የደቡብ ሱዳን ቀውስና የማዕቀብ ዛቻ | አፍሪቃ | DW | 23.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳን ቀውስና የማዕቀብ ዛቻ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ማዕቀብ የመጨረሻው አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አመለከቱ። ከዚህም ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው ተጨማሪ ጦር ወደ ሶማሊያ ለማዝመት ዝግጁ እንደሆነች መግለፃቸዉንም የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል።

ከደቡብ ሱዳን አስር ግዛቶች በስፋት ጆንጌሊን የሚያክል የለም። አለም አቀፉ የቀውስ ተመልካች ቡድን (International Crisis Group) ትናንት ባወጣው ዘገባ ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰነው ጆንጌሊ ለዘመናት የተዘፈቀችበትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አትቷል። እንደዚህ ዘገባ ከሆነ የጆንጌሊ ግዛት ከደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ግጭት በፊትም ቢሆን በጎሳ ልዩነት፤በታጣቂዎች ግጭት እና በተረጋጋ መንግስት እጦት ስትታመስ ቆይታለች። በግዛቲቱ የሚኖሩት የዲንቃ፤ኑዌርና ሙርሌ ጎሳዎች ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሰላማዊ ግኙነት ሳይኖራቸው መቆየታቸውን የአለም አቀፉ የቀውስ ተመልካች ቡድን ዘገባ ያትታል።


የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ግጭት ከአንድ አመት በፊት ሲቀሰቀስ የመንግስት ደጋፊ እና ተቀናቃኝ ታጣቂዎች ጦርነት የግዛቲቱን ደካማ አስተዳድር እና ኢኮኖሚ ጨርሶ ከማድከሙም ባሻገር የሰብዓዊ እርዳታ ስራዎችን አስተጓጉሏል። የጆንጌሊ ነዋሪዎች በተለይም ሴቶችና ህጻናት የገጠማቸው ስደት እና እንግልት ግን የመላዋ ደቡብ ሱዳናውያን እጣ ፈንታ ሆኗል።
የደቡብ ሱዳንን ተቃናቃኞች የማደራደር ሃላፊነቱን የወሰደው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ በአንድ አመት ጥረቱ ጠብ የሚል ውጤት አላስመዘገበም። በጉዳዩ ላይ ትናንት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ማዕቀብ የመጨረሻው አማራጭ እንደሆነ መናገራቸውን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። የምስራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዩሱፍ ያሲን የቀጠናው ሀገራት ማዕቀብን እንደማስፈራሪያ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ይናገራሉ።
«ተደጋግሞ የሚነገረውና የሚያስፈራሩበት ማዕቀብ መጣሉ ላይ ነው። ማዕቀብ የሚጣለው በኢጋድ አባል ሃገራት ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያን ሃገሮች አሉ።ለጋሾች አሉ። ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት አሉ። እና የአፍሪካ ህብረት አለ። እነዚህ የመሳሰሉትን ሁሉ ነው በእሳቤ የያዙት። ከማዕቀብ በፊት አስፈራርቶ ማስታረቅ ነው። ፈረንጆቹ ዱላና ካሮት የሚሉት አይነት ይመስለኛል።»
የፖለቲካ ተንታኙ ዩሱፍ ያሲን በተለያዩ ጉዳዮች የተወጠረው አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሄ የማፈላለጉን ሃላፊነት ለምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ በውክልና መስጠቱን ይናገራሉ። ይሁንና የቀጠናው ሃገራት በደቡብ ሱዳን ጉዳይ በጥቅም ግጭት ውስጥ በመግባታቸው መፍትሄ ማበጀት እንደተሳናቸው ዩሱፍ ያሲን ያስረዳሉ።


«እነዚህ የተለያዩ አጎራባች ሃገሮች የራሳቸው መጠበቅ ያለባቸው ጥቅማ ጥቅሞች አሏቸው። የሙሴቬኒን ጉዳይ ብንወስድ ሰራዊቱን እስከመላክና ሌሎቹ ደግሞ ሰራዊትህን ማስወጣት አለብህ እስከ ማለት ድረስ የተደረሰበት፤እራሱ የደቡብ ሱዳን መንግስት ኢትዮጵያን በተዘዋዋሪ መንገድ የከሰሰበት፤ሰሜን ሱዳንን የከሰሰበት የተለያዩ ጥቅሞች ይበልጥ የሚያወሳስበው ጉዳይ ነው።»
በአፍሪካ ህብረት የሶማልያ ሰላም አስከባሪ ሃይል አሚሶም ስር ላለፉት ሃያ ወራት በሶማልያ የዘመቱት የሴራሊዮን ወታደሮች የአገልግሎት ጊዜያቸው ተጠናቆ ወደ ሃገራቸው በመመለስ ናቸው። በኢቦላ ስጋት የሚተካ የሴራሊዮን ጦር ወደ ሶማሊያ እንደማይዘምት አሚሶም አስታውቋል።ትናንት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሶማሊያ ለቆ የሚወጣውን የሴራሊዮን ጦር ኢትዮጵያ ለመተካት ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል። ካሁን ቀደም የሶማሊያ ጎረቤት ሃገሮች የሰላም አስከባሪ እንዳያዘምቱ የተላለፈውን ውሳኔ ያስታወሱት የፖለቲካ ተንታኙ ዩሱፍ ያሲን ኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ ሊመጣ ከሚችለው የሽብር አደጋ ይበልጥ የውስጥ ፖለቲካዋም አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic