የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችና ኢጋድ | ዓለም | DW | 18.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችና ኢጋድ

አዲስ-አበባ ምርጥ ሆቴሎች እየዋሉ-እያደሩ እንዲደራደሩ አሥራ-ሰባት ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰላቸዉ ሹማምንት ግን የዚያን ሕዝብ-እልቂት-ስደት ፤ ችግርና ችጋር ለማቆም ተነጋገሩ-ሲባሉ እንቢኝ ይላሉ።«እሺ» እንዲሉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ «ቆንጠጥ»-ሊያደርጋቸዉ ይገባል።

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላት ተወካዮች ለአዲስ ድርድር ይዘዉት የነበረዉን ቀጠሮ መሠረዛቸዉ ስድስት ወራት ያስቆጠረዉን ጦርነት ለማስቆም ለሚደረገዉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሌላ እንቅፋት ሆኗል።የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ቀጠሮዉን ለመሠረዛቸዉ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)ን ይወቅሳሉ።ለወቀሳዉ የሰጡት ምክንያት ግን ለየቅል ነዉ።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ደግሞ ተፋላሚ ሐይላት የሠጡት ምክንያት የድርድሩን ሒደት በሠበብ አስባቡ ለመግፋት ነዉ።

«እዚሕ ከኛ ጋር የሌሉት ሁለቱ ወገኖች» አሉ ዋና አደራዳሪ አቶ ስዩም መስፍን ባለፈዉ ሰኞ-«እንደማይመጡ ነግረዉናል» አከሉ አንጋፋዉ ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት-አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደጠቀሰዉ።

ሁለቱ ወገኖች አዲስ አበባ ላይ የተያዘዉን ቀጠሮዉን ለመሠረዛቸዉ የሰጡት ምክንያት ለየቅል-የወቀሱት ግን ያንኑ አደራዳሪነቱን የተቀበሉትን ማሕበር ነዉ።ኢጋድን።የጁባ መንግሥት ተወካዮች -የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ማሕቡብ መዓሊም ባለፈዉ ሳምንት የተናገሩት ሥላስቀየመን ማብራሪያ እስኪሰጠን-«በድርድሩ አንካፈልም» ባዮች ናቸዉ።የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ማሕቡብ መዓሊም ሁለቱ ወገኖች በጦርነት ድል እናደርጋለን ብለዉ ካሰቡ «ደደብ» ናቸዉ ብለዉ ነበር።አዎ-«ደደብ» ናቸዉ ጨመሩላቸዉ የአፍሪቃ ፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ጃኪ ሲሊየ-ዛሬ።

«አዎ እንደሚመስለኝ ሁለቱም ወገኖች በርግጥ ደደቦች ናቸዉ።የኢጋድ ዋና ፀሐፊ መሐቡብ የሰጡት አስተያየትም ሁለቱ ወገኖች ለድርሩ ሒደት ቀና መንፈስ ከማሳየት ይልቅ ለጦር ሜዳዉ ዘመቻ ትኩረት መስጠታቸዉን የሚያመለክት ነዉ።ካለፈዉ ጥር ጀምሮ የሚያደርጉትም ይኽንኑ የሚያረጋግጥ ነዉ።»

የአማፂያኑ ተወካዮች ደግሞ-ኢጋድን የወቀሱት በድርድሩ የሚካፈሉትን የመንግሥት ተወካዮች ማንነት፤ የሥልጣን ደረጃና ብዛት ኢጋድ አስቀድሞ አላሳወቀንም የሚል ነዉ።«ግልፅነት የጎደለዉ» ብለዉታል የኢጋድን አሠራር።ዶከተር ሲሊየ እንደሚሉት ግን የሁለቱም መልዕክት-ሌላ ነዉ።

«ሁለቱም ምክንያቶች የማዘግየት ሥልቶች ናቸዉ።ኢጋድ ትክክለኛ አደራዳሪ እንዳልሆነ ለማሳየት የሚደረገዉ ሙከራም እርስ በርስ አለመተማማናቸዉንና ለሠላም ሒደቱ ደንታ እንደሌላቸዉ ጠቋሚ ነዉ።»

ሁለቱ ወገኖች ሲሻቸዉ እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ፤ ሲላቸዉ ኢጋድን ሲወቅሱ ከጦርነት-ሳይወጣ ከሌላ ጦርነት የማገዱት ሕዝብ እያለቀ፤ እየተራበ፤ እተሰደደ ነዉ።በቅርቡ ደቡብ ሱዳንን የጎበኙት የኢጋድ አጣሪና ተቆጣጣሪ ቢሮ ሐላፊ አምባሳደር ተፈራ ሻዉል እንደሚሉት ዉጊያዉ ከሞላ ጎደል ቆሟል።ከተሞች ግን ባዶ ናቸዉ።

ሠላም-ነዉ ግን ባዶ ነዉ።ከተማ-መንደሩን ለቅቆ-የተሰደደ ወይም የተፈናቀለዉ ሕዝብ ከ1,3 ሚሊዮን በልጧል።ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ደግሞ ለረሕብ-ተጋልጧል።የሞተዉን በአስር-ሺሕ ከመገመት ባለፍ የቆጠረዉ የለም።

አዲስ-አበባ ምርጥ ሆቴሎች እየዋሉ-እያደሩ እንዲደራደሩ አሥራ-ሰባት ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰላቸዉ ሹማምንት ግን የዚያን ሕዝብ-እልቂት-ስደት ፤ ችግርና ችጋር ለማቆም ተነጋገሩ-ሲባሉ እንቢኝ ይላሉ።«እሺ» እንዲሉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ «ቆንጠጥ»-ሊያደርጋቸዉ ይገባል።

«ዲፕሎማሲያዊዉን ጥረት መቀጠል፤መፍትሔ ለማግኘት እስካሁን ያለዉን አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር፤ሁለቱም ወገኖች በጦር ወንጀለኝነት እንደሚጠየቁ ግፊት ማድረግ-ምናልባት ያለዉ ብቸኛ አማራጭ ነዉ።»

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic