የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ወታደራዊ ስምምነት | አፍሪቃ | DW | 25.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የደቡብ ሱዳንና የግብፅ ወታደራዊ ስምምነት

ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋ የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ጁባ ተመሳሳይ መግባባት ላይ ከሁለት ዓመታት በፊት ከተነጠለቻት ሰሜን ሱዳን ጋም መድረሷ ተገልጿል።

ሱዳን ትሪቢዩን እንደሚለዉ የደቡብ ሱዳን እና ግብፅ ወታደራዊ ትብብር መፈራረም ይፋ የተደረገዉ በጁባ መንግስት ሥር በሚተዳደረዉ የደቡብ ሱዳን ቴሌቪዥን ነዉ። በመከላከያ ሚኒስትር ኩሎ ማንያንጋ ጁኩ የሚመራ የደቡብ ሱዳን የልዑካን ቡድን ካይሮን በጎበኘበት ወቅት ነዉ ካይሮና ጁባ የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ስምምነቱን የተፈራረሙት። ዝርዝር ስምምነቱ ይፋ ባይሆንም የዜና አዉታሩ ወታደራዊ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበዉ የወታደራዊ ኃይሎች የልምድ ልዉዉጥ፣ ልዩ ኃይሎችን የማሰልጠን እና በጋራ ልምምዶችን ማድረግን ያካትታል። ግብፅም ሆነች ደቡብ ሱዳን አሁን በሚገኙበት ያልተረጋጋ ሁኔታ ሊፈራረሙ የሚችሉት ወታደራዊ ስምምነት እንዴት ዓይነት ይሆናል? ዋና ፅህፈት ቤቱ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የአዲስ አበባዉ ቅርጫፍ ባልደረባ ዶክተር ሰሎም ደርሶ፤ የተባለዉ ዜና እዉነት ከሆነ እንዲያህ ያለዉ ስምምነት በተለይ በግጭት ጦርነት ለምትታመሰዉ ደቡብ ሱዳን ድጋፍ የማፈላለግ ዘመቻ አካል ነዉ ይላሉ።

እንደዘገባዉ የደቡብ ሱዳን መንግስት ይህን የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት ከግብፅ ጋ ከመፈራረሙ ከቀናት በፊት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም ከተነጠለዉ የኻርቱም መንግስት ጋም ተመሳሳይ መግባባት ላይ ደርሷል። በዉስጣዊ የፖለቲካ ቁርቁስ የጁባ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በአፈሙዝ መነጋገር ከጀመሩ ወዲህ በዜጎችና በሀገሪቱ ሃብትና ንብረት ላይ የደረሰዉንና አሁንም የሚደርሰዉን ዉድመት ለማስቆም የተጀመረዉ ድርድር ይህ ነዉ የሚባል ዉጤት ባላስገኘበት በዚህ ወቅት መንግስት የሚፈራረመዉ ወታደራዊ ትብብር አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረዉ እንደሚችል ይገመታል።

አያይዘዉም የፖለቲካ ተንታኙ የዉጭ ወታደራዊ ኃይሎች የሚሳተፉበት ሁኔታ በፖለቲካ ልዩነት የሚወዛገቡት የደቡብ ሱዳን ጦር የተመዛዘዙ ወገኖች ችግሩን በራሳቸዉ ነፃ አካሄድ ለመፍታት የሚችሉበትን አጋጣሚ እየቀነሰ እንዲሄድ እንደሚያደርገዉ አመልክተዋል። ችግሩም ከደቡብ ሱዳን አልፎ ለአካባቢዉ ሃገራትም ሊተርፍ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ከአካባቢዉ ሃገራት ለሰላም ጥረቱ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ የምትገኘዉ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባዉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ምክንያት ከግብፅ ጋ መወዛገብ መቀጠሏ እየታየ ነዉ። ካይሮ ከጁባ ጋ ያደረገችዉ ወታደራዊ ስምምነት በአዲስ አበባ በኩል በምን መልኩ ሊተረጎም ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል?

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች አዲስ አበባ ላይ ጀምረዉት የነበረዉን ዉይይት ዛሬ መቀጠላቸዉ ተሰምቷል። በምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት የልማት ድርጅት IGAD አደራዳሪነት የሚካሄደዉ የሰላም ድርድር ከአንድ ወር በፊት የተኩስ አቁም ማፈራረሙ ይታወሳል። በተግባር ባይዉልም። IGAD ዛሬu ባወጣዉ የጽሑፍ መግለጫም ከፊርማዉ በኋላ የተጣሰዉ የተኩስ አቁም እንደሚያሳስበዉ አመልክቶ፤ አደራዳሪዎች በሀገሪቱ የሚካሄደዉን ጦርነት ለማስቆም ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ ጫና እንዲያሳድር መጠየቃቸዉን ጠቅሷል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic