የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ተባርረዋል መባላቸውን አስተባበሉ | አፍሪቃ | DW | 24.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ተባርረዋል መባላቸውን አስተባበሉ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የኢትዮጵያ አማጽያን በዋና ከተማይቱ ጁባ ጽህፈት ቤት እንዲከፍቱ ተሰማምተዋል መባሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ የሀገሪቱን አምባሳደር ማባረሯ ትናንት ማምሻውን ተዘግቦ ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ግን ስምምነቱንም ሆነ ተባርረዋል መባሉን  አስተባብለዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:34

ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን አልሻከረም ብላለች

የደቡብ ሱዳኑ ሬድዮ ታማዙጅ የኢትዮጵያ መንግስት ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለውን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰኑን ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንን ጠቅሶ ባሰራጨው ዜና አውጇል፡፡ እኚሁ ባለስልጣን ኢትዮጵያ ሀገሪቱን በአፍሪቃ ህብረት ጭምር የሚወክሉትን አምባሳደር ከሀገር ማስወጣቷን መኮንናቸውም ተገልጿል፡፡

ተባርረዋል የተባሉት የደቡብ ሱዳኑ አምባሳደር ጄምስ ፒታ ሞርጋን ግን ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘው ቢሯቸው ነበሩ፡፡ ለዶይቸ ቨለ በስልክ በሰጡት ቃለ ምልልስም ዜናውን “ሀሰት” ብለውታል፡፡

“አሁን በቢሮ ነው ያለሁት፡፡ በቅርቡ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ስራ ተጠምደናል፡፡ ፕሬዝዳንቴ ስብሰባውን ለመካፈል ይመጣሉ፡፡ የተወሰኑ የልዑካን አባላት ቀድመው ገብተዋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ዛሬ ማታ ይገባሉ፡፡ ይህ አሉባልታ ከየት እንደመጣ አናውቅም ነገር ግን በእርግጠኝነት የምናወቀው ከቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር ጋር የወገኑ አማጽያን እና በመንግስትም ውስጥ ሆነ ከመንግስት ውጭ ያሉ ሌሎች ተቃዋሚ ቡድኖች ናቸው እንደዚህ አይነት አሉባልታ ሊያዛምቱ የሚችሉት” ይላሉ አምባሳደሩ፡፡   

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቃባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ እንደ አምባሳደሩ ሁሉ መረጃውን “መሰረተ ቢስ” ሲሉ ያጣጥሉታል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግስት አሰራራችን ሁልጊዜም ቢሆን  ያው ግልጽ ነው አይደለ? ማለት ምንድነው ልዩነቶች እንኳ ቢኖር እንወያይ ነው የምንለው፡፡ ለምሳሌ ከኤርትራም ጋር እንኳ እንወያይ ነው እኛ የምንለው፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ሁለቱ ሀገራት ጎረቤቶች ናቸው፡፡ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በጋራ ለመስራት ተስማምተው እንደውም በቅርብ ጊዜ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ የበለጠ ለመስራት እንዲመች ስምምነቶችን ተፈራርመው ያሉ ሀገራት ናቸው፡፡ የሚደጋጋፉ ሀገራት ናቸው፡፡ ስለዚህ ያልከው ነገር መሰረት ቢስ ነው” ብለዋል ቃል አቃባዩ፡፡     

አምባሳደሩም ሆነ ቃለ አቃባዩ ይህን ይበሉ እንጂ የምስራቅ አፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ውጥንቅጥቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የመጣ ይመስላል፡፡ ግብጽ በቀጠናው ላይ ያላት ከፍተኛ ፍላጎት እና በየጊዜው የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻዎችን እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ ግብጽ በተከታታይ ወደ ቀጠናው የምትልካቸው የተለያየ አጀንዳ ያነገቡ ልዑካንን እንዳሉ ሆነው በመሪዎች ዘንድ የሚደረጉ ጉብኝቶችም ጨምረው ታይተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወር ብቻ በፊት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እና የደቡብ ሱዳኑ አቻቸው ወደ ግብጽ ተጉዘዋል፡፡ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በበኩላቸው ወደ ኡጋንዳ ብቅ ብለው ነበር፡፡ ከእርሳቸው ጉብኝት ሶስት ቀናት በኋላ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ይፋዊ ላልሆነ ጉብኝት ወደ ጁባ አቅንተዋል፡፡ የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር ወደ ግብጽ የሄዱት የሙሴቪኒን ጉብኝት ተከትሎ ነው፡፡

ግብጽ በአንድ ወገን ከኤርትራ ጋር ጥምረት መመስረቷ የተዘገበ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከኡጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሶስትዮሽ ህብረት መፍጠሯ ሲወራ ሰንብቷል፡፡ በሃገራቱ መካከል የተለያዩ ዉሎች ቢፈፀሙም ከሁሉም ትኩረትን የሳበው ግን ግብጽ ከደቡብ ሱዳን ጋር አድርጋዋለች የተባለው ስምምነት ነበር፡፡ እንደ ግብጽ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ ደቡብ ሱዳን በግብጽ አግባቢነት ለኢትዮጵያ አማፅያን መጠለያ ለመስጠት እሺታውን ገልጻለች፡፡ የደቡብ ሱዳኑ አምባሳደር ግን ይህንንም ያስተባብላሉ፡፡

“ፕሬዝዳንታችን፣ ሀገራችንም ሆነ ህዝባችን- ኢትዮጵያም ሆነ ሱዳን፣ ኬንያም ሆነ ኡጋንዳ- ጎረቤታችንን ለማወክ የሚፈልጉ አማፅያንን የመርዳት ምንም ዓይነት ፍላጎት የላቸውም፡፡ ከዚህም ሌላ እኛ የራሳችን ችግር ያለብን እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሞከርን ያለን ነን ፡፡ ሀገራቸውን ለማወክ ለሚፈልጉ ቡድኖች የደቡብ ሱዳንን መሬት ለመፍቀድ የሚሆን ጊዜ የለንም፡፡ ደቡብ ሱዳን በፍጹም የየትኛውም ቡድን መንደርደሪያ ስፍራ አትሆንም” ሲሉ የሀገራቸውን አቋም አሳውቀዋል፡፡

ስለ ግብፅ የሰሞኑ እንቅስቃሴ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር አድርገዋለች ስለ ተባለለው ስምምነት ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተወልደ በቀጥታ ምላሽ መስጠት አልፈለጉም፡፡ የግብጽን ስም ሳይጠቅሱ ጠቅለል ያለ ምላሽ እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡፡

“መረዳት ያለብን ምንድነው? የትኛውም ሀገር ቢሆን ከሌሎች ጋር ያለውን የራሱን ግንኙነት የሚወስነው ራሱ ነው፡፡ እኛም እንደሀገር ደግሞ ከሌሎች ሀገሮች ጋር የሚኖረን ግንኙነት የምንወስነው በጋራ ከእነኚያ ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር በምንገባው ውልና ስምምነት መሰረት ነው፡፡ ግን የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በሚመለከት ሁሉንም ነገር እንከታተላለን ምክንያቱም ያንን የማስጠበቅ ኃላፊነት ስላለብን” ብለዋል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደ ደቡብ ሱዳኑ ኪር ሁሉ የግብጹ አልሲሲም ይገኛሉ ተብሏል፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ

 

 

Audios and videos on the topic