የደቡብ ሱዳን ህዝበ-ውሳኔ ታዛቢዎች ምሥክርነት፣ | ኢትዮጵያ | DW | 17.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የደቡብ ሱዳን ህዝበ-ውሳኔ ታዛቢዎች ምሥክርነት፣

የደቡብ ሱዳን ህዝበ-ውሳኔ ታዛቢዎች ምሥክርነት፣ የደምፅ አሰጣጡ ሂደትም ሰላማዊና ተዓማኒነት የተንፀባረቀበት ነበረ ነው ያሉት። የህዝበ ውሳኔው አጠቃላይ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2003 ይነገራል ተብሎ ይጠበቃል።

default

የምርC ጣቢያ በባህሪ ከተማ፣ ደቡብ ሱዳን፤ ፊት-ለፊት የሚታየው፣ በሱዳን የዶቸ ቨለ የዐረብኛው ክፍል ዘጋቢ፣ ዑስማን ሺንገር ነው።

ህዝበ ውሳኔውን ከታዘቡት መካከል፤ የአውሮፓ ፓርላማ አባልና ፣ በደቡብ ሱዳን የአውሮፓው ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች መሪ ፣ እንዲሁም «ሚዜሬዎር» የተሰኘው የጀርመን ካቶሊካውያን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሰጡትን ምስክርነት የዶቸ ቨለ ባልደረባ ዳንኤል ፔልዝ በዘገባው ላይ አካቶታል። ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

የአውሮፓ ፓርላማ አባልና በደቡብ ሱዳን የአውሮፓው ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን መሪ Veronique de Kayser ህዝበ ውሳኔው ዓለም አቅፍ ደረጃን እስከምን ድረስ እንዳሟላ ተጠይቀው እንዲህ ነበረ ያሉት።---

«ይህን ዐረፍተ ነገር(ሐረግ) አልተጠቀምንበትም። ህዝበ ውሳኔው ገና አልተቋጨምና! የምርጫው ሂደት ግን ሰላማዊና ተዓማኒነት የተረጋገጠበት ነበረ። የተሳተፈው መራጭ ህዝብ ቁጥርም አጅግ በዛ ያለ እንደነበረ ታዝበናል። እናም ባየነው የመጀመሪያ ዙር ህዝበ ውሳኔ፣ ተደንቀናል፤ ሙሉ-በሙሉም ረክተናል። »

የጀርመን ካቶሊካውያን በጎ አድራጎት ድርጅት (ሚዜሬዎር) ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ዮዘፍ ዛየርም ለቀረበላቸው ተመሳሳይ ጥያቄ መልስ ሲሰጡ፣ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«እኔ እንደ ምርጫ ታዛቢ፤ በተለያዩ የአፍሪቃ ምርጫዎች በታዛቢነት የተሳተፉት ባልደረቦቼም ጭምር፣ ያየነው፣ የተመለከትነው፣ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያለው ምርጫ መካሄዱን ነው። በደቡብ ሱዳን የተከናወነውን የመሰለ የተዋጣለት የምርጫ ሂደት፣ አፍሪቃ ውስጥ እስከዚህም የትም አልተካሄደም ማለት ይቻላል። እዚያ እንደደረስሁ የጠየቀሁት፣ የምርጫውን ዝግጅት የጀመሩት፣ ኅዳር 2 ቀን 2003 ዓ ም ሆኖ ሳለ ፣ የቀራቸው በጣም አጭር ጊዜ ነውና ፣ መሠረተ-ልማቱ እጅግ ኋላ-ቀር በሆነበት አገር፣

እውነት ይሳካላቸዋል? ብዬ ነበር። በመሠረቱ፣ ባየነው ዲስፕሊን፣ በምርጫ ጣቢያዎች፤ በተከናወነው ኀላፊነት ትልቅ ትርጉም በተሰጠው አሠራር እጅግ ነው የተገረምን። የአካል ጉዳተኞች፤ ማየት የተሳናቸው፤ እንዲሁም ሽማግሌዎችና ባልቴቶች፣ ክብካቤ እየተደረገላቸው ሲመርጡ መመልከት የሚያስደንቅ ነበር።»

ህዝበ- ውሳኔው ፤ ትንሽ እንኳ እንከን አላጋጠመውም?

«ሂደቶች ያላንዳች ሳንክ ይከናወናሉ ማለት ይከብዳል። እጅግ ብዙኀኑ መራጮች በተሳተፉባቸው የምርጫ ጣቢያዎች፣ ሁሉም ሰምሮ ነው የተከናወነው። ከዚህ ፍጹም በተለየ ሁኔታ ፤ 5 ሰዎች ዛቻ እንደደረሰባቸውተገንዝበናል ፤ ይህ ደግሞ ቀላል ነገር ነው።

ያሳዝናል፤ በደቡባዊው ኮርዶፋን በአቤዪ አውራጃ፣ ግጭት ተፈጥሮ የሰው ህይወት ጠፍቷል። ይሁንና በአጠቃላይ ሲታይ ፤ ሂደቱ በጥም ጥሩ ነበረ።»

ሰሜን ሱዳን ፤ የደቡቡን የነጻነት ሂደት ለመግታት፣ የምርጫውን ውጤት እንዲለውጥ ወይም በጥርጣሬ እንዲታይ ያደርግ ይሆናል፤ ብለው ደቡባውያኑ አልሠጉም ወይ ?

«ፍርሃት ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ፣በዚሁ ጉዳይ ላይ ማሰብ -ማሰላሰል እንደነበረ፣ ለመታዘብ ችየአለሁ። እዚህ ላይ ፣ ደቡቦቹ ባልጠበቁት ሁኔታ፣ በቴሌቭዥን፤ በራዲዮና በጋዜጣ ሰፊ ዓለም አቀፍ ትኩረት ነው ያገኘው። ታዋቂ ሰዎች፤ ጂሚ ካርተርና ኮፊ አናን በዚያ መገኘታቸው፤ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ እንዲሁ ልዑክ ብቻ ሳይሆን፤ ዕውቁን ሴናተር ፣ ጆን ኬሪን ነበረ የላኩት ። የእነዚህ ሰዎች በዚያ መገኘትም፣ የማይናቅ አስተዋጽዖ አድርጓል። የአፍሪቃ መንግሥታት፣ የደቡብ ሱዳንን ህዝበ -ውሳኔ፣ ነጻነትም ቢሆን ለመቀበል መዘጋጀታቸው፤ በደቡባውያኑ ዘንድ ፣ በራስ መተማመንን ማጠናከሩ አልቀረም። ሰሜኑ ጦርነት ለመክፈት የሚያስችል ቀዳዳ አላገኘም። ቢፈልግም ደቡብ ሱዳናውያንን ማሸነፍ እንደማይችል አይቶታል፤ ተገንዝቦታል።»

በሰሜን ሱዳን በኩል ስለተካሄደው ህዝበ-ውሳኔ፣ ከባልደረቦችዎ ምን ሰሙ?

«ከደቡብ ሱዳን አንጻር በሰሜን ሱዳን የደቡቡን የወደፊት መጻዔ-ዕድል ለመወሰን በተከናወነው ህዝበ-ውሳኔ የተሳታፊዎቹ ቁጥር አነስተኛ ነበረ። በደቡብ ሱዳን በየምርጫ ጣቢያው፤ ድምፅ ለመስጠት የተሠለፈው ህዝብ ብዛት የትእየሌሌ ነበረ። በሰሜን ሱዳን ፤ ለደቡብ ሱዳን ህዝበ-ውሳኔ ፤ ድምፅ ለመስጠት አደባባይ የወጡት፤ በጥም ጥቂቶች እንደነበሩ ባልደረቦቻችን ታዝበዋል። ደስተኞች ሆነው አልታዩም። የሰጠነው ድምፅ ምን ይደረግ ይሆን? የፀጥታ ኅይሎችስ በዐይነ ቁራኛ እየተከታተሉን ይሆን?! በማለት በሥጋት የተዋጡ አልታጡም። እጅግ ከባድ ሁኔታ ነበረ ማለት ይቻላል።»

የምርጫው ውጤት ይፋ ከመገለጡ በፊት ፣ ደቡብ ራሱን ችሎ ነጻ ሀገር እንዲሆን ብዙኀኑ ሳይመርጡ እንዳልቀሩ ነው የሚነገረው። በጁባ ዩኒቨርስቲ 2,663 መራጮች ደቡብ ሱዳን ነጻ እንዲሆን ሲመርጡ አንድነት ይሻላል ያሉት 69 ብቻ ናቸው። ከጁባ በማይርቀው በማላካል የምርጫ ጣቢያም፣ 1,809 ነጻነት ሲሉ፤ ተቃራኒውን ድምፅ የሰጡት 75 ብቻ ሆነው ተገኝተዋል።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ