ አልመታም።ለሕዝባችን ሠላም ይዘን እንመለሳለን የሚል ተስፋ ነበረን።እንዳለመታደል ሆኖ እንደታቀደዉ አልሆነም።ይሕ የሆነዉ በተቀናቃኞቹ ሐይላት አይደለም።ለንደራደራቸዉ ከሔድንባቸዉ አማፂያን ይልቅ መልዕክተኞቹ እና አደራዳሪዎቹ እንቅፋት በመሆናቸዉ ነዉ የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ።»

የፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር መንግሥት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወንጀል አስሮ በአደራዳሪዎች ግፊት በዋስ የለቀቃቸዉ ሰባት ፖለቲከኞች በአዲስ አበባዉ ድርድር መካፈላቸዉን የጁባ መንግሥት አልፈቀደዉም።ማስታወቂያ ሚንስትሩ እንደሚሉት በጦርነቱ የሌሉበት ወገኖች በድርሩ እንዲሳተፉ ሊፈቀድላቸዉ አይገባም ነበር።

«አንፈልጋቸዉም ምክንያቱም ነፍጥ አላነሱም።ይሕ ብቻ አይደለም የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ንቅናቄ (SPLM) አባልነን ይላሉ።SPLM ከሆኑ SPLM በዉስጡ ለሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ የሚሰጥበት ደንብ አለዉ።SPLM ከሆኑ የSPLM ጉዳይ ከሐገሪቱ ዉጪ ለዉይይት አይቀርብም።»

ጦርነቱ አላባራም።ሰዉም ያልቃል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከቦምብ፥ ጥይት የተረፈዉ ሕዝብ ይሰደዳል።ይፈናቀላል።ለሚሊዮን ጥቂት ቀረዉ።ተፈናቃይ፥ ስደተኛዉ ለከፋ ረሐብ ተጋልጧል።ሐገርም ይጠፋል።በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ ርዳታ አስተባባሪ ቶቢይ ላንሰር ከወደሙት ከተሞች አንዷን ማላካል እንዲሕ ይገልፁዋታል።

«ይቺ የተራቆተች ከተማ ናት።ሆስፒታሏ ኦና ነዉ።ወደ ከተማ መሐል የገባነዉ በእጅግ አደገኛ ሁኔታ ነዉ።ማላካልን ያገኘናት ለደሕንነት ጨርስዋ ዋስትና የሌለባት ከተማ ሆና ነዉ።ከከተማይቱ ያልወጡ ሰዎችም እኛ ከለላና መጠለያ እንድሰጣቸዉ የሚፈልጉ ናቸዉ።ዉሐ፥ ምግብ፥ ሕክምና እንዲያገኙ የምንችለዉን ሁሉ እናደርጋለን።ግን በጣም አስቸጋሪና የተጨናነቀ ሁኔታ ነዉ።ማድረግ ያቀድነዉ ለተጨማሪ ሰዎች ማስፈሪያ ቦታ ለማዘጋጀት እየጣርን ነዉ።»

ላንሰር በጠቀሱት በማላካል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጥር ግቢ ዉስጥ አንድ መቶ ሺሕ ሕዝብ ተፋፍጎ ተጠልሏል።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠAudios and videos on the topic