የደቡብ ሱዳን ሕዝበ-ዉሳኔ | ኢትዮጵያ | DW | 10.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የደቡብ ሱዳን ሕዝበ-ዉሳኔ

የዛሬ አስራ-ስምንት አመት ግድም ካስመራ-ተመሳሳይ ቃል ተስምቶ ነበር።በሁለት ሺሕ-ሁለት ከዲሊ-ምሥራቅ ቲሞር፥ ክዚያ በፊትና በመሐሉ ከብዙ የቀድሞ የሶቬት ሕብረት ሪፐብሎክ ርዕሠ-ከተሞች ብዙ ተስምቶ ነበር።ዛሬ ጁባ ነዉ-ተረኛዉ።ነገስ?

default

የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ዓርማ


10 01 11

የሐይለኛዉ አማፂ ቡድን ሐይለኛ መሪ ከያኔ-እስካሁንና አሁን የሚሆነዉን ለማድረግ-ለማየትም በርግጥ አልታደሉም።የነፃነት ፍቅር ፅናታቸዉ ለአማፂ ቡድን መሪነት፣የወታደርነት ብቃታቸዉ ለኮለኔልነት፣ የእርሻ እዉቀታቸዉ ለዶክተርነት አበቃቸዉ እንጂ ነብይ አልነበሩምም።ያሁን እዉነት- ግን ያኔ አሉት።«ዛሬ የሱዳን ቀን ነዉ።የአካባቢዉ ቀን ነዉ።ጫቃ ከገባዉ ልክ አርባ-ሁለተኛ አመቱ ነዉ።አርባ ሁለት ዓመት።ለመጀመሪያ ጊዜ ጫካ የገባሁት በዚሕ ዕለት ነበር።ታሕሳስ ሰላሳ-አንድ 1962። ሥለ ዚሕ ከስምምነት መድረስ ለኛ ምን ያሕል አስደሳች እንደሆነ መገመት ትችላላችሁ።»

ኮሎኔል ዶክተር ጆን ጋራንግ።ጥር ሁለት ሺሕ አምስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የደቡብ ሱዳን ሕዝበ-ዉሳኔ መነሻችን፣ የጥቅል ሱዳን-ጥቅል እዉነት ማጣቃሻ፥ የሱዳን ሁለትነት መድረሻችን ነዉ-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

የደቡብ ሱዳን ሕዝብ-እየሳቀ፥ እያዜመ፣ እየዘመረ፣ድምፁን ሰጠ።የተሰጠዉን ድምፅ ብዛት-ዉጤት ብዙዎች እንደሚያምነት ከታትስቲክስ ስሌት፣ ከመገናኛ ዘዴዎች ፍጆታ፣ከታሪክ ሰነድነት፣ ከሕጋዊ ዋቢነት ባለፍ-መጠበቅ አያስፈልግም።ጋራንግ ለአርባ ሁለት፣ ቀዳሚዎቻቸዉ ለግማሽ ምዕተ-አመት የተዋጉ፥ የገደሉ-የሞቱለት ነፃነት-አሁን ከእርግጥ በላይ ቃል ካለ እርግጥነቱ በድምፅ ሰጪዉ ሕዝብ ተረጋገጠ።እሱ አንዱ ነዉ።

«የመጀመሪያዉ የግል ስሜቴ እኔ ነፃነኝ የሚል ነዉ።የሚቀጥለዉ ትዉልድ ደግሞ ይበልጥ ነፃ ይሆናል።እኛ በኖርንበት-መንገድ አይኖሩም።ያየነዉን ፈተና አያዩም።ድምፄን ስሰጥ ፍቅሬን እንደሰጠሁ ነዉ-የሚሰማኝ።»

ካርቱሞች ለሞስኮ-ሲያድሩ፣ እነ ገራግን ከዋሽንግተኖች፣ ካርቱሞች ከዋሽግተን ጉያ ሲወሸቁ፣ እነ ጋራንግን ከሞስኮዎች እቅፍ እየዶለ ሰፊዋን አፍሪቃዊት ሐገር የሚያነፍረዉ ጦርነት ከሞስኮዎች ፍፃሜ-በሕዋላ እንደ ኢትዮጵያዉ፣ እንደ ሞዛምቢኩ፣ እንደ አንጎላ-ዛኢሩ ሁሉ ዋሽንግተን-ብራስልሶች በሚሹት መስመር መፈፀም ነበረበት።

ዶክተር አል ቱራቢ የሚዘዉሩት የጄኔራል ዑመር ሐሰን አልበሽር መንግሥት በ1990 አጋማሽ የዘመን-እዉነትን ዘንግቶ-ከዘመኑ አለም ዘዋሪዎች ጋር መቂያቂያሙ፣ ወደ ምሥራቅ በጣሙን ወደ ቤጂንግ ማማተሩ፣ የጦርነቱ ፍፃሜ-የእነጋራግን ትግል-ሕልም ከግብ የሚያደርስ መሆኑን ጠቋሚ ነበር።

Unabhängigkeitsreferendum Südsudan Flash-Galerie

ሕዝበ ዉሳኔ

ለካርቱሞች ዙሪያ መለስ ድጋፍ የሚሰጡት አረቦችን ተቃዉሞ፣ ኢትዮጵያ የደረሰዉ ሱዳን ተደግሞ በየሐገራቸዉ የተዳፈነዉን የመገንጠል ጥያቄ ይቀሰቀስላል ብለዉ የሚሰጉትን አፍሪቃዉያንን ቅሬታ ለማለሳለስ የካርቱም ገዢዎች ከሁሉም ጋር እንዲላተሙ መንገዱን መጥረግ ያጭር ጊዜ ሥልት መሳይ ነበር።

ኢትዮጵያን በጣሙን ሰሜናዊ ግዛትዋን ለሰላሳ ዘመናት ያነደደዉ፣ደርግን ለዉድቀት፣ኤርትራን ለነፃነት ያበቃዉ ወይም ኢትዮጵያን ለሁለት የገመሰዉ ረጅም ጦርነት የሚታቀድ፤ የሚደራጅ፣ የሚሰነዘር-የሚዘወረዉ ከሱዳንና ሱዳን ነበር።ሱዳን እየኖሩ፣ በሱዳን እየታገዙ፣ ሱዳን እየሰለጠኑ-እየታጠቁ ኤርትራን ነፃ ያወጡት፣ ደርግን የጣሉት ሐይላት አስመራንና አዲስ አበባን በተቆጠጠሩ በአመት እድሜ የካርቱም ጠላት ሆነዉ-በሱዳን ያወግዙ-በሱዳን ላይ ይዝቱ ገቡ።

እንደ አዲስ አበባና አስመራ መሪዎች ሁሉ ምዕራቦች የሚንቆለጳጵሷቸዉ ካምፓላዎች በቀጥታ ናይሮቢዎች በተዘዋዋሪ በካርቱም አንፃር ተሰለፉ።ሱዳን የተደራጁ፣ በሱዳን መንግሥት የሚደገፉ የተባሉ ታጣቂዎች የግብፁን ፕሬዝዳት ሁሲኒ ሙባረክን አዲስ አበባ ዉስጥ ለመግደል መሞከራቸዉ ደግሞ ካይሮዎችን ለብቀላ ባያዝት-ባያስፎክርም ማስቀየሙ አልቀረም።

ሱዳን በ1956 ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ደቡብ ሱዳኖች ለነፃነት ይሕ ቢቀር ለሰፊ የራስ-ገዝ መብት ያልተዋጉ-ያልተሟገቱበት ዘመን ጥቂት ነዉ።ጦርነቱ ግን በዚሕ ሁሉ ዘመን ከደቡባዊ ሱዳን ዉጪ ሌላዉ የሱዳን ግዛት ደርሶ አያዉቅም ነበር።ካርቱሞች ከአለም ዘዋሪዎች፣ በአለም ዘዋሪዎች ከሚዘወሩት ከፍሪቃና ከአረብ ጎረቤቶቻቸዉ ጋር በተላተሙ በወራት እድሜ ግን መንበሩን አስመራ ያደረገዉ የተቃዋሚዎች ሕብረት ጦር ሰሜን ሱዳንን ያጠቃ ገባ።ጆን ጋራንግ።

«ባለፉት (ዘመናት) ጦርነት የሚደረገዉ በደቡብ ብቻ ነበር።ከመንግሥቱ መቀመጫ ከካርቱም በጣም በራቀዉ አካባቢ።አሁን ግን ሰሜን እየተዋጋን ነዉ።ስልት አርቅቀናል።የሰወስት-ግባር ሥልት። የመጀመሪያዉ የደቡቡ ዉጊያ ነዉ።ሁለተኛዉ አሁን ሰፊ ጥቃት በከፈትንበት በሰሜንም መዋጋት ነዉ።በምሥራቅ ግንባር፥ በደቡብ አባይና በከሰላ ግዛት-የከፈት ነዉ።ሰወስተኛዉ እዚያዉ ካርቱም ዉስጥ ሕዝባዊ አመፅ መቀስቀስ ነዉ።»

ወዲያዉ ምዕራባዊ ሱዳን-ዳርፉር በጦርነት ትተረማመስ ያዘች።አራተኛ ግንባር።በአራት ግንባር የተወጠረዉ የካርቱም መንግሥት ደቡብ ተቃዋሚዎቹን አስቀድሞ ድርድር ይልገባ።ናቫሺ-ኬንያ የተያዘዉ ድርድር፥- የጦር ሜዳዉ የድል-ሽንፈት ሚዛን ወደደፋበት ከሰሜን-ደቡብ እየተላጋ-ጥቂት ጊዜ አስቆጥሮ የደቡቦችን የድል ፈር በቀደደ ስምምነት ተደመደመ።ጥር ሁለት-ሺሕ አምስት።እንደገና ጋራንግ።

ለአርባ ሁለት አመታት በተኮሱ ባስተኮሶት ቦምብ መድፍ-ጥይት ሌሎችን እየጣሉ በሌሎች ከሚተኮስባቸዉ-ያመለጡት ጋራንግ በርግጥ ከሔሊኮብተር አደጋ አላመለጡም።እንደ ቦምቡ ሁሉ ዛሬ የሉም።ምዕራብ ሱዳን ግን እንደነፈረች ነበር።ሱዳንም እስከ መጨረሻዉ ተለወጠች።የሱዳንን የእስከ መጨረሻ ለዉጥ ወይም የሁለትነት ጉዞ-የተቀበሉት፥ ቦምብ እንደማይኖር ቃል የገቡት ጋራንግ ብቻ አልነሩም።አል-በሽር ጭምር እንጂ።

UNMIS im Südsudan

የተመድ ሠራዊት

አል-በሽር ቃላቸዉን እንዳያጥፉ፥አንድ ያለዉ የደቡብ ሱዳን የነፃነት ጉዞ እንዳይጨናጎል በፊርማዉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኮሊን ፓወል አስጠንቅቀዉ ነበር።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ ስምምነቱ እንዳይጣስ ደቡብ ሱዳንን በአስር-ሺሕ ጦር ሲያስጠብቅ እስከ ዛሬ ቆየ።

የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገስት አፄ ሐይለ ስሌላ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የደቡብ ሱዳን አማፂያንን ከካርቱም ገዢዎች ጋር ለማስታራቅ-አንድ ሁለት ያሉት እንደ ሐገር መሪ ሱዳን ለመሸጉ የኤርትራ አማፂያን ካርቱሞች የሚሰጡትን ድጋፍ ለማስቀነስ፥ የዋሽንግተን፥ለንደን፥ ወዳጆቻቸዉን ለማስደስት አስበዉ ወይም ለግል ስምና ዝና አልመዉ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።

ሱዳንን-እንደ ሐገር በ1933 የዋላችላቸዉን ንጉሱ ሊዘነጉት ግን አይችሉም ነበር።የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ተደምስሶ አፄ ሐይለ ስላሴን ዳግም ከዙፋን ያበቃዉ፥ ኢትዮጵያ ዳግም ነፃነቷን የተቀዳጀችዉ የኢትዮጵያ አርበኞች ሱዳን ምድር ተጠልለዉ፥ ተደራጅተዉ፥ ከሱዳን ዘምተዉ፥ በሱዳን ተሻግረዉ ነበር።ጋራንግ በሁለት ሺሕ አምስት ናይሮቢ ላይ እንዳሉት ሁሉ የአፄ ሐይለ-ስላሴ ሽምግልና በ1972 አዲስ አበባ ላይ ለስምምነት ሲበቃ የያኔዎቹ ተፈራራሚዎች ሱዳን ተለወጠች
ብለዉ ነበር።

እየተለወጠች-ወይም ተለወጠች እያስባለች ሳትለወጥ መቀጠል-ወይም እንደገና መለወጥ ለሱዳን በርግጥ እንግዳ አይደለም።የኩሹ ሥርወ-መንግሥት ጠንካራ ንጉስ ካሻታ ግብፅን አስገብሮ መግዛት የጀመረበት ታላቅ ለዉጥ በአስርሺኛ አመቱ ተለዉጦ፣ መሐመድ ዓሊ የመሯቸዉ የግብፅ-ቱርክ ሐይላት ወርረዋት ለገባሪዎቿ ገብራ-ቅኝ ትገዛ ገባች።በሰወስት መቶ-ሐምሳ ዓመተ-ዓለም አክሱሞች የሜሮኢ ሥርወ-መንግሥቷን ከነከከተማቸዉ አጥፍተዉ የእስከዚያ ዘመን ጉዘዋን ለዉጠዉት ነበር።

በሁለት ሺሕ ሁለተኛዉ አመት ግድም መሐዲስት ገዢዎችዋ የኢትዮጵያን ወርረዉ ንጉሷን ገድለዉ ከተሞችዋን በዘበዙ።ሱዳን።ከእንግሊዝ-ግብፆች አገዛዝ ስትወድቅ ተለወጠች፥ ነፃ ስትወጣም ተለወጠች ተባለ።ነፃ በወጣች በሐምሳ-አምስተኛ አመቷ ዘንድሮ-ደግሞ ካንድነት ወደ ሁለትነት የመለወጧ-ጉዞ ሁለት አለ።ለዉጡ እርግጥ እንደሆነ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳት ሳልቫኪር እርግጠኛ ናቸዉ።ግን ሕዝባቸዉ እንዳይጣደፍ መከሩ።

«ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ በሙሉ፥ ምናልባት ድምፃችሁን ዛሬ ለመስጠት ካልቻላችሁ እንድታገሱ እጠይቃለሁ።»በለዉጡ ያልተደሰተ የደቡብ ሱዳን ተወላጅ ካለ-ያለዉ እስካሁን አልተሰማም።አብዛኛዉ ግን በርግጥ ደስተኛ ነዉ።እሳቸዉ እንዳሉት ለግዛቲቱ የአዲስ ዘመን ብስራት፥ለሕዝቡ ደግሞ የመሰቃየት፥ የመንገላታቱ-ፍፃሜ።

«ለኛ ልዩ ቀን ነዉ።የተዋጋንለት፥ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ የሞተለት ከዚሕ እለት ለመድረስ ነዉ። ለደቡብ ሱዳን አዲስ ጅምር።»

የደቡብ ሱዳኖች የነፃነት ትግል-ምኞትን ከእዉነት ያቃረበዉ የሠላም ዉል በሁለት ሺሕ አምስት ናይሮቢ ላይ ሲፈረም ዉሉ እንዳይፈርስ የአለም ሀያላን አስጠንቅቀዉ፥ ሠላም አስከባሪ ሠራዊትም አዝምተዉ ነበር።ዉሉ ተጠብቆ-የሱዳንን ሁለትነት የሚመሰክረዉ ሕዝበ-ዉሳኔ ትናንት ሲጀመርም የአለም ሐያላን ተወካዮች እዚያዉ ነበሩ።

«አሁን የዚሕ ቅፅበት ሁኔታ ለደቡብ ሱዳን አዲስ ዘመን መከፈቱን የሚወክል ነዉ።ለሱዳን ሪፐብሊክ-ለሰሜኗም አዲስ ዘመን መጀመሩን አመልካች ነዉ።»

Sudan Friedensvertrag für den Südsudan unterzeichnet

የሰላም ዉሉ ም/ፕ ዓሊ ጣሐና ጋራንግ

የዩናይትድ ስቴትሱ ሴናተር ጆን ኬሪ።የአዉሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን መሪ ወይዘሮ ቬሮኒክ ደ ኬይሰር በበኩላቸዉ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ለዘመናት ይጠብቀዉ የነበረዉ ትናንት ተጀመረ አሉ።
«ዕለቱን ሕዝቡ ለብዙ ወራትና አመታት ሲጠብቀዉ ነበር።ትልቅ ቀን ነዉ።በትክክል የሚሆነዉ ደግሞ ሕዝበ-ዉሳኔዉ የሚደረግበት ቀን ነዉ።ጥር-ዘጠኝ።ሕዝበ-ዉሳኔዉን ያደራጁትን ወገኖች፥ የሕዝበ ዉሳኔ ኮሚሽኑንና ቢሮዎቹን በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ።ምክንያቱም ታላቅ ሥራ ነዉ-የሰሩት።»

ታላቅ ስራ፥ ታላቅ ቀን።ታላቅ ፌስታ።ደቡብ ሱዳን።የዛሬ አስራ-ስምንት አመት ግድም ካስመራ-ተመሳሳይ ቃል ተስምቶ ነበር።በሁለት ሺሕ-ሁለት ከዲሊ-ምሥራቅ ቲሞር፥ ክዚያ በፊትና በመሐሉ ከብዙ የቀድሞ የሶቬት ሕብረት ሪፐብሎክ ርዕሠ-ከተሞች ብዙ ተስምቶ ነበር።ዛሬ ጁባ ነዉ-ተረኛዉ።ነገ-ነገን የነገ ሰዉ ይበልን።ለዛሬዉ ግን ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ