የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ | ኢትዮጵያ | DW | 06.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ወር ብቻ ከአራት ሺህ በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ኢትዮጵያ መድረሳቸውን አስታወቀ። በኢትዮጵያ የጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር 267,000 ሲሆን በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ብቻ 110,000 ሊጨመሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ሪየክ ማቻር መቃቃር ደቡብ ሱዳን ሰላም ካጣች ሰነባበተች። ደቡብ ሱዳናውያንም ጦርነትና ግጭት ለመዳን ሰላም ፍለጋ ቀያቸውን ጥለው ሽሽት ይዘዋል። ባለፈው ወር ብቻ ከ4,000 በላይ ደቡብ ሱዳናውያን በኢትዮጵያ ወደሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች መትመማቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ክሡት ገ/እግዚአብሄር «በፈረንጆች አቆጣጠር ከታህሳስ 2013 ጀምሮ ብዛት ያላቸው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ ነበር።ከባለለፈው አጋማሽ ጀምሮ የ2015 የመጀመሪያ ሶስት ወራት በአማካኝ በወር ወደ 1,000 ስደተኞች ነበር የሚመጡት።አሁን በሚያዝያ ወር ግን ቁጥሩ በ አራት እጥፍ አድጎ ከ4,000 በላይ ስደተኞች ናቸው የመጡት።» ሲሉ ተናግረዋል።


ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. የቀድሞ የትግል አጋራቸውን እና የአዲሲቱን ደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻርን ከስልጣን ሲያባርሩ የተጀመረው ግጭት ከ10,000 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በምስራቅ ኣፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን -ኢጋድ አማካኝነት ሲካሄድ የከረመው ድርድር አደራዳሪዎቹን ተስፋ አስቆርጦ ያለ ውጤት ተቋርጧል። በትክክል መቼ፣እንዴትና የት እንደሚጀመርም አይታወቅም። የደቡብ ሱዳንን መገንጠል በገንዘብና በፖለቲካ ስትደግፍ የከረመችው የዩ.ኤስ. አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በኬንያ ጉብኝታቸው ወቅት የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ሪየክ ማቻርን ግትርነት ተችተዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለደቡብ ሱዳን ቀውስ ተጠያቂ የሆኑ ሰዎች የሚዳኙበት የፍትህ ሥርዓት ቢቋቋም አገራቸው በገንዘብ ለመደገፍ ዝግጁ ነች ብለዋል። እስከዚያው ግን አገሪቱ መረጋጋት አልሆነላትም። ባለፈው ወር እንኳ በአፐር ናይል እና ማላካል አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸው ተሰምቷል። ከስደተኞቹ መካከል ህጻናትና ሴቶች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ የሚናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ አቶ ክሡት ገ/እግዚአብሄር «202,000 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአሁኑ ግጭት ከተከሰተ ወዲህ ነው። ወደ 60,000 የሚጠጉ ከዛም በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበሩ። በአጠቃላይ 267,000 የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ።» ብለዋል።


ስደተኞቹ ከመኖሪያ ቀያቸው እስከ መጠለያ ጣቢያ ካለ በቂ ውሃና ምግብ ለመጓዝ እንደሚገደዱ እንዲሁም በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል የሚገኙ የስደተኞች ጣቢያዎች እየሞሉ በመሆናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር የማስፋት ስራ እየራ መሆኑን አቶ ክሡት ተናግረዋል። ድርጅታቸው በዚህ አመት ብቻ 110,000 ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ይጠብቃል።
እሸቴ በቀለ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic