የደቡብ ሱዳን ውዝግብ | አፍሪቃ | DW | 23.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን ውዝግብ

ከ 60 በላይ ብሔር ብሔረ ሰቦች በሚኖሩባት በደቡብ ሱዳን ውጊያው ካለፉት አራት ወራት ወዲህ እንደቀጠለ ነው። የዲንካ ጎሣ ተወላጅ በሆኑት በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ከኑዌር ጎሣ በሚወለዱት በቀድሞው ምክትላቸው

ሪየክ ማቸር መካከል ባለፈው ታህሳስ ወር በሥልጣን ሽኩቻ ሰበብ በቀጠለው ውጊያ ብዙዎች ሲገደሉ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተለይ ባለፈው ሳምንት ዓማፅያኑ የቤንን ከተማ ሲይዙ በብዛት የዲንካ ጎሳ አባላት የሆኑ ከ200 መቶ የሚበልጡ ሰዎች ከተገደሉ እና ወደ 400 የሚጠጉ ከቆሰሉ በኋላ የፖለቲካ ተንታኞች ውዝግቡ ወደ ጎሳ ግጭት እየተቀየረ ነው በሚል ማጠያየቅ ይዘዋል። ባለፈው ሳምንት ደቡስ ሱዳን ውስጥ የተፈፀመውን የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጠፋ አሜሪካን ዘንጋናኝ ግድያ ስትል አወግዛለች ። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ደጋፊ ተዋጊዎች ባለፈው ሳምንት በያዟት ቤንቱ በተባለችው ከተማ በመስጊዶች በአብያተ ክርስቲያንና በሆስፒታሎች የተጠለሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን የተመድ ዘግቧል ። አማፅያን በቤንቱ ድል መቀዳጀታቸውን ካወጁ በኋላ ግድያው ለ2 ቀናት መካሄዱን የተመድ አስታውቋል ። አማፅያን ግን ግድያውን የፈፀሙት ከከተማይቱ ያፈገፈጉ የመንግሥት ወታደሮች ናቸው ይላሉ ። የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄይ ካርኒ እጅግ ዘግናኝ ያሉት ይህ ግድያ የደቡብ ሱዳን ህዝቦች በመሪዎቻቸው ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳጣ እንደሆነም አስታውቀዋል ።

ካርኒ እንዳሉት ስለግድያ የወጡ የምስል ዘገባዎች በአንድ መስጊድ ውስጥ የተከማቹ አስከሬኖችን ፣ሆስፒታል ውስጥ የተገደሉ በሽተኞችን እንዲሁም በየጎዳናውና በአብያተ ክርስቲያን ውስጥ ተተኩሶባቸው የሞቱ ሰዎችን ያሳያል ። እንደ ቃል አቀባይዋ ሰዎቹ የተገደሉት በጎሳቸውና በዜግነታቸው ምክንያት ሲሆን የአካባቢው ራድዮ ጣቢያዎች ጥላቻን የሚያስተጋቡ መልዕክቶችን ያስተላልፉ ነበር ። የቤንቱው ግድያ 4 ወራት በዘለቀው የደቡብ ሱዳን ግጭት ከደረሱት ግድያዎች እጅግ ዘግናኙ ነው ። ባለፈው ሳምንት በመንግሥት በሚቆጣጠራት ቦር በተባለችው ከተማ ታጣቂዎች በተባበሩት መንግሥታት ጦር ሰፈር በከፈቱት ተኩስ በዚያ የተጠለሉ 58 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ። ከዚሁ ጋርም በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማውረድ የተጀመረው ጥረት በአዲስ መልክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቻይና ጠየቀች ። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በቤንቱ የተፈፀመውን ግድያ አውግዘው ተቃዋሚዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ወገኖች በተቻለ ፍጥነት እርቀ ሰላም እንዲወርድ በፖለቲካዊ ውይይት እንዲገፉ ጥሪ አቅርበዋል ። ከዚህ በተጨማሪም የደቡብ ሱዳን መንግሥት ባለስልጣናት ለቻይና መብቶች እንዲሁም ደቡብ ሱዳን ለሚገኙ ቻይናውያን ደህንነት ጥበቃ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል ። ቻይና በደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ከሚያፈሱ ሃገራት አንዷ ናት ።

ካትሪን ማቴ

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic